መልካም ማድረግንና ለሌሎች ማካፈልን አትርሱ
1 ዶርቃ “ዘወትር በትጋት በጎ ነገር እያደረገችና ድኾችን እየረዳች ትኖር ነበር።” (ሥራ 9:36, 39) የነበራት የልግስና መንፈስ በሚያውቋት ሰዎችና በይሖዋ አምላክ ፊት ተወዳጅ እንድትሆን አድርጓታል። ዕብራውያን 13:16 “መልካም ማድረግንና ያላችሁንም ከሌሎች ጋር መካፈልን አትርሱ፤ እግዚአብሔር ደስ የሚሰኘው እንደዚህ ባለው መሥዋዕት ነውና” ይላል። በዛሬው ጊዜ መልካም ማድረግና ለሌሎች ማካፈል የምንችለው እንዴት ነው?
2 ሌሎችን መጥቀም የምንችልበት አንደኛው መንገድ ‘ሀብታችንን’ በማካፈል ነው። (ምሳሌ 3:9) ለዓለም አቀፉ ሥራ የምናደርገው የገንዘብ መዋጮ በዓለም ዙሪያ የመንግሥት አዳራሾች፣ ትላልቅ መሰብሰቢያ አዳራሾችና ቅርንጫፍ ቢሮዎች ለመገንባት ያስችላል። የምናደርገው ልግስና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ቲኦክራሲያዊ ትምህርትና የሚያንጹ መንፈሳዊ ባልንጀሮች ለማግኘት አስችሏቸዋል።
3 ሰዎችን አጽናኑ:- አንድ ዓይነት አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ የይሖዋ ሕዝቦች ለእምነት ወንድሞቻችንና እምነታችንን ለማይጋሩ ሰዎች ‘መልካም ለማድረግ’ ዝግጁዎች ነን። (ገላ. 6:10) በፈረንሳይ አንድ የኬሚካል ፋብሪካ በፈነዳ ጊዜ በፋብሪካው አጠገብ የሚኖሩ አንድ ባልና ሚስት እንዲህ ብለው ተናግረዋል:- “ክርስቲያን ወንድሞቻችን ወዲያው ደረሱልንና የእኛንም ሆነ በሕንፃው ውስጥ የሚገኙ ሌሎች መኖሪያ ቤቶችን አጸዱ። ይህን የሚያህሉ ሰዎች ሊረዱን መምጣታቸው ጎረቤቶቻችንን በጣም አስደነቃቸው።” ሌላም እህት “ሽማግሌዎች ተረባርበው ረዱን። ሊያጽናኑንና ሊያበረታቱን መጡ። እንደ እውነቱ ከሆነ ከቁሳዊው እርዳታ ይበልጥ ያስፈልገን የነበረው ይህ ነበር” ብላለች።
4 ለጎረቤቶቻችን መልካም ልናደርግ የምንችልባቸው ብዙ መንገዶች ቢኖሩም ከሁሉ የላቀው መንገድ ውድ የሆነውን የእውነት እውቀት ማካፈል ነው፤ ይህም ይሖዋ ራሱ ቃል የገባልንን “የዘላለም ሕይወት ተስፋ” ይጨምራል። (ቲቶ 1:1, 2) በዓለም ላይ በሚፈጸሙት ሁኔታዎችና ኃጢአተኛ በመሆናቸው ምክንያት ለሚያዝኑ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት እውነተኛ መጽናኛ ይሰጣቸዋል። (ማቴ. 5:4) አቅሙ እስካለን ድረስ መልካም ማድረግንና ለሌሎች ማካፈልን አንርሳ።—ምሳሌ 3:27