የሰዎችን ፍላጎት ለመቀስቀስ ወቅታዊ ሁኔታዎችን ተጠቀሙ
1 አገልግሎትህ አስደሳችና የሰዎችን ፍላጎት የሚቀሰቅስ እንዲሆን የሚረዳ ጥሩ ጥሩ ሐሳብ ዘወትር ማግኘት ትፈልጋለህ? እንግዲያው በዓለም ላይና በአካባቢህ የተከሰቱ ሁኔታዎችን ውይይት ለመጀመር ተጠቀምባቸው። በአካባቢህና በአገር ውስጥ በቅርብ የተከሰቱ ሁኔታዎችን ወይም ዓለም አቀፋዊ ዜናዎችን መጥቀስ ትችላለህ። የዓለም ሁኔታዎች በየጊዜው ይለዋወጣሉ። (1 ቆሮ. 7:31) የሚከተሉትን ምሳሌዎች ተመልከት።
2 የኢኮኖሚ ችግሮችና የኑሮ ውድነት ሰዎችን በጣም ያሳስባቸዋል። ስለዚህ እንዲህ ማለት ትችላለህ:-
◼ “[አንድ ነገር ጥቀስና] የዚህ ነገር ዋጋ እንደገና እንደጨመረ የሚገልጸውን ዜና ሰምተዋል?” ወይም ስለ ሥራ አጥነት ማንሳት ትችላለህ። ውይይቱ በየት አቅጣጫ እንዲቀጥል እንደምትፈልግ ግምት ውስጥ በማስገባት “ኑሮ በጣም እየከበደ የመጣው ለምንድን ነው ብለው ጠይቀው ያውቃሉ?” ወይም “ኑሮ እንዲህ ማጣፊያው እንዳጠረ ለሁልጊዜ ይቀጥላል ብለው ያስባሉ?” ብለህ መጠየቅ ትችላለህ።
3 በቤተሰብ ውስጥ ወይም በትምህርት ቤት እንደተፈጸመ የሚገልጽ ወንጀል ነክ ዜና ውይይት ለመጀመር አማራጭ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ብለህ መጠየቅ ትችላለህ:-
◼ “[በአካባቢው የተፈጸመ አንድ አሳዛኝ ሁኔታ ከጠቀስክ በኋላ] በጋዜጣ ላይ የወጣውን ስለዚህ ጉዳይ የሚገልጽ ዜና አንብበዋል?” ከዚያም “በዓለም ውስጥ ለዓመፅ መስፋፋት መንስኤው ምንድን ነው ብለው ያስባሉ?” ወይም “ወደፊት ያለ ስጋት መኖር የምንችልበት ጊዜ ይመጣል ብለው ያስባሉ?” ብለህ መጠየቅ ትችላለህ።
4 ስለ አውዳሚ የውኃ መጥለቅለቅ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ ወይም በተለያዩ የምድር ክፍሎች ስለሚቀሰቀሰው ሕዝባዊ ዓመፅ የሚነገረው ዜና የሰዎችን ፍላጎት የሚቀሰቅስ ጥሩ መግቢያ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል እንዲህ ብለህ መጠየቅ ትችላለህ:-
◼ “[አንድን የተፈጥሮ አደጋ ከጠቀስክ በኋላ] ይህን የተፈጥሮ አደጋ ያመጣው አምላክ ነውን?” ወይም ደግሞ በቅርብ የተቀሰቀሰን አንድ ሕዝባዊ ዓመፅ ጠቅሰህ “ሰው ሁሉ ሰላምን የሚሻ ከሆነ ሰላምን ማስፈን ያልተቻለው ለምንድን ነው?” ብለህ መጠየቅ ትችላለህ።
5 በመግቢያ ላይ ልትጠቀምባቸው የምትችላቸውን ወቅታዊ የዓለም ሁኔታዎች በንቃት ተከታተል። ማመራመር በተባለው መጽሐፍ ከገጽ 10-11 ላይ “ወቅታዊ የዓለም ሁኔታዎች” በሚለው ርዕስ ሥር ጠቃሚ ሐሳቦች ሰፍረዋል። ይሁን እንጂ በፖለቲካዊም ሆነ በማኅበራዊ ጉዳዮች ረገድ ወገን እንዳትይዝ ተጠንቀቅ። ከዚህ ይልቅ ለሰው ልጅ ችግሮች ብቸኛው ዘላቂ መፍትሔ ቅዱሳን ጽሑፎችና የአምላክ መንግሥት እንደሆነ እንዲገነዘቡ እርዳቸው።