ብሮሹሮች ለአገልግሎት ጠቃሚ የሆኑ መሣሪያዎች
1 ጥሩ ችሎታ ያለው የእጅ ባለሙያ እያንዳንዳቸው የተወሰነ ተግባር ያላቸው ልዩ ልዩ መሣሪያዎች መያዙ የማይቀር ነው። የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች እንደመሆናችን መጠን የምንሰብክላቸውን ሰዎች መንፈሳዊ ፍላጎት በብቃት ለማሟላት የሚረዱ ብዙ ልዩ ልዩ ብሮሹሮች አሉን። (ምሳሌ 22:29) አንድ ቤት ስታንኳኳ የምታገኘው ሰው የተጨነቀ ይሆናል። ሌላኛው የቤት ባለቤት ደግሞ ሐቀኛ መስተዳድር እንዲመጣ የሚናፍቅ ሊሆን ይችላል። ሌላው ደግሞ የመኖር ዓላማ ምን ይሆን በማለት የሚጨነቅ ይሆናል። እነዚህን ሰዎች ለመርዳት በብሮሹሮቻችን እንዴት መጠቀም እንችላለን?
2 “አምላክ ስለ እኛ በእርግጥ ያስባልን?” የተባለውን ብሮሹር ስታበረክት እንዲህ ለማለት ትችል ይሆናል፦
◼ “በዓለም ያለውን መከራና የፍትሕ መጓደል የተመለከቱ አንዳንድ ሰዎች አምላክን ለዚህ ነገር ተጠያቂ አድርገው መውቀስ ይቀናቸዋል። አምላክ ሁሉን ቻይ ስለሆነ ለእኛ የሚያስብ ቢሆን ኖሮ መከራዎቻችንን ሁሉ ያስወግድልን ነበር የሚል ምክንያት ያቀርባሉ። እርስዎስ ስለዚህ ጉዳይ እንዴት ይሰማዎታል? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት] መዝሙር 72:12–14 አምላክ በእርግጥ እንደሚያስብልን ያሳያል። መከራና ፍትሕ መጓደል የመጣው ከእርሱ ስሕተት አይደለም። በቅርቡ ክፉ አድራጊዎች እንደሚጠፉ ተስፋ ሰጥቷል። “አምላክ ስለ እኛ በእርግጥ ያስባልን?” የተባለው ይህ ብሮሹር አምላክ ምን እንደሚያደርግና እኛ እንዴት መጠቀም እንደምንችል ያሳያል።” ውይይቱን በገጽ 27 አንቀጽ 22 ላይ ባለው ሐሳብ ለመቀጠል ትችል ይሆናል።
3 “የአምላክ መንግሥት ገነትን ታመጣለች” የተባለውን ብሮሹር ለማበርከት በገጽ 31 ላይ ያለውን ስዕላዊ መግለጫ በማሳየትና የሚከተለውን ጥያቄ በመጠየቅ ልታስተዋውቅ ትችላለህ፦
◼ “ምድር ይህንን እንድትመስል ምን ያስፈልጋል ብለው ያስባሉ? [ሐሳብ እንዲሰጥ ፍቀድለት] በዚህ ስዕል ላይ የሚታየው ሰው ሁሉ ደስተኛ ነው። ሰላምና የተትረፈረፈ ምግብ ከመኖሩም ሌላ ምድሪቱን የሚበክል ነገር የለም። ሰብዓዊ መንግሥታት ምንም ቢጥሩ እንዲህ ዓይነቱን ዓለም ማምጣት የማይቻል ሆኖባቸዋል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ሁሉን አዲስ እንደሚያደርግ ያረጋግጥልናል። [ራእይ 21:3, 4ን አንብብ] ይህ ብሮሹር በዚህ አዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር ምን ማድረግ እንደሚያስፈልግዎ እንዲያውቁ ሊረዳዎት ይችላል።”
4 “በምድር ላይ ኑር!” ለተባለው ብሮሹር የሚከተለውን አቀራረብ ልትጠቀም ትችላለህ፦
◼ አያሌ ሰዎች ለዘላለም ተደስተው ለመኖር ሰማይ መሄድ እንዳለባቸው ያስባሉ። እርስዎስ በምድር ላይ ለዘላለም ስለመኖር ምን ይሰማዎታል? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት] መጽሐፍ ቅዱስ ለዘላለም መኖር እንደሚቻል ከማረጋገጥ ሌላ እንዴት ልናገኘው እንደምንችልም ይነግረናል።” ዮሐንስ 17:3ን አንብብ። ከዚያም ለቤቱ ባለቤት ሥዕል ቁጥር 49ን አሳየውና እንደሚከተለው ብለህ ጠይቀው:- “ይህን በመሰለ ዓለም ውስጥ ስለመኖር ምን ይሰማዎታል?” ብሮሹሩን አበርክትለትና ተመልሰህ መጠየቅ የምትችልበትን መንገድ አመቻች።
5 ብሮሹሮቹ ወቅታዊ ርዕሶችን የሚያቀርቡ፣ የሰዎችን ጥያቄዎች የሚመልሱና ማጽናኛ የሚሰጡ ናቸው። እነዚህን መሣሪያዎች በጥበብ በመጠቀም ቅኖች “ወደ ትክክለኛው የእውነት እውቀት እንዲደርሱ” ልንረዳቸው እንችላለን። — 1 ጢሞ. 2:4 አዓት