እርስ በርስ ለመበረታታት የሚያስችል ልዩ አጋጣሚ
1 የይሖዋ ሕዝቦች እምነታቸው ሳይፈተን የሚውሉበት አንድም ቀን የለም ለማለት ይቻላል። ዲያብሎስ የቀረው ጊዜ አጭር እንደሆነ ስለሚያውቅ ለይሖዋ ታማኝ እንዳንሆን ለማድረግ ባለ በሌለ ኃይሉ ጥቃት በመሰንዘር ላይ ነው። (ራእይ 12:12) ‘በክፉው ቀን ለመቃወምና ሁሉንም ፈጽመን ለመቆም እንድንችል በጌታና በኃይሉ ችሎት እየበረታን’ መሄዳችን በጣም አስፈላጊ ነው።—ኤፌ. 6:10, 13
2 ይሖዋ እኛን ለማበርታት ከእምነት አጋሮቻችን ጋር አብረን መሰብሰብ እንድንችል ዝግጅት አድርጎልናል። ሐዋርያው ጳውሎስ የዚህን ዝግጅት ጠቀሜታ ተገንዝቦ ነበር። ‘እርስ በእርሳቸው መበረታታትና መጽናት’ እንዲችሉ ከክርስቲያን ወንድሞቹ ጋር አንድ ላይ የሚሆንበትን አጋጣሚ ይናፍቅ ነበር። (ሮሜ 1:11, 12 አ.መ.ት ) የአስተዳደር አካል የአምላክን ፈቃድ በመፈጸም ረገድ እንድንጠናከር ለማድረግ በቅርቡ በሚደረገው “ቀናተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች” የአውራጃ ስብሰባ ላይ እርስ በእርስ መበረታታት የምንችልበትን ፍቅራዊ ዝግጅት አድርጎልናል።
3 ከዝግጅቱ ተጠቃሚ ለመሆን በስብሰባው ላይ ተገኙ፦ በሦስቱም ቀን ለመገኘት ግብ አውጡ። የመጀመሪያው መዝሙር ከመዘመሩ በፊት በመድረስና እስከ መደምደሚያው ጸሎት ድረስ እዚያው በመቆየት ራሳችንን ልንጠቅም እንችላለን። (ኢሳ. 48:17, 18 NW ) ብዙዎች ሦስቱንም ቀን በስብሰባው ላይ መገኘት እንዲችሉ ቀደም ብለው የሥራ ፕሮግራማቸውን ማስተካከል ያስፈልጋቸው ይሆናል። እርግጥ ነው፣ የሥራ ፈቃድ ማግኘት ቀላል ላይሆን ይችላል፤ ቢሆንም ይሖዋ ፈቃዱን እንድናደርግ እንደሚረዳን ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (1 ዮሐ. 5:14, 15) እስካሁን እንዲህ አላደረጋችሁ ከሆነ ‘ጊዜው ሲደርስ ሁሉ ይስተካከላል’ በሚል ሳትዘናጉ ከሥራ ፈቃድ ማግኘትን መጓጓዣንና ማረፊያ ቦታን በተመለከተ ከአሁኑ ሁኔታዎችን አመቻቹ። በስብሰባው ላይ ሦስቱንም ቀን ለመገኘት የምናደርገውን ጥረት ይሖዋ እንደሚባርክልን ልንተማመን እንችላለን።—ምሳሌ 10:22
4 የምታገኙትን ማበረታቻ በጉጉት ተጠባበቁ፦ ከአውራጃ ስብሰባ ስትመለሱ “የዘንድሮው ደግሞ ልዩ ነበር!” ያላችሁበትን ጊዜ ታስታውሳላችሁ? እንዲህ እንዲሰማችሁ ያደረገው ነገር ምን ሊሆን ይችላል? ፍጹማን ያልሆንን ሰዎች በመሆናችን ምክንያት ቀስ በቀስ እየደከምን ስለምንሄድና መንፈሳዊ ማበረታቻ ስለሚያስፈልገን ነው። (ኢሳ. 40:30) አንዲት እህት እንዲህ ብላለች:- “ይህ ሥርዓት እንድዝል ሲያደርገኝ የአውራጃ ስብሰባዎች ደግሞ የሚያስፈልገኝን መንፈሳዊ ብርታት በመስጠት ዳግመኛ ትኩረቴን በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ እንዳነጣጥር ይረዱኛል። ማበረታቻውን የማገኘው በጣም በሚያስፈልገኝ ሰዓት ላይ ነው።” እናንተም እንደዚህ ሳይሰማችሁ አይቀርም።
5 የሚያስፈልገንን ማበረታቻ የምናገኘው በንግግሮችና በቃለ ምልልሶች ብቻ ሳይሆን የስብሰባዎቻችን ጉልህ ገጽታዎች በሆኑት በሌሎች ፕሮግራሞችም ጭምር ነው። አንድ ወንድም እንዲህ ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል:- “የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ እንዴት እንደሚውሉ ግልጽና ተግባራዊ ትምህርት የሚሰጥበት በመሆኑ ያስደስተኛል። በመልካምም ሆነ በመጥፎ ሥራቸው ከሚታወሱት የጥንት ምሳሌዎች ትምህርት በማስጨበጥ ረገድ ድራማዎች የሚሰጡት እርዳታ ወደር የለውም። ሁልጊዜ በስብሰባው ላይ የሚወጡትን አዳዲስ ጽሑፎች በጉጉት የምጠባበቅ ሲሆን እቤት ከተመለስኩ ከረጅም ጊዜ በኋላም ደስታ ይሰጡኛል።”
6 የአውራጃ ስብሰባዎች በዚህ “የሚያስጨንቅ ዘመን” ከይሖዋ ያገኘናቸው በጣም ጠቃሚ የሆኑ ዝግጅቶች ናቸው። (2 ጢሞ. 3:1) “ንቁ፣ በሃይማኖት ቁሙ፣ ጐልምሱ ጠንክሩ” የሚለውን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ምክር በሥራ ላይ እንድናውል ይረዱናል። (1 ቆሮ. 16:13) እንግዲያው አንዱም ክፍል ሳያመልጠን “ቀናተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች” በተሰኘው የአውራጃ ስብሰባችን ላይ በመገኘት እርስ በእርስ ለመበረታታት ቁርጥ ያለ ውሳኔ እናድርግ!
[ገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በሦስቱም ቀን ፕሮግራም ላይ ለመገኘት አስቀድመህ እቅድ አውጣ
■ የሥራ ፈቃድ ጠይቅ
■ የት እንደምታርፍ ዝግጅት አድርግ
■ ለመጓጓዣ የሚሆንህን ወጪ አዘጋጅ