ምሥራቹን በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች መስበክ
1. የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ምሥራቹን በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች ለማዳረስ ምን ያከናወኑት ነገር አለ?
1 የጥንቶቹ የኢየሱስ ተከታዮች የመንግሥቱን መልእክት ለማዳረስ ልባዊ ፍላጎት ነበራቸው። ምሥራቹን በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች ለመስበክ ውጤታማ ዘዴዎችን ተጠቅመዋል። ክርስቲያን ጸሐፊዎች ቅዱሳን ጽሑፎችን በመንፈስ ተነሳስተው የጻፉት በወቅቱ በሮም ግዛት ብሔራዊ ቋንቋ በነበረው ተራው ሕዝብ በሚግባባበት የግሪክኛ ቋንቋ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በሁለተኛውና በሦስተኛው ክፍለ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ቀናተኛ ሰባኪዎች በጥቅልል መልክ ከተዘጋጁት ቅዱሳን ጽሑፎች ይልቅ ለአጠቃቀም አመቺ የነበረውንና ጥቅሶችን በቀላሉ ፈልጎ ለማግኘት የሚያስችለውን በመጽሐፍ መልክ የቀረበውን የቅዱሳን ጽሑፎች ቅጂ (ኮዴክስ) ለማዘጋጀት የመጀመሪያዎቹ ሳይሆኑ አይቀሩም።
2, 3. (ሀ) ኢሳይያስ 60:16 በዛሬው ጊዜ ተፈጻሚነቱን ያገኘው እንዴት ነው? (ለ) ንጹሑን አምልኮ በማስፋፋት ረገድ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጥቅም ላይ የዋሉት እንዴት ነው?
2 በቴክኖሎጂ መጠቀም:- ይሖዋ በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል “የነገሥታትንም ጡት ትጠቢያለሽ” በማለት ትንቢት ተናግሯል። (ኢሳ. 60:16) በዚህ ትንቢት ዘመናዊ ፍጻሜ መሠረት የይሖዋ አገልጋዮች የስብከቱን ሥራ ለማስፋፋት መንግሥታት ባዘጋጁአቸው አንዳንድ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ይጠቀማሉ። ለምሳሌ ከድምፅ ጋር የተቀናበሩ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች በንግዱ ዓለም መታየት ከመጀመራቸው ከዓመታት በፊት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” የተባለውን ፊልም በ1914 ማሳየት ጀምረው ነበር። ይህ ስምንት ሰዓት የሚፈጅ የፎቶግራፍ ስላይድና ተንቀሳቃሽ ፊልም ባለ ቀለም እንዲሁም ከድምፅ ጋር የተቀናበረ ሲሆን በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ኃይለኛ መልእክት ያለው ምሥክርነት ሰጥቷል።
3 በዛሬው ጊዜ የአምላክ ሕዝቦች ከፍተኛ ፍጥነት ባላቸው ማተሚያዎችና በኮምፒውተር በሚታገዙ መሣሪያዎች በመጠቀም መጽሐፍ ቅዱሶችንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በመቶዎች በሚቆጠሩ ቋንቋዎች ማተም ችለዋል። እንዲሁም በፈጣን መጓጓዣዎች በመጠቀም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ወደ 235 አገሮችና ደሴቶች ማዳረስ ችለዋል። ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት አገልጋዮቹ እንዲህ ያሉትን የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንዲጠቀሙ ያነሳሳቸው ሲሆን ይህም በታሪክ ውስጥ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንዲደርሳቸው አድርጓል።
4. አንዳንዶች ምሥራቹን በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች ለመስበክ ሲሉ ምን ዓይነት ማስተካከያዎችን አድርገዋል?
4 በግለሰብ ደረጃ የተደረጉ ማስተካከያዎች:- ምሥራቹን በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች ለመስበክ እውነተኛ የይሖዋ አምላኪዎችም በግላቸው ማስተካከያዎችን እንዲያደርጉ ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል። ብዙዎች በስብከቱ ሥራ ይበልጥ ለመሥራት ሲሉ አኗኗራቸውን ቀላል አድርገዋል። አንዳንዶች የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ሄደዋል። ሌሎች ደግሞ የውጭ አገር ቋንቋ በመማር አገልግሎታቸውን ሊያሰፉ ችለዋል።
5, 6. በክልላችን ውስጥ ለሚገኙ ለብዙ ሰዎች ለመስበክ ምን ማድረግ እንችላለን?
5 በተጨማሪም ሰዎች ቤታቸው በሚኖሩበት ጊዜ እንዲሁም በሚገኙበት አካባቢ በመስበክ ምሥራቹን በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች ለማዳረስ እንችላለን። በክልልህ ውስጥ ያሉት ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ቀን ቀን የማይገኙ ከሆነ አመሻሹ ላይ ለመስበክ ፕሮግራምህን ማስተካከል ትችል ይሆን? ለመመሥከር የምትችልባቸው ሰዎች በብዛት የሚገኙባቸው ቦታዎች ይኖሩ ይሆን? በስልክና በንግድ አካባቢዎች ምሥክርነት ለመስጠት ሞክረሃል? መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመመሥከር አጋጣሚዎችን ትፈልጋለህ?
6 ስለ ይሖዋ ስምና ስለ መንግሥቱ በሚሰጠው ሰፊ ምሥክርነት በመካፈላችን ምንኛ ተባርከናል! በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ሕይወት ሰጪ እውነት ለብዙ ሰዎች መስበካችንን እንቀጥል።—ማቴ. 28:19, 20