አዲስ የልዩ ስብሰባ ቀን ፕሮግራም
የጥንት ክርስቲያኖች በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተው ምሥራቹን በስፋት ለማወጅ ብርቱ ጥረት ያደርጉ ነበር። (ሥራ 1:8፤ ቈላ. 1:23) በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ይህን የመሰለ ቅንዓት እያሳዩ ነው። በ2007 የአገልግሎት ዓመት የምናደርገው የልዩ ስብሰባ ቀን ፕሮግራም ጭብጥ “ለቃሉ የተጋችሁ ሁኑ” የሚል ሲሆን በግለሰብ ደረጃ ትጉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችና ቀናተኛ ሰባኪዎች እንድንሆን ያበረታታናል።—ሥራ 18:5
“ለሥራ ከመትጋት አትለግሙ” እንዲሁም “የእውነትን ቃል በትክክል መጠቀም” በሚል ርዕስ በስብሰባው መክፈቻ ላይ የሚቀርቡት ንግግሮች የስብከቱንና የማስተማሩን ሥራ በጥድፊያ ስሜት እንድናከናውን ይረዱናል። ጎብኚ ተናጋሪው የሚያቀርበው የመጀመሪያ ንግግር “ሁልጊዜ የአምላክ ቃል ባለው ኃይል ተጠቀሙ” የሚል ሲሆን ቅዱሳን መጻሕፍት ነገሮችን ‘በማቅናት’ ረገድ ያላቸውን ጠቀሜታ ያጎላል። (2 ጢሞ. 3:16, 17) በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በዕለት ተዕለት ሕይወታችን በሥራ ላይ በማዋል ከአደጋ መራቅና ራሳችንን መጥቀም የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያሳያል።
ወጣቶችንና አዲሶችን መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ ለመርዳት የአምላክን ቃል እንዴት መጠቀም እንችላለን? የመጠበቂያ ግንብ ፍሬ ሐሳብን ከሚያስጨብጠው ንግግር ቀጥለው የሚቀርቡት ሁለት ክፍሎች መልሱን ይሰጡናል። በስብሰባው ላይ የሚገኙ ሁሉ ቅዱሳን መጻሕፍት በሕይወታቸው ውስጥ በጎ ተጽዕኖ ካሳደሩባቸው ሰዎች ጋር በሚደረገው ቃለ ምልልስ ይበረታታሉ። በመጨረሻም ጎብኚ ተናጋሪው የሚያቀርበው የመደምደሚያ ንግግር ‘በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን የአምላክን ቃል “በትጋት” እንድንጠቀምበት’ ይረዳናል።
ይህ የልዩ ስብሰባ ቀን ፕሮግራም ለአምላክ ቃል ያለን አድናቆት እንዲጨምርና በቅንዓት ለመስበክ እንድንነሳሳ ያደርገናል። እንግዲያው ሁላችንም በዚያ ተገኝተን ከትምህርቱ ተጠቃሚ እንሁን!