‘ልትረዱና ልታካፍሉ የተዘጋጃችሁ ሁኑ’
1 ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት የእምነት አጋሮቹ ‘መልካምን እንዲያደርጉ፣ በበጎም ሥራ ባለጠጎች እንዲሆኑ፣ ሊረዱና ሊያካፍሉም የተዘጋጁ እንዲሆኑ’ እንዲያበረታታቸው ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ መመሪያ ሰጥቶት ነበር። (1 ጢሞ. 6:18) በተጨማሪም ጳውሎስ የዕብራውያን ክርስቲያኖች ‘መልካም ማድረግንና ለሌሎች ማካፈልን’ እንዳይረሱ አሳስቧቸዋል። (ዕብ. 13:16) ጳውሎስ እነዚህን መመሪያዎች የጻፈው ለምንድን ነው? ‘በጎ ሥራ ለሚያደርጉ ሁሉ ምስጋናና ክብር ሰላምም እንደሚሆንላቸው’ ያውቅ ስለነበር ነው።—ሮሜ 2:10
2 ይሖዋ አምላክ ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን የሁሉ ነገር ባለቤት ነው። (ራእይ 4:11) የራሱ ንብረት የሆኑትን ነገሮች ተጠቅሞ የሚያደርግልንን ሁሉ ከልብ እናደንቃለን። አብዛኛው የሰው ዘር ውለታ ቢስ ቢሆንም ልዑሉ አምላክ ሕይወትን ለማቆየት ከሚያስፈልጉት የልግስና ዝግጅቶቹ ሁሉም ሰው መጠቀሙን እንዲቀጥል ፈቅዷል። (ማቴ. 5:45) ሌላው ቀርቶ የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ሲል ውድ ልጁን መሥዋዕት አድርጎ ሰጥቶናል። አምላክ ያሳየን ፍቅር ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ ለጋሶች በመሆን አመስጋኝነታችንን እንድናሳይ አይገፋፋንምን?—2 ቆሮ. 5:14, 15
3 ምን ልናካፍል እንችላለን? ያለንን ማንኛውንም ንብረት በአምላክ ዓይን አስደሳች በሆነ መንገድ መጠቀማችን ተገቢ ነው። ዓለም አቀፉን የመንግሥት ሥራ በቁሳዊና በመንፈሳዊ መንገድ መደገፍ እንደምንፈልግ ምንም ጥርጥር የለውም። እርግጥ ነው፣ ምሥራቹ ‘የእግዚአብሔር የማዳን ኃይል ስለሆነ’ ማንኛውም ሰው ሊያገኘው ከሚችለው ከፍተኛ ዋጋ ያለው ውድ ሃብት ሁሉ የላቀ ነው። (ሮሜ 1:16) በየወሩ ጊዜያችንንና ንብረታችንን ለስብከቱና ለማስተማሩ ሥራ በልግስና በማዋል ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራውን ውድ መንፈሳዊ ሃብት ለሌሎች ማካፈል እንችል ይሆናል።
4 ይሖዋ ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸውን ስንደግፍ በጣም ይደሰታል። እንደሚባርከን ቃል ከመግባቱም በላይ “በቁጣ ቀን ሀብት አትረባም፤ ጽድቅ ግን ከሞት ታድናለች” ሲል ያሳስበናል። (ምሳሌ 11:4፤ 19:17) የመንግሥቱን ሥራ በቁሳዊ ነገሮች መደገፍና ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ ላይ ሙሉ ተሳትፎ ማድረግ ለጋሶችና ለማካፈልም የተዘጋጀን መሆናችንን የምናሳይበት ግሩም መንገድ ነው።