መጠነኛ ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች በሙሉ ተመላልሶ መጠየቅ አድርጉላቸው
1 ዛሬ አብዛኞቻችን ወደ እውነት ልንመጣ የቻልነው አንድ ሰው ለመንግሥቱ መልእክት ጥሩ ምላሽ መስጠታችንን አስተውሎ ስላነጋገረንና ፍላጎታችንን ለማሳደግ ሲል ምናልባትም ለበርካታ ጊዜያት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ተመላልሶ ስለረዳን ሊሆን ይችላል። እኛም በተመሳሳይ መጠነኛ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን በሙሉ በትጋት ተመላልሰን ልንጠይቃቸው ይገባል። ‘ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ’ የተሰጠን ተልእኮ ተመላልሶ መጠየቅንም እንደሚጨምር እሙን ነው።—ማቴ. 28:19, 20
2 የሰዎችን ፍላጎት አስተውሉ:- አንድ ሰው ጽሑፍ ለመውሰድ ፈቃደኛ ባይሆንም እንኳ ፊቱ ላይ የሚነበበው ስሜት፣ የድምፁ ቃና ወይም የቃላት አመራረጡ ለመንግሥቱ መልእክት መጠነኛ አድናቆት እንዳለው የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም በዚህ ላይ ተመሥርተን ተመላልሶ መጠየቅ ልናደርግለት እንችላለን። አንድ ወንድም፣ ላነጋገረው ግለሰብ ምንም ጽሑፍ ሳያበረክትለት ለአምስት ተከታታይ ሳምንታት ተመላልሶ መጠየቅ አደረገለት። ይህ ሰው በስድስተኛው ተመላልሶ መጠየቅ ላይ ጽሑፎችን የወሰደ ከመሆኑም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመርም ተስማማ።
3 አንድ ሰው ፍላጎት እንዳለው ካስተዋልክ የተሟላ ማስታወሻ ያዝና ጥሩ ቦታ አስቀምጠው። ከዚያም ብዙ ጊዜ ሳታጠፋ ምናልባትም ከጥቂት ቀናት በኋላ ግለሰቡን ተመልሰህ አነጋግረው። በሰውዬው ልብ ውስጥ የተዘራውን ዘር “ክፉው” መጥቶ እንዲነጥቀው አጋጣሚ አትክፈትለት። (ማቴ. 13:19) ተመልሰህ ለመሄድ ቀጠሮ ከያዝክ ቃልህን ጠብቀህ በቀጠሮህ ተገኝ።—ማቴ. 5:37
4 ከመንገድ ወደ መንገድ:- ከመንገድ ወደ መንገድ ስታገለግል ወይም መደበኛ ባልሆነ መንገድ ስትመሠክር ያገኘኸውን ሰው ፍላጎት ለማሳደግ ጥረት ታደርጋለህ? በውይይታችሁ መደምደሚያ ላይ “በውይይታችን ተደስቻለሁ። ታዲያ እንደገና ለመነጋገር እንድንችል የት እንገናኝ?” ልትለው ትችላለህ። አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ አንዳንድ አስፋፊዎች እንደሚያደርጉት ፍላጎት ላሳየው ሰው ስልክ ቁጥራችንን ልንሰጠው አሊያም የስልክ ቁጥራችንን እንድንለዋወጥ ልንጠይቀው እንችላለን። ሰዎች በአንድ አካባቢ በተደጋጋሚ ጊዜ ከመንገድ ወደ መንገድ ስታገለግል ካዩህ የስልክ ቁጥራቸውን አሊያም የሚገኙበትን አድራሻ ለመስጠት ፈቃደኞች ሊሆኑ ይችላሉ። አድራሻቸውን ሊሰጡህ ፈቃደኛ ባይሆኑም እንኳ በሌላ ጊዜ በመንገድ ላይ ስታገኛቸው ፍላጎታቸውን ለማሳደግ ጥረት ማድረግ ትችላለህ።
5 ውኃ ስናጠጣቸውና ስንኮተኩታቸው የነበሩ አትክልቶች ሲያድጉ መመልከት ደስ ያሰኛል። በተመሳሳይም ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግና ሰዎችን በመንፈሳዊ እንዲያድጉ በመርዳት ታላቅ ደስታ ማግኘት እንችላለን። (1 ቆሮ. 3:6) መጠነኛ ፍላጎት ያሳዩትን ሁሉ ተመልሳችሁ የመጠየቅ ግብ ይኑራችሁ።