ለተግባር የሚያነሳሳን ትምህርት ቤት
1 በ2006 በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ላይ የምንወስደውን ትምህርት በቅዱስ አገልግሎታችንና በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ተግባራዊ በማድረግ ከትምህርቱ ጥቅም ለማግኘት ብርቱ ጥረት እናደርጋለን። የምንማራቸውን ነገሮች በሥራ ላይ ለማዋል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።—ዮሐ. 13:17፤ ፊልጵ. 4:9
2 ሐሳብ መስጠት:- የዚህ ዓመት የትምህርት ቤት ፕሮግራም አድማጮች በመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ጎላ ያሉ ነጥቦች ላይ ሐሳባቸውን እንዲሰጡ የተመደበላቸው ጊዜ የአንድ ደቂቃ ጭማሪ እንደተደረገበት ይገልጻል። ይህም ሲባል ጎላ ያሉ ነጥቦችን የሚያቀርበው ወንድም ክፍሉን በስድስት ደቂቃ ሳይሆን በአምስት ደቂቃ ውስጥ ማጠናቀቅ ይኖርበታል ማለት ነው። ሐሳብ የሚሰጡ አድማጮችም ቢሆኑ የተመደበላቸውን ጊዜ ከግምት ውስጥ ማስገባት ይገባቸዋል። አንድ ሰው አስቀድሞ በጥንቃቄ ካሰበበት በ30 ሴኮንድ ወይም ከዚያ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ጠቃሚ ሐሳብ ማካፈል ይችላል። በመሆኑም አድማጮች እንዲሳተፉበት ታስቦ በተመደበው አምስት ደቂቃ ውስጥ አሥር የሚያህሉ ሰዎች ትርጉም ያለው ሐሳብ መስጠት ይችላሉ።
3 ትምህርት ሰጪ ንግግሮች:- የመጽሐፍ ቅዱስ ጎላ ያሉ ነጥቦችና የማስተማሪያ ንግግር እየቀረበ ያለው ትምህርት በአገልግሎት እንዲሁም በዕለት ተዕለት የሕይወት ዘርፎች እንዴት ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል የሚያሳዩ መሆን ይኖርባቸዋል። ተናጋሪው አድማጮቹን ለተግባር ማነሳሳቱ ብቻ በቂ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ምን ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው፣ ይህን እንዴት ማከናወን እንደሚችሉና ያን ማድረጋቸው የሚያስገኝላቸውን ጠቀሜታ ለይቶ መጥቀስ ይኖርበታል። ተናጋሪው “ይህ ጥቅስ በዚህ መልኩ ይህንን ዓይነት መመሪያ ይሰጠናል” አሊያም “በዚህ መንገድ ይህን ጥቅስ በአገልግሎታችን ልንጠቀምበት እንችላለን” ማለት ይችላል። የጉባኤያቸውን ሁኔታ ጠንቅቀው የሚያውቁ ሽማግሌዎችና አገልጋዮች ትምህርቱን ከነባራዊው ሁኔታ ጋር በሚስማማ መንገድ ተግባራዊ ጠቀሜታውን አጉልተው ለመጥቀስ የቻሉትን ያህል ይጥራሉ።
4 በተለይ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን መጠቀም ትምህርቱን እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል በጥሩ ሁኔታ ለማጉላት ያስችላል። ተናጋሪው አንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌ ከጠቀሰ በኋላ “እናንተም ከዚህ ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል ነገር ይገጥማችሁ ይሆናል” ለማለት ይችላል። ተናጋሪው የመጽሐፍ ቅዱስን ምሳሌ የሚጠቀምበት ዓላማ ከመላው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሁም “ታማኝና ልባም ባሪያ” ከሚያሳትማቸው ጽሑፎች ጋር የሚስማማ መሆን ይኖርበታል።—ማቴ. 24:45 የ1954 ትርጉም
5 ጥበብ እውቀትንና ማስተዋልን በተገቢው መንገድ በሥራ ላይ የማዋል ችሎታ ነው። “ጥበብ ታላቅ ነገር ናት።” (ምሳሌ 4:7) በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት በምናደርገው ጥናት አማካኝነት መልካም ጥበብ በቀሰምን መጠን ሌሎችን የማስተማር ክህሎታችንንም ለማሳደግ እንጣር።