የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • km 7/12 ገጽ 2-3
  • ሰዎች አምላክን እንዲሰሙ እርዷቸው

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሰዎች አምላክን እንዲሰሙ እርዷቸው
  • የመንግሥት አገልግሎታችን—2012
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አምላክን ስማ የተባለውን ብሮሹር መጠቀም የሚቻልበት መንገድ
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ—2017
  • ከአምላክ የተላከ ምሥራች!
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2013
  • ስታገለግሉ በተለያዩ ብሮሹሮች ተጠቀሙ
    የመንግሥት አገልግሎታችን—1995
  • ብሮሹሮች ለአገልግሎት ጠቃሚ የሆኑ መሣሪያዎች
    የመንግሥት አገልግሎታችን—1994
ለተጨማሪ መረጃ
የመንግሥት አገልግሎታችን—2012
km 7/12 ገጽ 2-3

ሰዎች አምላክን እንዲሰሙ እርዷቸው

1. “የአምላክ መንግሥት ይምጣ!” በተባለው የአውራጃ ስብሰባ ላይ የትኞቹን ብሮሹሮች አግኝተናል? እነዚህ ብሮሹሮች ጠቃሚ መሣሪያ እንዲሆኑ አስተዋጽኦ ያደረገውስ ምንድን ነው?

1 “የአምላክ መንግሥት ይምጣ!” በተባለው የአውራጃ ስብሰባ ላይ አምላክን ስማ የዘላለም ሕይወት ታገኛለህ እና አምላክን ስማ የተባሉ ሁለት አዳዲስ ብሮሹሮችን አግኝተናል። እነዚህ ብሮሹሮች ጽሑፍ ያልበዛባቸው ስለሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ በቀላሉ ሊተረጎሙ ይችላሉ። እንዲያውም አምላክን ስማ የዘላለም ሕይወት ታገኛለህ የተባለው ብሮሹር መጀመሪያ ላይ በወጣበት ወቅት በ431 ቋንቋዎች እንዲተረጎም ፈቃድ ተሰጥቷል።

2. ከእነዚህ ብሮሹሮች የሚጠቀሙት እነማን ናቸው?

2 ከእነዚህ ብሮሹሮች ይበልጥ የሚጠቀሙት እነማን ናቸው? እስቲ ከአገልግሎታችን ጋር በተያያዘ በዓለም ዙሪያ በተደጋጋሚ የሚከሰቱትን የሚከተሉትን ሁኔታዎች እንመልከት፦

• አንድ አስፋፊ ለመጀመሪያ ጊዜ አሊያም በተመላልሶ መጠየቅ ወቅት የቤቱ ባለቤት በደንብ ማንበብ እንደማይችል ወይም ጨርሶ እንደማያነብ ሊያስተውል ይችላል።

• አንድ አስፋፊ በሚሰብክበት ጊዜ የእኛ ጽሑፎች እምብዛም ያልተተረጎሙበትን አሊያም ጨርሶ ያልተዘጋጁበትን ቋንቋ የሚናገር ሰው ሊያጋጥመው ይችላል። ወይም ደግሞ በክልሉ ውስጥ የሚገኙት አብዛኞቹ ሰዎች፣ የምንጠቀምበትን ቋንቋ መናገር ቢችሉም ማንበብ ግን ሊከብዳቸው ይችላል።

• አንድ አስፋፊ በክልሉ ውስጥ ለሚገኙ መስማት የተሳናቸው ሰዎች በምልክት ቋንቋ የሚሰብክበት ጊዜ ይኖራል።

• አንድ ወላጅ ማንበብ ላልጀመረ ትንሽ ልጁ እውነትን ማስተማር ይፈልግ ይሆናል።

3. አምላክን ስማ የተባለው ብሮሹር የተዘጋጀበት መንገድ ምን ይመስላል?

3 ብሮሹሮቹ የተዘጋጁበት መንገድ፦ አምላክን ስማ በሚለው ብሮሹር ውስጥ የሚገኘው ጽሑፍ በጣም አነስተኛ ነው፤ በአብዛኛው በገጾቹ ግርጌ ላይ ዋናውን ነጥብ ጎላ የሚያደርግ አጭር ዓረፍተ ነገርና ጥቅስ ይገኛል። ይህ የሆነበት ምክንያት ምንድን ነው? አንድ ሰው በማታውቀው ቋንቋ የተዘጋጀ ምናልባትም ለአንተ እንግዳ በሆኑ ፊደላት የተጻፈ ብሮሹር ቢሰጥህ ምን ይሰማሃል? ማራኪ የሆኑ ሥዕላዊ መግለጫዎች ቢኖሩትም እንኳ ብሮሹሩን ለመውሰድ ትነሳሳለህ? እንደማትነሳሳ ግልጽ ነው። በተመሳሳይም ማንበብ የማይችሉ ሰዎች የሚነበብ ነገር የበዛባቸው ጽሑፎች ሲሰጣቸው ሊሸማቀቁ ይችላሉ። በመሆኑም በዚህ ብሮሹር በእያንዳንዱ ገጽ ላይ ጎላ ብለው እንዲታዩ የተደረገው ሥዕላዊ መግለጫዎቹ ናቸው፤ በተጨማሪም ውይይት የሚደረግባቸውን ሥዕላዊ መግለጫዎች ቅደም ተከተል ለማመልከት ቀስቶች ተዘጋጅተዋል።

4. አምላክን ስማ የዘላለም ሕይወት ታገኛለህ የተባለው ብሮሹር የተዘጋጀበት መንገድ ምን ይመስላል?

4 አምላክን ስማ የዘላለም ሕይወት ታገኛለህ በተባለው ብሮሹር ውስጥ የሚገኙት ሥዕላዊ መግለጫዎች አምላክን ስማ በሚለው ብሮሹር ውስጥ ካሉት ጋር አንድ ዓይነት ናቸው። አምላክን ስማ የዘላለም ሕይወት ታገኛለህ የተባለው ብሮሹር የተዘጋጀው የማንበብ ችሎታቸው ውስን ለሆኑ ወይም ማንበብ እየተማሩ ላሉ ሰዎች ነው። በተጨማሪም አንድ አስፋፊ አምላክን ስማ በተባለው ብሮሹር አማካኝነት የሚማር ጥናት ካለው አምላክን ስማ የዘላለም ሕይወት ታገኛለህ በተባለው ብሮሹር ተጠቅሞ ጥናቱን መምራት ይችላል። እያንዳንዱ ትምህርት ሁለት ገጽ የሚሸፍን ሲሆን በስተቀኝ በኩል አናት ላይ፣ በሁለቱ ገጾች ላይ መልስ የሚሰጥበት ጥያቄ አለ። በሥዕላዊ መግለጫዎቹ ውስጥ አጠር ያሉ ሐሳቦችና ጥቅሶች ይገኛሉ። አብዛኞቹ ገጾች ግርጌ አካባቢ ደግሞ የተለየ ቀለም ባለው ሣጥን ውስጥ የተማሪውን አቅም ግምት ውስጥ በማስገባት ልንወያይባቸው የምንችል ተጨማሪ ነጥቦችንና ጥቅሶች አሉ።

5. ብሮሹሮቹን መቼና እንዴት ማበርከት እንችላለን?

5 ብሮሹሮቹን መጠቀም የሚቻልበት መንገድ፦ ከቤት ወደ ቤት በምናገለግልበት ወቅት፣ አስፈላጊ እንደሆነ በሚሰማን ጊዜ ሁሉ ብሮሹሮቹን ማበርከት እንችላለን፤ በወር ውስጥ የምናበረክተው ብሮሹሮችን ባይሆንም እንኳ ይህን ማደረግ ይቻላል። (“ብሮሹሮቹን ማበርከት የሚቻልበት መንገድ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ፍላጎት ላለው ሰው ተመላልሶ መጠየቅ ስናደርግ አንድ ጽሑፍ እንዳመጣንለት ከነገርነው በኋላ ብሮሹሩን ልንሰጠው እንችላለን።

6. ብሮሹሮቹን ተጠቅመን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት የምንችለው እንዴት ነው?

6 አምላክን ስማ የተባለው ብሮሹር ጥያቄዎች ስለሌሉት ውይይቱን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ በምናስጠናበት መንገድ ማለትም በጥያቄና መልስ ማካሄድ አንችልም። በሁሉም ባሕሎች ውስጥ ሰዎች ታሪኮችን መስማት ያስደስታቸዋል። በመሆኑም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት በመንፈስ መሪነት የተጻፉ ታሪኮችን በሥዕላዊ መግለጫዎቹ ተጠቅመን ልንነግራቸው እንችላለን። ሥዕሉ የሚያስተላልፈውን መልእክት አብራሩላቸው። ማብራሪያውን በምትሰጡበት ጊዜ በጋለ ስሜት ተናገሩ። ተማሪው ሐሳቡን እንዲገልጽ አበረታቱት። በገጾቹ ግርጌ ላይ የሚገኙትን ጥቅሶች ካነበባችሁ በኋላ ተወያዩባቸው። ተማሪው በውይይቱ እንዲሳተፍ ለማድረግና ትምህርቱን ተረድቶት እንደሆነና እንዳልሆነ ለማረጋገጥ ጥያቄዎችን ተጠቀሙ። ተማሪው የሚያጠናው አምላክን ስማ የዘላለም ሕይወት ታገኛለህ የተባለውን ብሮሹር ከሆነ ለሥዕሎቹ የተሰጡትን ማብራሪያዎችና ጥቅሶቹን አብራችሁ አንብቡ።

7. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪያችን እድገት እንዲያደርግ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?

7 ተማሪው እድገት እንዲያደርግ እርዱት፦ ውይይታችሁ፣ ተማሪው በራሱ ስለ ይሖዋ እውቀት መቅሰም እንዲችል ማንበብ የመማር ፍላጎት እንዲቀሰቀስበት ሊያደርግ ይችላል። (ማቴ. 5:3፤ ዮሐ. 17:3) በመሆኑም የምትወያዩት አምላክን ስማ በሚለውን ብሮሹር ላይ ከሆነ ተስማሚ እንደሆነ ባሰባችሁት ጊዜ ላይ ጥናታችሁን ማንበብ ልታስተምሩት እንደምትችሉ ልትነግሩት ትችላላችሁ፤ ከዚያም አምላክን ስማ የዘላለም ሕይወት ታገኛለህ በተባለው ብሮሹር ጥናቱን ልትቀጥሉለት ትችላላችሁ። የምታጠኑት በየትኛውም ብሮሹር ቢሆን ተማሪው ብሮሹሩን ስለጨረሰ ብቻ ለጥምቀት ብቁ አይሆንም። ጥናቱ ብሮሹሩን ሲጨርስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ ወይም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የተሟላ እውቀት ሊሰጠው የሚችል ሌላ ተስማሚ ጽሑፍ ተጠቅማችሁ ጥናቱን ልትቀጥሉለት ይገባል።

8. በአገልግሎት ላይ ልንጠቀምባቸው የምንችል እነዚህን አዳዲስ መሣሪያዎች በማግኘታችን አመስጋኝ የሆናችሁት ለምንድን ነው?

8 ሰዎች ለዘላለም መኖር የሚፈልጉ ከሆነ የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥ የሆነውን አምላክ መስማት ይኖርባቸዋል። (ኢሳ. 55:3) የይሖዋ ፈቃድ ደግሞ ማንበብ የማይችሉትን ጨምሮ “ሁሉም ዓይነት ሰዎች” እሱን መስማት የሚችሉበትን መንገድ እንዲማሩ ነው። (1 ጢሞ. 2:3, 4) ሰዎች አምላክን መስማት የሚችሉበትን መንገድ ለማስተማር የሚረዱንን እነዚህን አዳዲስ መሣሪያዎች በማግኘታችን ምንኛ አመስጋኞች ነን!

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ብሮሹሮቹን ማበርከት የሚቻልበት መንገድ

ለምታነጋግረው ሰው በገጽ 2 እና 3 ላይ የሚገኘውን ሥዕል ካሳየኸው በኋላ እንዲህ ማለት ትችላለህ፦ “እንዲህ በመሰለ ዓለም ውስጥ መኖር ይፈልጋሉ? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።] በቅርቡ አምላክ ዓለማችንን ከድህነትና ከበሽታ የጸዳች አስደሳችና ሰላማዊ ስፍራ እንደሚያደርጋት ቅዱሳን መጻሕፍት ይናገራሉ። እንዲህ በመሰለ ዓለም ውስጥ ለመኖር ምን ማድረግ እንዳለብን የሚናገር አንድ ጥቅስ ላሳይዎት። [በገጽ 3 አናት ላይ የሚገኘውን ኢሳይያስ 55:3⁠ን አንብብለት።] ይህ ጥቅስ ወደ አምላክ ‘መቅረብና’ እሱን ‘ማዳመጥ’ እንዳለብን ይነግረናል። ይሁንና አምላክን መስማት የምንችለው እንዴት ነው?” ወደ ገጽ 4 እና 5 ሂድና ለዚህ ጥያቄ በተሰጠው መልስ ላይ ተወያዩ። የምታነጋግረው ሰው ጊዜ ከሌለው ብሮሹሩን ስጠውና በሌላ ጊዜ ተገናኝታችሁ በመልሱ ላይ ለመወያየት ቀጠሮ ያዝ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ