አዲስ የወረዳ ስብሰባ ፕሮግራም
በዚህ ብልሹና አሮጌ ሥርዓት የመደምደሚያ ቀኖች ውስጥ ስንኖር መንፈሳዊ ልብሳችንን እንዲሁም ክርስቲያናዊ መለያችንን ጠብቀን መኖራችን በጣም አስፈላጊ ነው። (ራእይ 16:15) ስለሆነም የ2006 የአገልግሎት ዓመት የወረዳ ስብሰባ “አዲሱን ሰው ልበሱ” የሚል ጭብጥ ያለው መሆኑ ተገቢ ነው።—ቈላ. 3:10
የመጀመሪያው ቀን:- በስብሰባው ላይ ከሚቀርቡት ተከታታይ ንግግሮች መካከል የመጀመሪያው “የአዲሱን ሰው የተለያዩ ገጽታዎች ማንጸባረቅ” የሚል ጭብጥ ያለው ሲሆን አዲሱን ሰው መልበሳችን በሁሉም የኑሮ ዘርፎች እንዴት እንደሚጠቅመን ያጎላል። አዲሱን ሰው መልበስ የምንችለው እንዴት ነው? “በተገቢው ሁኔታ ለማሰላሰል ራሳችሁን ገሥጹ” እና “አዲሱን ሰው ለመቅረጽ የሚረዳ ትምህርት” በሚል ጭብጥ ከሚቀርቡት የዕለቱ የመደምደሚያ ንግግሮች የዚህን ጥያቄ መልስ እናገኛለን።
ሁለተኛው ቀን:- “የጠቢብ አንደበት ይኑራችሁ” የሚል ጭብጥ ባለው በሁለተኛው ተከታታይ ንግግር ላይ አዲሱን ሰው መልበሳችን በአንደበት አጠቃቀማችን ላይ ምን ተጽዕኖ እንደሚኖረው ይብራራል። የሕዝብ ንግግሩ ጭብጥ “ክፉውን እያሸነፋችሁት ነው?” የሚል ሲሆን በሰይጣን ዘዴዎች እንዳንታለል ነቅቶ የመኖርን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ይገልጻል። በስብሰባው ማጠቃለያ ላይ የሚቀርቡት ሁለት ንግግሮች “ከዓለም ርኩሰት ራሳችሁን ጠብቁ” እንዲሁም “ውስጣዊ ሰውነታችን በየዕለቱ ይታደስ” የሚል ጭብጥ ያላቸው ሲሆን የይሖዋን የጽድቅ መንገድ ከሚቃረን አመለካከትና አኗኗር በመራቅ እርሱን በማምለክ ጸንተን እንድንኖር ይረዱናል።
አዲሱን ሰው እንድንለብስና ጠብቀን እንድንኖር የሚሰጠንን እንዲህ ዓይነቱን ግሩም ማበረታቻ በጉጉት እንጠብቃለን!