የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • km 3/02 ገጽ 3-4
  • ‘በበጎ ሥራ ባለ ጠጎች ሁኑ’

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ‘በበጎ ሥራ ባለ ጠጎች ሁኑ’
  • የመንግሥት አገልግሎታችን—2002
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ‘የአምላክን ቃል በተሟላ ሁኔታ ስበኩ’
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2002
  • መልካም ለማድረግ የምትቀኑ ሁኑ!
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2003
  • ‘ምሥራቹን በሚገባ መሥክሩ’
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2008
  • ‘ለሰው ሁሉ መልካም አድርጉ’
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2002
ለተጨማሪ መረጃ
የመንግሥት አገልግሎታችን—2002
km 3/02 ገጽ 3-4

‘በበጎ ሥራ ባለ ጠጎች ሁኑ’

1 ሐዋርያው ጳውሎስ በቅንዓት ባከናወነው አገልግሎቱ መገባደጃ አካባቢ ከጢሞቴዎስና ከቲቶ ጋር በጣም ተቀራርቦ ይሠራ ነበር። ለሁለቱም ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ማበረታቻ ጻፈላቸው። ለቲቶ “እግዚአብሔርንም የሚያምኑት በመልካም ሥራ በጥንቃቄ” መጽናት እንደሚገባቸው ነግሮታል። (ቲቶ 3:8) ለጢሞቴዎስ ደግሞ ተስፋቸውን በአምላክ ላይ የሚያደርጉ “በበጎ ሥራ ባለ ጠጎች” መሆን እንዳለባቸው ነግሮታል። (1 ጢሞ. 6:17, 18) ይህ ለሁላችንም የሚሆን ግሩም ምክር ነው! ይሁን እንጂ በሕይወታችን ውስጥ በጎ ሥራዎች እንድንሠራ የሚገፋፋን ምንድን ነው? ከፊታችን ባሉት ጊዜያት ምን በጎ ሥራ ማከናወን እንችላለን?

2 በመልካም ሥራዎች ባለ ጠጎች ለመሆን የሚያነሳሳን ውስጣዊ ግፊት በይሖዋ ላይ ካለን እምነትና ለእሱ ካለን ፍቅር እንዲሁም ይሖዋ ለሰጠን ድንቅ ተስፋዎች ካለን አድናቆት የሚመነጭ ነው። (1 ጢሞ. 6:18, 19፤ ቲቶ 2:11) በተለይ በዚህ ወቅት ይሖዋ ልጁን ወደ ምድር በመላክ ኢየሱስ የአባቱን ስም ከነቀፋ ነጻ እንዲያደርግና ለሚገባቸው የሰው ልጆች ሁሉ የዘላለም ሕይወት የሚያገኙበት መንገድ እንዲከፍት ማድረጉን እናስታውሳለን። (ማቴ. 20:28፤ ዮሐ. 3:16) ይህ መጋቢት 28 በሚከበረው በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ይበልጥ ግልጽ ሆኖ ይብራራል። ያገኘነው የዘላለም ሕይወት ተስፋ “በበጎ ሥራ ባለ ጠጎች” ለመሆን የቻልነውን ሁሉ እንድናደርግ አያነሳሳንም? እንደሚያነሳሳን የተረጋገጠ ነው! በዚህ ወቅት ምን ሥራ ልናከናውን እንችላለን?

3 በመጋቢትና በቀጣዮቹ ወራት የምናከናውናቸው በጎ ሥራዎች፦ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በዓመቱ ውስጥ የላቀ ግምት በሚሰጡት የመታሰቢያው በዓል ላይ እንደምንገኝ ምንም ጥርጥር የለውም። (ሉቃስ 22:19) ሆኖም በበዓሉ ዕለት የተቻለውን ያህል ብዙ ሰዎች ተገኝተው አብረውን እንዲደሰቱ እንፈልጋለን። በጥር 1, 2002 መጠበቂያ ግንብ እትም ላይ ያለውን የአገልግሎት ሪፖርት ተመልከት። ባለፈው ዓመት በምድር ዙሪያ በሚገኙ በብዙ አገሮች የመታሰቢያው በዓል ተሰብሳቢዎች ቁጥር ከአስፋፊዎቹ በሦስት፣ በአራት፣ በአምስት ወይም ከዚያ በላይ እጥፍ ይበልጥ እንደነበር ትገነዘባለህ። የመታሰቢያውን በዓል የመጋበዣ ወረቀት በአገልግሎት ክልላቸው ውስጥ በስፋት ለማሰራጨት ሁሉም የጉባኤው አባላት ትጋት የተሞላበት ጥረት እንዳደረጉ ምንም ጥርጥር የለውም። እኛም ከአሁን ጀምሮ እስከ መጋቢት 28 ባለው ጊዜ ውስጥ ሰዎች ስለ መዳን ተስፋ እንዲማሩ ወደ መታሰቢያው በዓል በመጋበዙ ሥራ የቻልነውን ያህል በርካታ ሰዓት ለማሳለፍ እንፈልጋለን።

4 ‘መልካሙንም ለማድረግ እየቀናን’ ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ በግለት መካፈላችንን በመቀጠል በሚያዝያም “በበጎ ሥራ ባለ ጠጎች” ለመሆን የሚያስችል ጥሩ አጋጣሚ አለን። (ቲቶ 2:14፤ ማቴ. 24:14) በመጋቢት ረዳት አቅኚ መሆን ካልቻልክ በሚያዝያ እና/ወይም በግንቦት ረዳት አቅኚ ሆነህ ማገልገል ትችል ይሆን? በመጋቢት አቅኚ ሆነህ እያገለገልክ ከሆነ ደግሞ በዚያው መቀጠል ትችላለህ?

5 አንዳንዶች ወደ መሥሪያ ቤታቸው ሲሄዱ በመንገድ ላይ ወይም ማለዳ ሱቃቸውን ለሚከፍቱ ሰዎች በመመሥከር አንድ ሰዓት ወይም ከዚያ የሚበልጥ ሰዓት በአገልግሎት ማሳለፍ እንደሚችሉ ተገንዝበዋል። ሌሎች ደግሞ ከምሳ ሰዓታቸው ከፊሉን ለምሥክርነት ይጠቀሙበታል። አንዳንዶች ይህን ሰዓት ከሥራ ባልደረባቸው ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ያውሉታል። የቤት እመቤት የሆኑ ብዙ እህቶች ልጆቻቸው ትምህርት ቤት ሲሄዱ ለመስክ አገልግሎት የሚሆናቸውን ጊዜ መመደብ ችለዋል። የቤት ውስጥ ተግባሮቻቸውን ለማከናወን አንዳንድ ቀናት ከወትሮው ትንሽ ቀደም ብለው በመነሳት በቀኑ ውስጥ ለስብከቱና ለማስተማሩ ሥራ የበለጠ ጊዜ አግኝተዋል።​—⁠ኤፌ. 5:15, 16

6 ረዳት አቅኚ ሆነህ ለማገልገል ሁኔታህ ባይፈቅድልህ እንኳን በአገልግሎቱ የበለጠ ተሳትፎ ለማድረግ የሚያስችል የግል ፕሮግራም ማውጣት ትችል ይሆናል። ይህም ‘መልካምን ለማድረግ በበጎም ሥራ ባለ ጠጋ ለመሆን’ እንዲሁም እውነትን ለሌሎች ‘ለማካፈል የተዘጋጀህ’ በመሆን ረገድ አቅምህ የሚፈቅደውን ሁሉ ለማድረግ ያስችልሃል።​—⁠1 ጢ⁠ሞ. 6:18

7 ደቀ መዛሙርት የማድረጉን በጎ ሥራ አስታውሱ፦ በየዓመቱ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ ይገኛሉ። በጉባኤ ውስጥ ያሉ አንዳንዶች በበዓሉ ላይ የተገኙ ሆኖም በአሁኑ ወቅት የማያጠኑ ሰዎችን ቀርበው ማነጋገር ይችሉ ይሆን? መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ የመርዳት ግብ በመያዝ ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ ይቻል ይሆን? በመታሰቢያው በዓል ላይ ከተገኙት ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ የይሖዋ ምሥክር ዘመድ ይኖራቸው ይሆናል። ሌሎች ደግሞ ቀደም ሲል ያጠኑ የነበሩ ሊሆኑና አሁን የሚያስፈልጋቸው ጥናታቸውን እንዲቀጥሉና በስብሰባዎች ላይ አዘውትረው እንዲገኙ ትንሽ ማበረታቻ መስጠት ብቻ ሊሆን ይችላል። ከእኛ ጋር ተባብረው ይሖዋን በንቃት ሲያገለግሉ ማየት ምንኛ የሚያስደስት ነው!

8 በመጋቢትና በቀጣዮቹ ወራት አገልግሎታችንን ከፍ ስናደርግ ተመልሰን ልናነጋግራቸው የምንችል ፍላጎት ያሳዩ ብዙ ሰዎች ማግኘታችን አይቀርም። ጥያቄ አቅርባችሁላቸው ሂዱ። ከዚያም በሚቀጥለው ጉብኝታችሁ ወቅት መልሱን እንደምትነግሯቸው ግለጹላቸው። እንደዚህ ማድረጋችን ለተመላልሶ መጠየቅ መንገድ ይጠርግልናል። ሳንዘገይ ተመላልሶ መጠየቅ ማድረጋችን የተሻለ ይሆናል። የመጀመሪያ ውይይት ባደረግንበት ወቅት ጥናት ማስጀመር ካልቻልን በተቻለ መጠን በቀጣዩ ጉብኝት ወቅት ጥናት ለማስጀመር እንሞክር።

9 በመንገድ ላይ ምሥክርነት በምንካፈልበት ጊዜ ሰዎችን አስቁመን ለማነጋገር ንቁዎች መሆን ይገባናል። ብዙ አስፋፊዎች በመንገድ ላይ ካነጋገሯቸው ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ስማቸውን፣ አድራሻቸውንና የስልክ ቁጥራቸውን ተቀብለዋል። ያነጋገራችሁት ሰው በእናንተ የአገልግሎት ክልል ውስጥ የማይኖር ከሆነ የግለሰቡን ስምና አድራሻ በግልጽ ጽፋችሁ (ወይም Please Follow up (S-43) የተባለውን ቅጽ ከመንግሥት አዳራሹ በመውሰድ ሞልታችሁ) ለጉባኤው ጸሐፊ ስጡት። ጸሐፊውም ያነጋገራችሁት ሰው በሚኖርበት ክልል ላለው ጉባኤ ይልከዋል። ጸሐፊው እንደዚያ ማድረግ ካልቻለ ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው ያስተላልፈዋል። በዚህ መንገድ የሰዎቹን ፍላጎት መኮትኮት ይቻላል።

10 ግለሰቡ የሰጣችሁ የስልክ ቁጥሩን ብቻ ከሆነ ስልክ በመደወል ተመላልሶ መጠየቅ አድርጉለት። ልትወያዩ የምትፈልጉትን ርዕስ ቀደም ብላችሁ ተዘጋጁ። በቀላሉ ማየት እንድትችሉ የማመራመር መጽሐፋችሁን አጠገባችሁ አስቀምጡት። አንዳንዶች እቤታቸው ሊያገኟቸው ያልቻሉትን ሰዎች ጨምሮ ከአንዳንድ ግለሰቦች ጋር በስልክ ለማጥናት ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸዋል። አንዲት እህት ከቤት ወደ ቤት ስታገለግል ያገኘቻትን ሴት የስልክ ቁጥሯን ጠየቀቻት፤ በውጤቱም ሁለት የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ማስጀመር ቻለች።

11 አገልግሎት ያቆሙትን በመርዳት ረገድ ከሽማግሌዎች ጋር ተባብራችሁ ሥሩ፦ ሽማግሌዎች አገልግሎት ላቆሙ ፍቅራዊ እርዳታ ለማድረግ ይፈልጋሉ። ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ በራሳቸው ተነሳሽነት እንደገና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀምረዋል። በመዝሙር 91 ላይ የተገለጸውን መንፈሳዊ ደህንነት ለማግኘት ከይሖዋ ድርጅት ጋር የቀረበ ግንኙነት ማዳበር እንዳለባቸው ተገንዝበዋል። አንዳንዶቹ በአሁኑ ወቅት በመስክ አገልግሎት ለመሳተፍ ዝግጁ ናቸው። ሌሎች አገልግሎት ያቆሙ ሰዎችም በዚህ ወር በመታሰቢያው በዓል ላይ ከተገኙ የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላቸው ይስማሙ ይሆናል። እንደዚያ ከሆነ ሽማግሌዎች አንድ ሰው እርዳታ የሚፈልጉትን ሰዎች እንዲያስጠና ዝግጅቶች ያደርጋሉ። በዚህ መንገድ እርዳታ እንድታበረክት ከተጠየቅህ የምታደርገው ትብብር የሚደነቅ ነው።​—⁠ሮሜ 15:1, 2

12 ‘በመልካም ሥራ መጽናታችሁን’ ቀጥሉ፦ ለአንድ ወይም ከዚያ ለሚበልጡ ወራት ረዳት አቅኚ ሆነው ያገለገሉ ብዙዎች በቀጣዮቹ ወራትም የመስክ አገልግሎት እንቅስቃሴያቸው ከፍ እንዳለ ተገንዝበዋል። ተመልሰው እንዲያነጋግሯቸው የሚፈልጉ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች አግኝተዋል። ይህም ፍላጎት ያሳዩትን ሰዎች እንደገና ለማነጋገር አዘውትረው ወደ መስክ ለመውጣት ጥረት እንዲያደርጉ ገፋፍቷቸዋል። አንዳንዶች ጥናቶች ማግኘታቸው በአገልግሎቱ የበለጠ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ረድቷቸዋል።

13 ሌሎች ደግሞ በስብከቱና ደቀ መዝሙር በማድረጉ ሥራ የበለጠ ተሳትፎ ማድረጋቸው ከፍተኛ ደስታ ስላስገኘላቸው ቅድሚያ የሚሰጧቸውን ነገሮች ለመመርመር ተገፋፍተዋል። በውጤቱም አንዳንዶች በሰብዓዊ ሥራቸው ላይ የሚያሳልፉትን ሰዓት በመቀነስ ላልተወሰነ ጊዜ ረዳት አቅኚ ሆነው ለማገልገል ችለዋል። ሌሎች የዘወትር አቅኚ ሆነው ማገልገል ጀምረዋል። ተስፋቸውን ይህ ዓለም በሚያቀርባቸው ነገሮች ላይ ከማድረግ ይልቅ ሙሉ በሙሉ በአምላክ ላይ አድርገዋል። “ሊረዱና ሊያካፍሉም የተዘጋጁ” መሆናቸው የይሖዋን የተትረፈረፉ በረከቶች አስገኝቶላቸዋል እንዲሁም “እውነተኛውን ሕይወት” የማግኘት ተስፋቸውን አጠንክሮላቸዋል። (1 ጢ⁠ሞ. 6:18, 19) ብዙዎች በአቅኚነት አገልግሎት ሲካፈሉ መላው ጉባኤ እንደሚጠቀም የታወቀ ነው። አቅኚዎች ስለ አገልግሎታቸው ማውራታቸውና ሌሎችም ከእነሱ ጋር በአገልግሎቱ እንዲካፈሉ መጋበዛቸው አይቀርም፤ ይህም በጉባኤው ውስጥ መንፈሳዊ አመለካከት እንዲሰፍን ያደርጋል።

14 ሁላችንም በዚህ በመታሰቢያው ሰሞንና በቀጣዮቹ ወራት በክርስቲያናዊው አገልግሎት የምናደርገውን ተሳትፎ ከፍ በማድረግ “በበጎ ሥራ ባለ ጠጎች” እንሁን። እንዲህ በማድረግ ይሖዋ ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ምድር ለዘላለም የመኖር ተስፋ በመስጠት ላደረገልን ነገር አመስጋኞች መሆናችንን እናሳያለን።​—⁠2 ጴ⁠ጥ. 3:13

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ