ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች ተመላልሶ መጠየቅ አድርጉ—መቼ?
1. ሰዎችን ደቀ መዛሙርት ማድረግ ምን ነገር ይጨምራል?
1 ሰዎችን ደቀ መዛሙርት ማድረግ፣ ይሖዋ በመንግሥቱ በኩል ስላደረጋቸው ዝግጅቶች ለመማር ፍላጎት ያሳየ ማንኛውንም ሰው ተመልሶ መጠየቅን ይጨምራል። (ማቴ. 28:19, 20) ተመላልሶ መጠየቅ የምናደርግበትን አመቺ ጊዜ ለመምረጥ አብዛኛውን ጊዜ የእኛንም ሆነ ፍላጎት ያሳየውን ሰው ፕሮግራም ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልገናል። ግለሰቡን መጀመሪያ ካነጋገርነው በኋላ ቶሎ ተመልሰን መጠየቅ ያለብን ለምንድን ነው?
2, 3. በተቻለን መጠን ቶሎ ተመልሰን ለመሄድ መጣር ያለብን ለምንድን ነው?
2 ቶሎ ተመልሰን መጠየቅ ያለብን ለምንድን ነው? ‘የመንግሥቱን ምሥራች’ የመስበኩ ሥራ የሚጠናቀቅበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፤ እንዲሁም የዚህ ሥርዓት መጨረሻ ቀርቧል። (ማቴ. 24:14፤ 1 ጴጥ. 4:7) በመሆኑም ፍላጎት ላላቸው ሰዎች የተሰጠው ‘የመዳን ቀን’ ከማብቃቱ በፊት ‘ቃሉን በጥድፊያ ስሜት እንድንሰብክ’ የተሰጠንን ማሳሰቢያ ተግባራዊ ለማድረግ መጣር አለብን፤ ይህ ደግሞ የሰዎቹን ፍላጎት ለማሳደግ በተቻለ መጠን ቶሎ ሄዶ መጠየቅን ይጨምራል።—2 ቆሮ. 6:1, 2፤ 2 ጢሞ. 4:2
3 ሰይጣን ፍላጎት ባሳየ ሰው ልብ ውስጥ የዘራነውን ማንኛውንም ዓይነት የመንግሥቱን ዘር ለመውሰድ ይፈልጋል። (ማር. 4:14, 15) አንድ ግለሰብ ፍላጎት ሲያሳይ ብዙውን ጊዜ የቤተሰቡ አባላት፣ የሥራ ባልደረቦቹና ሌሎች ሰዎች ሊያሾፉበት ይችላሉ። ቶሎ ተመልሰን መሄዳችን፣ በግለሰቡ ልብ ውስጥ የተጫረው ፍላጎት በሌሎች ሰዎች ከመጥፋቱ በፊት በመጀመሪያው ቀን በተነጋገርነው ጉዳይ ላይ ተንተርሰን ተጨማሪ ውይይት ለማድረግ ያስችለናል።
4. በመጀመሪያው ቀን ላይ ለተመላልሶ መጠየቅ መሠረት መጣል የምንችለው እንዴት ነው?
4 ቀጠሮ ያዙ፦ ፍላጎት ያሳየውን ግለሰብ መጀመሪያ ባነጋገራችሁበት ዕለት ከመለያየታችሁ በፊት ቁርጥ ያለ ቀጠሮ መያዛችሁ የተሻለ ነው። በቀጠሯችሁ ቀን የምትወያዩበትን አንድ ጥያቄ አንሱለት። በዚህ ረገድ ጥሩ ማስታወሻ መያዛችሁ በጣም አስፈላጊ ነው። ሁኔታችሁ የሚፈቅድላችሁ ከሆነ በቀጣዩ ቀን ወይም ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ተመልሳችሁ ብትመጡ ይመቸው እንደሆነ ልትጠይቁት ትችላላችሁ። መጀመሪያ የተገናኛችሁት በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ላይ ከሆነና ፍላጎት ያሳየው ግለሰብ በአዘቦት ቀናት የሚሠራ ከሆነ በሚቀጥለው ቅዳሜ ወይም እሁድ ቀጠሮ ለመያዝ ፈቃደኛ ሊሆን ይችላል። ቀጠሮ በምትይዙበት ጊዜ ቃላችሁን ጠብቃችሁ እንደምትሄዱ እርግጠኞች መሆን አለባችሁ።—ማቴ. 5:37
5. ሳንዘገይ ተመላልሶ መጠየቅ ማድረጋችን ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ የሰጠንን ተልዕኮ ለመፈጸም የሚረዳን እንዴት ነው?
5 ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን በተቻለን መጠን ቶሎ ተመልሰን ለመጠየቅ እንድንነሳሳ የሚያደርጉን አጥጋቢ ምክንያቶች አሉን። እንግዲያው ‘የቀረው ጊዜ አጭር በመሆኑ’ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ቶሎ ተመልሳችሁ ለመጠየቅ ቀጠሮ ያዙ። (1 ቆሮ. 7:29) ለመንግሥቱ መልእክት ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ተመልሰን የምንጠይቅበትን ጊዜ ባቀረብነው መጠን ጥረታችንም ፍሬያማ የመሆን አጋጣሚው እየጨመረ ይሄዳል።