‘እናንተ ቅዱሳኑ ሁሉ፣ ይሖዋን ውደዱት’
የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ ሚያዝያ 4 ይከበራል
1 ከበርካታ ዓመታት በፊት ዩክሬይን በኮሚኒስት አገዛዝ ሥር እያለች የመንግሥት ባለ ሥልጣናት የይሖዋ ምሥክሮች የሚሰበሰቡበትን ቦታ ለማግኘት ወንድሞችን በዓይነ ቁራኛ ይከታተሉ የነበረ ሲሆን በተለይ ደግሞ የጌታ እራት የሚከበርበት ቀን ሲቃረብ በተጠናከረ መልክ ክትትላቸውን ያካሂዱ ነበር። ባለ ሥልጣናቱ በዓሉ የሚከበርበት ወቅት መቃረቡን ስለሚያውቁ ወንድሞች የጌታ እራት በደረሰ ቁጥር ይቸገራሉ። ታዲያ ምን ማድረግ ይችላሉ? የአንዲት እህት ምድር ቤት በውኃ የተጥለቀለቀ ነበር። ባለ ሥልጣናቱ የይሖዋ ምሥክሮች እዚያ ውስጥ ይሰበሰባሉ የሚል ግምት ስላልነበራቸው ወንድሞች እስከ ጉልበታቸው ከሚደርሰው ውኃ በላይ ከሳንቃ ወለል ሠሩ። አጭር ኮርኒስ ባለው ክፍል ውስጥ ሳንቃው ላይ ተኮራምተው መቀመጥ ግድ ቢሆንባቸውም ማንም ሳይረብሻቸው የመታሰቢያውን በዓል በደስታ ማክበር ችለዋል።
2 በዩክሬይን የሚኖሩ ወንድሞቻችን የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ እንድናከብር የተሰጠንን ትእዛዝ ለመፈጸም ያደረጉት ጥረት ለአምላክ ምን ያህል ፍቅር እንዳላቸው ያሳያል። (ሉቃስ 22:19፤ 1 ዮሐ. 5:3) በበዓሉ ላይ እንዳንገኝ እንቅፋት የሚሆኑብን ነገሮች ካሉ እነዚህን ከመሳሰሉ ምሳሌዎች ትምህርት በመውሰድ ሚያዝያ 4 በሚከበረው የጌታ እራት ላይ ለመገኘት ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይገባናል። እንዲህ ካደረግን መዝሙራዊው “እናንተ ቅዱሳኑ ሁሉ፣ [“ይሖዋን፣”NW ] ውደዱት” ብሎ በዘመረ ጊዜ የገለጸውን ስሜት እንደምንጋራ እናሳያለን።—መዝ. 31:23
3 ሌሎች ለአምላክ ፍቅር እንዲያዳብሩ እርዷቸው:- ለአምላክ ያለን ፍቅር ሌሎች ሰዎች በዓሉን ከእኛ ጋር እንዲያከብሩ እንድንጋብዛቸውም ያነሳሳናል። በየካቲት የመንግሥት አገልግሎታችን አባሪ ላይ በበዓሉ ላይ እንዲገኙ ለመጋበዝ ያሰብናቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር እንድንጽፍ ማበረታቻ ተሰጥቶናል። ማስታወሻህ ላይ የጻፍካቸውን ሰዎች ሁሉ ለመጋበዝ በትጋት ጥረት እያደረግህ ነው? በዓሉ ለእነርሱ ምን ትርጉም እንዳለው ጊዜ መድበህ አስረዳቸው። የመታሰቢያው በዓል የሚከበርበትን ቀንና ሰዓት በደግነት ማስታወስህ፣ አስፈላጊ ከሆነም ይዘሃቸው ልትሄድ እንደምትችል ማሳወቅህ ወደ ስብሰባው እንዲመጡ ሊያበረታታቸው ይችላል።
4 ጥሪያችንን አክብረው በበዓሉ ላይ ለተገኙት ሰዎች ሰላምታ ለመስጠትና እንግድነት እንዳይሰማቸው ለማድረግ ጣር። ይሖዋን እንዲወዱ መርዳት የምትችለው እንዴት ነው? ጥያቄዎች ካሏቸው ለመመለስ ዝግጁ ሁን። የሚቻል ከሆነም መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት እንዲጀምሩ ሐሳብ ልታቀርብላቸው ትችላለህ። በሳምንታዊ የጉባኤ ስብሰባዎቻችን ላይ እንዲገኙ ጋብዛቸው። በበዓሉ ላይ የተገኙትን ከጉባኤ የጠፉ ወንድሞችና እህቶች ለማነጋገር በተለይ ሽማግሌዎች ንቁ መሆን አለባቸው። እነዚህን ክርስቲያኖች ለመጠየቅ ቀጠሮ ሊይዙና ምናልባትም በመታሰቢያው ንግግር ላይ የቀረቡትን አንዳንድ ሐሳቦች በማብራራት ወደ ቀድሞ አቋማቸው እንዲመለሱ ሊያበረታቷቸው ይችላሉ።—ሮሜ 5:6-8
5 ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ማሳደግ:- ስጦታ ሆኖ በቀረበልን በቤዛው ላይ በጥልቅ ማሰላሰላችን ለይሖዋና ለልጁ ያለንን ፍቅር ያሳድግልናል። (2 ቆሮ. 5:14, 15) ለበርካታ ዓመታት በመታሰቢያው በዓል ላይ ስትገኝ የቆየች አንዲት እህት እንዲህ ብላለች:- “የመታሰቢያውን በዓል በጉጉት ነው የምንጠባበቀው። ለበዓሉ ያለን አድናቆት በየዓመቱ እየጨመረ ሄዷል። ከ20 ዓመታት በፊት በጣም የምወድደው አባቴ ሞቶ አስከሬኑን ቆሜ የተመለከትኩበትንና ለቤዛው ልባዊ አድናቆት ያሳደርኩበትን ጊዜ አልረሳውም። ከዚያ በፊት ስለ ቤዛው የነበረኝ ግንዛቤ ከጭንቅላት እውቀት ያለፈ አልነበረም። ከቤዛው ጋር የተያያዙትን ጥቅሶችና ትርጉማቸውን አሳምሬ አውቅ ነበር! ሆኖም አባቴን በሞት ከተነጠቅሁ በኋላ ቤዛው ሊያስገኝልኝ የሚችለውን ነገር ሳስብ ልቤ በደስታ ተሞላ።”—ዮሐ. 5:28, 29
6 በዚህ ዓመት የሚከበረው የመታሰቢያው በዓል እየተቃረበ ሲመጣ ለበዓሉ ልብህን ለማዘጋጀት ጥረት አድርግ። (2 ዜና 19:3) ቅዱሳን ጽሑፎችን በየዕለቱ መመርመር—2004 እና የ2004 የቀን መቁጠሪያ ላይ የወጡትን ከመታሰቢያው በዓል ጋር የተያያዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አንብበህ አሰላስልባቸው። አንዳንዶች ታላቅ ሰው ከተባለው መጽሐፍ ላይ ምዕራፍ 112-16ን በቤተሰብ ጥናታቸው ወቅት መሸፈኑን ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል። ሌሎች ደግሞ ታማኝና ልባም ባሪያ ያዘጋጃቸውን ለጥናት የሚረዱ ሌሎች ጽሑፎች ተጠቅመው ተጨማሪ ምርምር ያደርጋሉ። (ማቴ. 24:45-47) ሁላችንም ስጦታ ሆኖ ስለቀረበልን ቤዛ የሚሰማንን አመስጋኝነት በጸሎታችን መጥቀስ እንችላለን። (መዝ. 50:14, 23) በመታሰቢያው በዓል ሰሞን ይሖዋ ባሳየን ፍቅር ላይ ማሰላሰላችንን መቀጠላችንና ለእርሱ ያለንን ፍቅር በተለያዩ መንገዶች መግለጻችን ተገቢ ነው።—ማር. 12:30፤ 1 ዮሐ. 4:10