ሕይወታችሁን በይሖዋ አገልግሎት ዙሪያ ገንቡ
1 ኢየሱስ አድማጮቹን ከሁለት ዓይነት ገንቢዎች ጋር አመሳስሏቸዋል። አንደኛው የሕይወት መንገዱን የገነባው ለክርስቶስ መታዘዝን በሚያመለክተው ዓለት ላይ በመሆኑ የተቃውሞና የመከራ ማዕበሎችን ለመቋቋም ችሎ ነበር። ሌላኛው ደግሞ በአሸዋ በተመሰለውና ከራስ ወዳድነት በመነጨው ያለመታዘዝ ባሕርይ ላይ በመገንባቱ የደረሰበትን ተጽእኖ ሊቋቋም አልቻለም። (ማቴ. 7:24-27) በዚህ የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ውስጥ የምንኖር በመሆናችን ብዙ የስደት ማዕበሎች ያጋጥሙናል። የታላቁ መከራ ጥቁር ደመና ከአድማስ ባሻገር በፍጥነት እየተቃረበ ነው። እምነታችን ምንም ሳይደርስበት እስከ መጨረሻው እንጸና ይሆን? (ማቴ. 24:3, 13, 21) ይህ ሁኔታ በአብዛኛው የተመካው አሁን ሕይወታችንን በምንገነባበት መንገድ ነው። በመሆኑም ‘ክርስቲያናዊ ሕይወቴን ለአምላክ በሚቀርብ የታዛዥነት አገልግሎት ዙሪያ ጽኑ አድርጌ እየገነባሁ ነውን?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን አጣዳፊ ነው።
2 ሕይወታችንን በይሖዋ አገልግሎት ዙሪያ መገንባት ማለት ምን ማለት ነው? ይሖዋን የሕይወታችን ዋነኛ ማዕከል ማድረግ ማለት ነው። መንግሥቱን ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫችን ማድረግን ይጨምራል። በዕለት ተለት የሕይወት እንቅስቃሴዎቻችን በሙሉ አምላክን መታዘዝን ይጠይቃል። ልባችንን ሙሉ በሙሉ በግል፣ በቤተሰብና በጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲሁም በመስክ አገልግሎታችን ላይ በማድረግ ለእነዚህ ነገሮች ቅድሚያ መስጠትን ይጠይቃል። (መክ. 12:13፤ ማቴ. 6:33) እንዲህ ያለው የታዛዥነት አካሄድ ማንኛውንም የመከራ ማዕበል ጸንቶ የሚቋቋም እንደ ዓለት የጠነከረ እምነት ያስገኛል።
3 ኢየሱስ እንዳደረገው በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውንና ለወደፊት ያላቸውን ተስፋ በአምላክ አገልግሎት ዙሪያ በትምክህት ሲገነቡ መመልከቱ የሚያስደስት ነው። (ዮሐ. 4:34) ለቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ያወጡትን ቋሚ ፕሮግራም በጥብቅ ይከተላሉ፤ በውጤቱም የተትረፈረፉ በረከቶችን ያጭዳሉ። አንዲት እናት ከባለቤቷ ጋር ሆና ሁለት ልጆቻቸው ይሖዋን እንዲያገለግሉ እንዴት በተሳካ መንገድ እንዳሳደጓቸው ስትናገር እንዲህ ብላለች:- “ሕይወታችን በእውነት የተሞላ ነበር፤ በሁሉም የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ መገኘት፣ ለስብሰባዎች መዘጋጀትና በእነሱም ላይ መገኘት እንዲሁም በመስክ አገልግሎት ላይ አዘውትሮ መካፈል የሕይወታችን ክፍል ነበር።” ባለቤቷ እንዲህ በማለት ያክላል:- “እውነት የሕይወታችን ክፍል ሳይሆን ሕይወታችን ነው። የተቀረው ነገር በሙሉ በዚህ ዙሪያ የሚሽከረከር ነው።” በተመሳሳይ እናንተም በቤተሰባችሁ ውስጥ ለይሖዋ አገልግሎት ቀዳሚውን ቦታ ትሰጣላችሁ?
4 ሊሠራ የሚችል ሳምንታዊ ፕሮግራም አውጡ፦ የይሖዋ ድርጅት በሳምንት ውስጥ አምስት ስብሰባዎችን በማዘጋጀት ጥሩ የሆነ መንፈሳዊ ልማድ እንድናዳብር ይረዳናል። ሕይወታቸውን በይሖዋ አምልኮ ዙሪያ የሚገነቡ ክርስቲያኖች በእነዚህ አስፈላጊ ስብሰባዎች ላይ ለመካፈል በሚያስችላቸው መንገድ ሥራቸውንና የቤተሰብ ጉዳዮቻቸውን ያመቻቻሉ። እምብዛም አስፈላጊ ያልሆኑ ነገሮች አዘውትረው በስብሰባዎች ላይ እንዳይገኙ እንቅፋት እንዲሆኑባቸው አይፈቅዱም።—ፊልጵ. 1:10፤ ዕብ. 10:25
5 የጎለመሱ ክርስቲያኖች በእያንዳንዱ ቀን ቋሚ የመመገቢያ ሰዓት መኖሩ አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉ ለስብሰባዎች መዘጋጀትን ጨምሮ የግልና የቤተሰብ ጥናት ለማድረግ ቁርጥ ያለ ፕሮግራም ማውጣትም አስፈላጊ መሆኑን ይገነዘባሉ። (ማቴ. 4:4) የግል ጥናት ለማድረግ በየቀኑ ቢያንስ የ15 ወይም የ20 ደቂቃ ጊዜ መመደብ ትችላላችሁ? ቁልፉ ለጥናት በተመደበው ጊዜ ውስጥ ሌሎች ነገሮች ሰርገው እንዳይገቡ መከላከሉ ላይ ነው። ጠቃሚ የሆነ ልማድ አድርጉት። ይህ ምናልባት በየጠዋቱ አሁን ከምትነሱበት ሰዓት ቀደም ብሎ መነሳትን ይጠይቅ ይሆናል። በዓለም ዙሪያ የሚገኙት 17,000 የቤቴል ቤተሰብ አባላት በዕለቱ ጥቅስ ላይ ለመወያየት በማለዳ ይነሣሉ። እርግጥ ነው በማለዳ ለመነሣትና በቂ እረፍትና ጥሩ የአካል ጥንካሬ አግኝቶ ቀጣዩን ቀን ለመጀመር ማታ ላይ በጊዜ መተኛት አስፈላጊ ነው።
6 የቤተሰብ ራስ ከሆንክ የቤተሰብህን የቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴ ፕሮግራም ለማውጣትና ለማደራጀት ቅድሚያውን ውሰድ። አንዳንድ ቤተሰቦች ራት ከበሉ በኋላ ዘና ብለው መጽሐፍ ቅዱስ፣ የዓመት መጽሐፍ ወይም ሌሎች ጽሑፎች ያነባሉ። ልጆቻቸው በመንፈሳዊ ጠንካሮች ሆነው ያደጉላቸው ብዙ ቤተሰቦች ለስኬታቸው አስተዋጽኦ ያደረገላቸው አንዱ ነገር በሳምንቱ ውስጥ አንድ ላይ ሆነው በመንፈሳዊ የሚታነጹበት አንድ ምሽት መመደባቸው መሆኑን ተናግረዋል። ይህ ዓይነቱ ፕሮግራም ያለው አንድ አባት እንደሚከተለው ብሏል:- “ለልጆቻችን መንፈሳዊ እድገት በአብዛኛው አስተዋጽኦ ያበረከተው ነገር ከዛሬ 30 ዓመት በፊት ጀምሮ ዘወትር ረቡዕ ማታ የምናደርገው የቤተሰብ ጥናት እንደሆነ ይሰማኛል።” ሦስቱም ልጆቹ የተጠመቁት ገና ትንሽ እያሉ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ሦስቱም ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ገብተዋል። ከቤተሰብ ጥናት በተጨማሪ የመስክ አገልግሎት አቀራረቦች ወይም በስብሰባ ላይ የሚቀርቡ ክፍሎችና ሌሎች ገንቢ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን አንድ ላይ ማድረግ ይቻላል።
7 በሳምንታዊ ፕሮግራማችሁ ውስጥ ለመንግሥቱ ስብከት የሚሆን ‘ጊዜ ዋጅታችኋል?’ (ቆላ. 4:5) አብዛኞቻችን የቤተሰብና የጉባኤ ኃላፊነቶች ስላሉብን በሥራ የተጠመደ ሕይወት እንመራለን። በየሳምንቱ በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ ለመካፈል ቁርጥ ያለ ዝግጅት ካላደረግን ለዚህ አስፈላጊ እንቅስቃሴ የምናውለውን ጊዜ ሌሎች ነገሮች በቀላሉ ሊሻሙት ይችላሉ። የአንድ ትልቅ የከብት ርቢ ባለቤት እንዲህ ብሏል:- “በ1944 አካባቢ በአገልግሎት ለመካፈል የምችለው አንድ የተወሰነ ቀን ከመደብኩ ብቻ መሆኑን ተገነዘብኩ። እስከ ዛሬ ድረስ በሳምንቱ ውስጥ አንድ ቀን ለአገልግሎት አውላለሁ።” አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ ቋሚ ጊዜ መመደቡ በምሥክርነቱ እንቅስቃሴ በወር በአማካይ 15 ሰዓት እንዲያሳልፍ አስችሎታል። ቅዳሜ የሚሠራው ማንኛውም ዓይነት ሰብዓዊ ሥራ ካለው ጠዋት ከሚያደርገው የመስክ አገልግሎት በኋላ ለመሥራት ፕሮግራም ይይዝለታል። አንተና ቤተሰብህ በየሳምንቱ ቢያንስ አንዱን ቀን ለመስክ አገልግሎት ለማዋል ፕሮግራም ልታወጡ ትችላላችሁ? ይህንንስ መንፈሳዊ የሕይወት መንገዳችሁ ክፍል ልታደርጉት ትችላላችሁ?—ፊልጵ. 3:16
8 የዘወትሩን የሕይወት ልማዳችሁን መርምሩ፦ ሕይወታችንን በይሖዋ አገልግሎት ዙሪያ እንዳንገነባ እንቅፋት የሚሆኑ ሌሎች ነገሮችም አሉ። ድንገተኛ ሁኔታዎች ለጥናት፣ ለስብሰባዎችና ለአገልግሎት በጥንቃቄ ያወጣነውን እቅድ ሊያሰናክሉ ይችላሉ። እንዲሁም ጠላታችን ሰይጣን ‘መንገዳችንን ለማሰናከልና’ እቅዶቻችን ሁሉ መና ሆነው እንዲቀሩ ለማድረግ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። (1 ተሰ. 2:18፤ ኤፌ. 6:12, 13) እነዚህ እንቅፋቶች ተስፋ ቆርጣችሁ እጃችሁን እንድትሰጡ እንዲያደርጓችሁ አትፍቀዱ። ለቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ያወጣችሁትን ፕሮግራም ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስፈልገውን ማንኛውንም ማስተካከያ አድርጉ። ጠቃሚ የሆነን ነገር ለመፈጸም ቆራጥነትና መንፈሰ ጠንካራነት አስፈላጊ ናቸው።
9 ዓለማዊ ተጽእኖዎችና ወደ ኋላ የሚጎትተን ፍጹም ያልሆነው ሥጋችን ጊዜያችንንና ትኩረታችንን ይበልጥ ሊያጠፉ የሚችሉ መንፈሳዊ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎችን አስርገው እንዲያስገቡብን መፍቀድ የለብንም። እንደሚከተሉ ያሉ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ራስን መመርመር አስፈላጊ ነው:- ‘የሕይወት አካሄዴ ቀስ በቀስ ሚዛኑን እየሳተ ወይም አቅጣጫውን እየቀየረ ነው? በዚህ ዓለም በሚገኙ አላፊ በሆኑ ነገሮች ዙሪያ ሕይወቴን መገንባት ጀምሬያለሁን? (1 ዮሐ. 2:15-17) በግል ለምከታተላቸው ነገሮች፣ ለመዝናኛ ጉዞዎች፣ ለስፖርት እንቅስቃሴዎች ወይም ቴሌቪዥን መመልከትንና በኢንተር ኔት መጠቀምን ጨምሮ ለሌሎች መዝናኛዎች የማጠፋው ጊዜ ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ከማውለው ጊዜ ጋር ሲነጻጸር ምን ያክል ነው?’
10 ሕይወታችሁ ከጊዜ ወደ ጊዜ እጅግም አስፈላጊ ባልሆኑ ጉዳዮች ውስጥ እየተተበተበ እንዳለ ከተሰማችሁ ምን ማድረግ ይኖርባችኋል? ጳውሎስ ወንድሞቹ “እንዲስተካከሉ” ወይም “ተገቢውን አቅጣጫ እንዲይዙ” እንደጸለየ ሁሉ በአገልግሎቱ ላይ እንድታተኩሩ እንዲረዳችሁ ይሖዋን ለምን አትለምኑትም? (2 ቆሮ. 13:9, 11, የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) ከዚያም ውሳኔያችሁን ለማክበርና ተፈላጊ ማስተካከያዎችን ለማድረግ ቁርጥ አቋም ውሰዱ። (1 ቆሮ. 9:26, 27) ይሖዋ ለእሱ ከምታቀርቡለት አገልግሎት ወደ ቀኝም ወደ ግራም እንዳትሉ ይረዳችኋል።—ከኢሳይያስ 30:20, 21 ጋር አወዳድር።
11 በአምላክ አስደሳች አገልግሎት ተጠመዱ፦ ደስታ ለማግኘት ባለ በሌለ ኃይላቸው ፍለጋ ያደረጉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ሕይወታቸው ፍጻሜ ሲቃረቡ በጉጉት የሰበሰቧቸው ቁሳዊ ነገሮች ዘላቂ ደስታ እንዳላስገኙላቸው ይገነዘባሉ። ልፋታቸው ሁሉ ‘ነፋስን እንደመከተል ነበር።’ (መክ. 2:11) በሌላ በኩል ግን ይሖዋን ‘ሁልጊዜ በፊታችን በማየት’ ሕይወታችን በእርሱ ላይ እንዲያተኩር የምናደርግ ከሆነ ጥልቅ እርካታ እናገኛለን። (መዝ. 16:8, 11) እንዲህ የምናደርግበት ምክንያት በሕይወት እንድንኖር ያስቻለን ይሖዋ ስለሆነ ነው። (ራእይ 4:11) ታላቅ ዓላማ አውጪ ከሆነው አምላክ የተለየ ሕይወት ትርጉም የለሽ ነው። ይሖዋን ማገልገል ዘላቂ አዎን፣ ዘላለማዊ በሆነ መንገድ ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን በሚጠቅምና ዓላማ ባለው እንቅስቃሴ ሕይወታችን እንዲሞላ ያደርጋል።
12 ወደ ፍጻሜው እየገሰገሰ ያለውን ይህን የሰይጣን ዓለም በተመለከተ ቸልተኞች ልንሆን ወይም የጥድፊያ ስሜታችንን ልናጣ አይገባም። የዕለት ተዕለት ሕይወታችን ለወደፊቱ ጊዜ ባለን አመለካከት ላይ ተጽእኖ ያሳድራል። ዓለምን የሚያጥለቀልቅ የጥፋት ውኃ እንደሚመጣ ያላመኑት በኖኅ ዘመን የነበሩት ሰዎች የግል ፍላጎታቸውን በማሳደድ ማለትም በመብላት፣ በመጠጣትና በማግባት ላይ ሕይወታቸው እንዲያተኩር በማድረጋቸው የጥፋት ውኃ ‘እስከወሰዳቸው’ ጊዜ ድረስ ‘ምንም አላወቁም ነበር።’ (ማቴ. 24:37-39) ዛሬም ሕይወታቸው በዚህ ዓለም ላይ እንዲያተኩር የፈቀዱ ሰዎች የወደፊት ተስፋቸው ከፊታቸው በሚጠብቃቸው በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እጅግ ታላቅ በሆነው ጥፋት ማለትም “በይሖዋ ቀን” ሲፈረካከስ ይመለከታሉ።—2 ጴጥ. 3:10-12
13 ስለዚህ ሕይወታችሁን ሕያው በሆነው አምላክ በይሖዋና የእሱን ፈቃድ በማድረግ ላይ መገንባታችሁን ቀጥሉ። ይህን ሕይወታችሁን እንደ ይሖዋ ላለው የታመነ ደጋፊ ከማዋል የተሻለ ምንም ነገር የለም። እርሱ አይዋሽም፤ የሰጣቸውን ተስፋዎች በሙሉ ይፈጽማል። (ቲቶ 1:2) እርሱ አይሞትም፤ በይሖዋ ዘንድ በአደራ የተቀመጠ ነገር ሁሉ አይጠፋም። (ዕን. 1:12፤ 2 ጢሞ. 1:12) አሁን በመገንባት ላይ ያለነው የእምነትና የታዛዥነት ሕይወት ደስተኛ የሆነውን አምላካችንን በማገልገል ለዘላለም የሚዘልቀው ሕይወታችን አንድ ብሎ የሚጀምርበት ብቻ ነው!—1 ጢሞ. 1:11፤ 6:19
[በገጽ 1 ላይ የሚገኝ ሥዕል3]
“እውነት የሕይወታችን ክፍል ሳይሆን ሕይወታችን ነው።
የተቀረው ነገር በሙሉ በዚህ ዙሪያ የሚሽከረከር ነው።”