አዲሱን ብሮሹር ለማሰራጨት የሚደረግ ልዩ ዘመቻ
1 ብዙ ሰዎች በጊዜያችን በሚታዩት የዓለም ሁኔታዎች ይረበሻሉ፤ ይሁን እንጂ ነገሮች እንዲህ የሆኑበትን ምክንያት፣ የወደፊቱ ጊዜ ምን እንደሚመስል እንዲሁም ከፊት ለፊታችን ካለው የፍርድ ቀን ለመትረፍ ምን ማድረግ እንዳለባቸው የተገነዘቡት በጣም ጥቂቶች ናቸው። (ሕዝ. 9:4) እነዚህ ሰዎች እንዲነቁና በጊዜያችን እየተፈጸሙ ያሉትን ነገሮች ትክክለኛ ትርጉም እንዲያስተውሉ ለመርዳት ነቅተህ ጠብቅ! የተባለውን ብሮሹር ከሰኞ ጥር 3 አንስቶ እስከ እሁድ ጥር 30 ድረስ በልዩ ዘመቻ እናሰራጫለን።
2 ብሮሹሩን ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል፣ ተመላልሶ መጠየቆችን ስናደርግ፣ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ምሥክርነት ስንሰጥ እንዲሁም ሰዎች በብዛት በሚገኙባቸው አካባቢዎች ማበርከት እንችላለን። ነገር ግን ነቅተህ ጠብቅ! የተሰኘውን ብሮሹር እንዲሁ ማደል አይኖርብንም። በዓለም ላይ የሚፈጸሙት ነገሮች ስላላቸው ትክክለኛ ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ሐሳብ ለመስማት ፍላጎት ላላቸው ሰዎች ብቻ ማበርከት ይኖርብናል። ለመልእክቱ እምብዛም አድናቆት ላላሳዩ ሰዎች ትራክት ልንሰጣቸው እንችላለን።
3 የሰዎችን ትኩረት ለመሳብ እንዲህ ልትል ትችላለህ:-
◼ “ብዙ ሰዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ የመጡትን አሳሳቢ ችግሮችና አስደንጋጭ የሆኑ ክስተቶችን ሲመለከቱ በጣም ያሳስባቸዋል። [አንድ በአካባቢው የሚታወቅ ጉዳይ ጥቀስ።] እነዚህ ነገሮች አስቀድመው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተነገሩ ያውቁ ኖሯል? [መልስ እስኪሰጥህ ጠብቀው። ከዚያም ካነሳኸው ጉዳይ ጋር የሚዛመድ ጥቅስ አንብብለት፤ እንደ ማቴዎስ 24:3, 7, 8፤ ሉቃስ 21:7, 10, 11 ወይም 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5 ያሉትን ጥቅሶች መጠቀም ትችላለህ።] መጽሐፍ ቅዱስ በጊዜያችን እየተፈጸሙ ያሉት ነገሮች ምን ትርጉም እንዳላቸውና የሰው ዘር ወደፊት ምን እንደሚጠብቀው ያብራራል። ስለዚህ ጉዳይ ይበልጥ ለማወቅ ይፈልጋሉ? [መልስ እስኪሰጥህ ጠብቀው። ልባዊ ፍላጎት ካሳየ ብሮሹሩን አበርክትለት።] ይህ ጽሑፍ ያለ ክፍያ የሚሰጥ ነው፤ ይሁንና ለምናከናውነው ዓለም አቀፋዊ የስብከት ሥራ አስተዋጽኦ ማድረግ ከፈለጉ ለመቀበል ፈቃደኞች ነን።”
4 ወይም እንዲህ ማለት ትችላለህ:-
◼ “በዛሬው ጊዜ ብዙዎች በራሳቸውም ሆነ በሌሎች ላይ በሚደርሱት አሳዛኝና አስደንጋጭ ሁኔታዎች በጣም ይጨነቃሉ። አንዳንዶች አምላክ እነዚህን ነገሮች ለማስወገድ ለምን ጣልቃ አይገባም ብለው ይጠይቃሉ። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በቅርቡ የሰው ልጆችን ሰቆቃ ለማስወገድ እርምጃ እንደሚወስድ ዋስትና ይሰጠናል። አምላክ ለሰው ልጆች የሚያመጣውን በረከት እዚህ ላይ ይመልከቱ። [መዝሙር 37:10, 11ን አንብብ።] ስለዚህ ጉዳይ ይበልጥ ማወቅ ይፈልጋሉ?” ከዚያም ከላይ በተጠቀሰው መንገድ መደምደም ትችላለህ።
5 ብሮሹሩን ያበረከትክላቸውን ሰዎች ስምና አድራሻ መዝግበህ በመያዝ ተመልሰህ ሄደህ ፍላጎታቸውን ለመኮትኮት ፕሮግራም አውጣ። ፍላጎታቸውን ማሳደግ የሚቻልባቸውን መንገዶች በተመለከተ በጥር 2005 የመንግሥት አገልግሎታችን እትም ላይ የሚወጡ ሐሳቦች ይኖራሉ። በመጀመሪያ ውይይታችን ግለሰቡ ጥሩ ፍላጎት ካሳየ ነቅተህ ጠብቅ! የተባለውን ብሮሹር አሊያም አምላክ ከእኛ የሚፈልገው እንደሚሉት ያሉ ሌሎች ጽሑፎችን ተጠቅሞ ወዲያውኑ ጥናት ማስጀመር ይቻላል።
6 ይህ ርዕስ በአገልግሎት ስብሰባ ላይ ከተጠና በኋላ ብሮሹሩን ማግኘት ይቻላል። በዘመቻው የመጀመሪያ ቀናት አቅኚዎችም ሆናችሁ አስፋፊዎች ልታሰራጩት የምትችሉትን መጠን ብቻ እንድትወስዱ ልናሳስባችሁ እንወዳለን። ይሖዋ እርሱ የሚወደስበትንና በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ ልበ ቅን ሰዎች የሚጠቀሙበትን ይህን ልዩ እንቅስቃሴ እንዲባርከው እንመኛለን።—መዝ. 90:17