‘ለሰው ሁሉ መልካም አድርጉ’
1 ‘የአምላክን ቃል በተሟላ ሁኔታ ስበኩ’ እና ‘በበጎ ሥራ ባለ ጠጎች ሁኑ’ የሚሉት ርዕሶች በየካቲትና መጋቢት 2002 የመንግሥት አገልግሎታችን አባሪዎች ላይ የወጡ ጭብጦች ነበሩ። (ቆላ. 1:25 NW ፤ 1 ጢሞ. 6:18) በእነዚህ ርዕሶች ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ ለመርዳት፣ አገልግሎት ያቆሙት በድጋሚ በጉባኤ ውስጥ ተሳትፎ ማድረግ እንዲጀምሩ እገዛ ለመስጠት እንዲሁም ልጆቻችንና ብቃቱ ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን የምሥራቹ አስፋፊ እንዲሆኑ ለመርዳት ልዩ ጥረት እንድናደርግ ተበረታተን ነበር። ባደረግነው ትጋት የተሞላበት ጥረት መልካም ውጤት እንዳገኘን አያጠራጥርም። አሁንም ቢሆን “ጊዜ ካገኘን ዘንድ ለሰው ሁሉ . . . መልካም” ማድረጋችንን እንቀጥል።—ገላ. 6:10
2 በድጋሚ በስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ ጋብዟቸው፦ በክልላችን ውስጥ ካሉት በየዓመቱ በመታሰቢያው በዓል ላይ ከሚገኙት ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የምሥራቹ አስፋፊዎች አይደሉም። በበዓሉ ላይ መገኘታቸው ራሱ በተወሰነ ደረጃ ፍላጎት እንዳላቸው የሚያሳይ ስለሆነ እነዚህን ‘ለዘላለም ሕይወት የተዘጋጁ’ ሰዎች ‘አማኞች’ እንዲሆኑ ለማበረታታት ምን ማድረግ አለብን? (ሥራ 13:48) ሳትውሉ ሳታድሩ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ አበረታቷቸው።
3 አንድን ፍላጎት ያሳየ ሰው በጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት ላይ ተገኝቶ መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? በተባለው መጽሐፍ ላይ በሚደረገው አስደሳች ውይይት እንዲካፈል ለምን አትጋብዘውም? ከግለሰቡ ጋር ዝምድና ወይም የቅርብ ትውውቅ ካላችሁና በሚቀጥሉት ሳምንታት በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የምታቀርበው ክፍል ካለህ በስብሰባው ላይ ተገኝቶ ክፍልህን እንዲሰማ ልትጋብዘው ትችላለህ። በቀጣዮቹ ሳምንታት የሚሰጡትን የሕዝብ ንግግር ርዕሶች ንገረው። (የሚሰጡት የሕዝብ ንግግሮች ፕሮግራም በየጊዜው በማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ መለጠፍ አለበት።) በግለሰቡ ልብ ውስጥ ይሖዋን የማምለክ ፍላጎት ለመቀስቀስ የሚያስችሉህን አጋጣሚዎች ፈልግ። እንዲሁም ጉባኤው ውስጥ ካለ ሌላ ሰው ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ካልጀመረ ካንተ ጋር እንዲያጠና በደግነት ልትጋብዘው ትችላለህ።
4 አገልግሎት ያቆሙትን ማበረታታት ቀጥሉ፦ በመታሰቢያው በዓል ላይ ከሚገኙት ውስጥ በርካታዎቹ ከዚህ ቀደም ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ ናቸው። ይሁን እንጂ በሆነ ወቅት ላይ አዘውትረው ምሥራቹን መስበክ አቁመዋል። ቢሆንም ጳውሎስ “በተለይም ለእምነት ቤተ ሰቦች መልካም እናድርግ” በማለት አጥብቆ አሳስቦናል። (ገላ. 6:10 አ.መ.ት ) ስለዚህ አገልግሎት ላቆሙት በዋነኛነት ትኩረት ልንሰጣቸው ይገባል።
5 ምናልባት አንዳንዶች በድጋሚ በአገልግሎት እንዲካፈሉ ከሽማግሌዎችና ከሌሎች ለተሰጣቸው ማበረታቻ አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተው ሊሆን ይችላል። በድጋሚ በአገልግሎት መካፈል ከጀመረ አስፋፊ ጋር አብረህ እንድታገለግል በሽማግሌዎች ተመድበህ ከሆነ ለይሖዋና ለመስክ አገልግሎት ያለህ ፍቅር ልበ ሙሉነትን እንዲያዳብር እንደሚረዳው አትዘንጋ። በአገልግሎት ደስታ ማግኘት፣ በስብከቱ ሥራ መጽናትና ይሖዋ የሚሰጠውን በረከት መቅመስ እንዲችል በተለያዩ የአገልግሎቱ ዘርፎች እንዴት እንደምትካፈል አሳየው።
6 አዳዲስ አስፋፊዎች ጥሩ ጅምር እንዲኖራቸው አድርጉ፦ ፍላጎት ያሳየች አንዲት ሴት እውነተኛውን የአምላክ ድርጅት እንዳገኘች ስትገነዘብ ወዲያውኑ አገልግሎት ለመጀመር ፈለገች። አገልግሎት ለመጀመር ምን ማድረግ እንደሚፈለግባት ካወቀች በኋላ “ጊዜ ሳናጠፋ አሁኑኑ እንጀምር” አለች። መጽሐፍ ቅዱስን የምታስጠኑት ሰው በአገልግሎት መካፈል እንዲጀምር ከተፈቀደለት ‘ጊዜ ሳያጠፋ መጀመር’ አስፈላጊ መሆኑን እንዲገነዘብ በመርዳት ጥሩ ጅምር እንዲኖረው አድርጉት። በየሳምንቱ ለመስክ አገልግሎት የመዘጋጀትና አዘውትሮ የመካፈል ልማድ እንዲያዳብር እርዱት።
7 አዲስ ያልተጠመቀ አስፋፊ የሆነው ልጃችሁ ከሆነ ከዕድሜውና ከችሎታው ጋር የሚመጣጠን እድገት እንዲያደርግ አብራችሁት በአገልግሎት ተካፈሉ። ከእናንተ በሚያገኘው መጠነኛ እገዛ ውጤታማ በሆነ ሁኔታ ከሰዎች ጋር ውይይት በመክፈት፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በማንበብና ጽሑፍ በማበርከት ያልጠበቃችሁት እንቅስቃሴ ሊያደርግ ይችላል። በመስክ አገልግሎት ላይ ፍላጎት ያለው ሰው ሲያገኝ ተመላልሶ መጠየቅ እንዲያደርግና የግለሰቡን ፍላጎት ተከታትሎ ማሳደግ እንዲችል አሠልጥኑት።
8 የራሳችሁንም የአገልግሎት እንቅስቃሴ አስፉ፦ ከመታሰቢያው በዓል በኋላም በወንጌላዊነቱ ሥራ ያለህን ተሳትፎ ለማሳደግ ሁኔታዎችህ ይፈቅዱልሃል? በአብዛኛው በየሳምንቱ በአገልግሎት በምታሳልፈው ጊዜ ላይ አንድ ወይም ሁለት ሰዓት መጨመር ትችላለህ? በድጋሚ በረዳት አቅኚነት የምታገለግልበትን ጊዜ ለመወሰን ቀደም ብለህ የቀን መቁጠሪያ በመመልከት እቅድ ታወጣለህ? ወይም ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመግባት በአኗኗርህ ላይ አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረግ ትችላለህ? ከአገልግሎቱ ጋር በተያያዘ የምናደርገው ማንኛውም ጥረት አንድ ሰው እውነትን እንዲቀበል ሊረዳው ይችላል! (ሥራ 8:26-39) ከፊታችን ያሉትን ቀናት በጉጉት እየተጠባበቅን ‘እርስ በርሳችንም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ሁልጊዜ መልካም የሆነውን ነገር ለማድረግ እንጣር።’—1 ተሰ. 5:15 አ.መ.ት
[ገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
እነዚህን መርዳታችሁን ቀጥሉ፦
□✔ በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኙትን
□✔ በድጋሚ በአገልግሎት መካፈል የጀመሩ አስፋፊዎችን
□✔ ያልተጠመቁ አዲስ አስፋፊዎችን