ስለ ፍቅራዊ ደግነቱ ይሖዋን እናመስግነው
የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል መጋቢት 24, 2005 ይከበራል
1. ይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት ያሳየን እንዴት ነው?
1 መዝሙራዊው በአድናቆት ስሜት ተገፋፍቶ “እግዚአብሔርን ስለ ምሕረቱ [“ስለ ፍቅራዊ ደግነቱ፣”NW]፣ ለሰው ልጆችም ስላደረገው ድንቅ ሥራ ያመስግኑት” ብሎ ነበር። (መዝ. 107:8) የይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት ለሕዝቦቹ ከሚያሳየው የፍቅር እንዲሁም የአዘኔታ ስሜት የበለጠ ነገርን ይጨምራል። “እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህ [“ፍቅራዊ ደግነትህ፣” NW] ደግፎ ያዘኝ” ከሚሉት በመንፈስ አነሳሽነት ከተጻፉት የውዳሴ ቃላት ይህን እውነታ በግልጽ መረዳት ይቻላል። (መዝ. 94:18) ይሖዋ አንድያ ልጁን ለእኛ ሲል መስጠቱ አቻ የማይገኝለት የፍቅራዊ ደግነት መግለጫ ነው።—1 ዮሐ. 4:9, 10
2. ለይሖዋ አመስጋኝነታችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
2 የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ሲቃረብ “የፍቅራዊ ደግነት አምላክ” ለሆነው ለይሖዋ ያለንን አመስጋኝነት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? (መዝ. 59:17 NW) እያንዳንዳችን ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ የመጨረሻ ቀናት ላይ ስላደረጋቸው ነገሮች ለማሰላሰል ጊዜ መመደብ እንፈልጋለን። (መዝ. 143:5) በበዓሉ ሰሞን ቅዱሳን ጽሑፎችን በየዕለቱ መመርመር—2005 በተባለው ቡክሌት ላይ በወጣው ልዩ ፕሮግራም መሠረት መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባችን ጠቃሚ ነው። እንዲሁም እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው ከተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 112-116ን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከተመሠረቱ ሌሎች ጽሑፎች ጋር እያመሳከርን ማንበብና ተጨማሪ ምርምር ማድረግ እንችላለን። ባነበባችሁት ሐሳብ ላይ በጥሞና አስቡ እንዲሁም አሰላስሉ። (1 ጢሞ. 4:15) ጸሎት የታከለበት እንዲህ ዓይነቱ ጥናት ልባችንን ከመመገብ አልፎ ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ያንጸባርቃል።—ማቴ. 22:37
3, 4. (ሀ) በላይቤሪያ የሚኖሩ ወንድሞች ያሳዩትን መንፈስ እንዴት መኮረጅ እንችላለን? (ለ) በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ እነማንን ለመጋበዝ አስበሃል?
3 ሌሎች ይሖዋን እንዲያመሰግኑ ማነሳሳት:- ባለፈው ዓመት በዓለም ዙሪያ 16,760,607 የሚያክሉ ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ ተገኝተው ነበር። በላይቤሪያ በምትገኝ አንዲት መንደር ውስጥ የሚኖሩ ወንድሞች ለከተማው ኃላፊ የጌታ እራትን እርሳቸው በሚኖሩበት ከተማ ውስጥ ማክበር እንደሚፈልጉ የሚገልጽ ደብዳቤ ጻፉ። ኃላፊው በከተማው በሚገኝ የእግር ኳስ ሜዳ ላይ እንዲሰበሰቡ ፈቃድ ከመስጠታቸውም በላይ በአካባቢው ያሉ ሰዎች ሁሉ በዝግጅቱ ላይ መጋበዛቸውን የሚገልጽ ማስታወቂያ እንዲነገር አደረጉ። በመንደሩ ውስጥ አምስት አስፋፊዎች ብቻ የነበሩ ቢሆንም በመታሰቢያው በዓል ላይ 636 ተሰብሳቢዎች ተገኝተዋል!
4 እኛም ብንሆን የመታሰቢያውን በዓል በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች አብረውን እንዲያከብሩ እንፈልጋለን። ለመጋበዝ ያሰብካቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር በማስታወሻህ ላይ ለምን አታሰፍርም? ሰዎችን ለመጋበዝ በመጋቢት 15, 2005 መጠበቂያ ግንብ መጨረሻ ገጽ ላይ ያለውን ሐሳብ መጠቀም ትፈልግ ይሆናል። እንዲሁም የመታሰቢያውን በዓል የመጋበዣ ወረቀት መጠቀም የምትችል ሲሆን በዓሉ የሚከበርበትን ሰዓትና ቦታ በታይፕ ወይም በግልጽ በሚነበብ ጽሑፍ ካሰፈርክ በኋላ ለጋበዝካቸው ሰዎች መስጠት ትችላለህ። በዓሉ የሚከበርበት ቀን ማለትም መጋቢት 24 ሲቃረብ የጋበዝካቸውን ሰዎች ስልክ ደውለህ አስታውሳቸው፤ እንዲሁም በዚያው ሌሎች ዝግጅቶችንም አጠናቅቅ።
5. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን በዓሉ ላይ እንዲገኙ እንዴት ማበረታታት እንችላለን?
5 በስብሰባዎች ላይ መገኘት ያልጀመሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ካሉን ከመታሰቢያው በዓል ሙሉ በሙሉ እንዲጠቀሙ እንዴት ልንረዳቸው እንችላለን? በዓሉን ማክበር ምን ጠቀሜታ እንዳለው መረዳት እንዲችሉ ለማድረግ ጥቂት ደቂቃዎችን በእያንዳንዱ የጥናት ክፍለ ጊዜ መድብ። በመጋቢት 15, 2004 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 3-7 እንዲሁም በማመራመር መጽሐፍ ገጽ 265-269 ላይ ጠቃሚ ሐሳቦችን ማግኘት ትችላለህ።
6. ወደ መታሰቢያው በዓል የሚመጡ እንግዶችን በደስታ መቀበላችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
6 እንግዶችን በደስታ ተቀበሉ:- በመታሰቢያው በዓል ላይ እንግዶችን ቀርበን እንኳን ደህና መጣችሁ ልንላቸው ይገባል። (ሮሜ 12:13) የጋበዛችኋቸው ሰዎች አብረዋችሁ እንዲቀመጡ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስና የመዝሙር መጽሐፍ ማግኘት እንዲችሉ ዝግጅት አድርጉ። በተለይ ደግሞ የቀዘቀዙ ወንድሞችና እህቶች ከመጡ ቅድሚያውን ወስደን ሞቅ ያለ ሰላምታ ብንሰጣቸው ጥሩ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ፍቅራዊ አሳቢነት እንደ ቀድሞው አዘውትረው ጉባኤ መገኘት እንዲጀምሩ ያበረታታቸው ይሆናል። (ሉቃስ 15:3-7) እጅግ ቅዱስ በሆነው በዚህ በዓል ላይ ሌሎች ሰዎች አብረውን በመሆን “የሚያስደንቅ ፍቅራዊ ደግነት” ያሳየንን ይሖዋን እንዲያመሰግኑ ሁላችንም የቻልነውን እናድርግ።—መዝ. 31:21 NW