አስቀድማችሁ ዕቅድ አውጡ!
1 የይሖዋ ድርጅት በመንፈሳዊ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ለማሟላት ታቅደው የተዘጋጁ ቋሚ የቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ፕሮግራም ያወጣል። ዕቅድ ተይዞላቸው ከሚከናወኑት ዝግጅቶች ሁሉ የተሟላ ጥቅም ለማግኘት የሚያነሳሳን ለዝግጅቶቹ ያለን አድናቆት ነው። እነዚህም የተጓዥ የበላይ ተመልካች ጉብኝቶችን፣ የልዩና የወረዳ እንዲሁም የአውራጃ ስብሰባዎችንና በጉባኤው የታቀዱ ሌሎች ልዩ እንቅስቃሴዎችን ያካትታሉ። (ማቴ. 5:3 NW) ሆኖም አንዳንዶች ሌሎች ነገሮች ለማከናወን ፕሮግራማቸውን በማስያዛቸው ከእነዚህ መንፈሳዊ ዝግጅቶች ብዙዎቹ እንዲያመልጧቸው ይፈቅዳሉ። ይህን ለማስቀረት ምን ማድረግ እንችላለን? ቀዳሚ ሥፍራ ሊሰጣቸው የሚገቡት ከሁሉ ‘ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች’ ቲኦክራሲያዊ ባልሆኑ እንቅስቃሴዎች ቦታ እንዳያጡ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?—ፊልጵ. 1:10
2 በጥበብ ዕቅድ ማውጣት ያስፈልጋል፦ ምሳሌ 21:5 [NW] “የትጉህ ሰው ዕቅድ ጥቅም አለው፤ ችኩል የሆነ ሰው ሁሉ ግን ችግር ላይ ይወድቃል” ሲል ይመክራል። መንፈሳዊ “ጥቅም” ማግኘት እንድንችል በፕሮግራም የተያዙትን ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች በአእምሮአችን ይዘን አስቀድመን ጥንቃቄ የተሞላበት ዕቅድ ማውጣት አለብን። በግል ለምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ፕሮግራም ስንይዝ መንፈሳዊ በረከቶች ለማጨድ ከምንገኝባቸው ፕሮግራሞች ጋር በማይጋጩበት መንገድ መሆን አለበት። ከፊታችን ያሉትን ቲኦክራሲያዊ ክንውኖች ግምት ውስጥ ሳናስገባ በችኮላ በግል ማድረግ ለምንፈልጋቸው ነገሮች ዕቅድ ካወጣን መንፈሳዊ ‘ችግር’ ሊደርስብን ይችላል።
3 ፈጽሞ አያምልጣችሁ! ሁላችንም ለእረፍት፣ በሥራ ጉዳይ ለሚደረግ ጉዞ፣ ዘመድ ለመጠየቅና እነዚህን ለመሳሰሉ ሌሎች ጉዳዮች ዕቅድ እናወጣለን። አንድ ነገር ለማድረግ ቃል ከመግባትህ ወይም ያወጣሃቸውን ዕቅዶች ከማጽደቅህ በፊት ከፊታችን ያሉትን የመንፈሳዊ እንቅስቃሴ ፕሮግራሞች ተመልከት። አንተ ወደ ሌላ ቦታ በምትሄድበት ጊዜ የወረዳ አገልጋዩ እንደሚጎበኛችሁ ወይም ለአንድ ትልቅ ስብሰባ ፕሮግራም መያዙን ካወቅህ መገኘት እንድትችል ጉዳዮችህን እንደገና ለማስተካከል ልባዊ ጥረት አድርግ። በፕሮግራም የተያዙ ጎላ ያሉ ክንውኖች መኖራቸው የሚነገረን አስቀድሞ ነው። የጉባኤህ ሽማግሌዎች በአካባቢህ ሊደረጉ ስለታቀዱት ስብሰባዎች ሊነግሩህ ይችላሉ።
4 አርቆ በማስተዋልና ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑት ነገሮች አስቀድሞ ዕቅድ በማውጣት ‘ለእግዚአብሔር ክብርና ምስጋና የጽድቅ ፍሬ የሞላብን’ ሆነን እንገኛለን።—ፊልጵ. 1:11