የቆዩ መጽሔቶችን ጥሩ አድርጋችሁ ተጠቀሙባቸው
የቆዩ መጽሔቶችን ከማስቀመጥ ወይም ከመጣል ይልቅ ማበርከታችን የተሻለ ጥቅም ያስገኛል። አንድ መጽሔት ብቻ አንድን ሰው ለእውነት ፍላጎት እንዲያድርበትና የይሖዋን ስም ለመጥራት እንዲነሳሳ ሊያደርገው ይችላል። (ሮም 10:13, 14) የቆዩ መጽሔቶችን ጥሩ አድርገን እንድንጠቀምባቸው የሚረዱ አንዳንድ ጠቃሚ ሐሳቦች ከዚህ ቀጥሎ ቀርበዋል፦
ብዙ ባልተሠራባቸው ክልሎች ውስጥ ስትሰብኩ ሰው ያላገኛችሁባቸው ቤቶች ውስጥ አላፊ አግዳሚው በማያይበት ቦታ ላይ አንድ የቆየ መጽሔት ትታችሁ ልትሄዱ ትችላላችሁ።
እንደ አውቶብስ ፌርማታ ወይም ባቡር ጣቢያዎች ባሉ፣ ሰዎች ቆመው በሚጠብቁባቸው ቦታዎች የአደባባይ ምሥክርነት ስትሰጡ ሰዎችን ቀርባችሁ የሚያነብቡት ነገር ይፈልጉ እንደሆነ ጠይቋቸው፤ ከዚያም በርከት ያሉ የቆዩ መጽሔቶችን በማውጣት መርጠው እንዲወስዱ አድርጉ።
እንደ ክሊኒክ፣ ጤና ጣቢያ፣ ባንክ ወይም የውበት ሳሎን ወዳሉ በክልላችሁ የሚገኙ ሕዝባዊ አገልግሎት ወደሚሰጡ ተቋማት ስትሄዱ በእንግዳ ማረፊያው አካባቢ ጥቂት የቆዩ መጽሔቶችን ልታስቀምጡ ትችላላችሁ። አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ከማድረጋችሁ በፊት የሚመለከተውን አካል ፈቃድ ብትጠይቁ የተሻለ ነው። በርከት ያሉ መጽሔቶች ቀድሞውኑም በቦታው እንደተቀመጡ ካስተዋላችሁ ተጨማሪ ማስቀመጡ አስፈላጊ አይደለም።
ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ በምትዘጋጁበት ወቅት ተመላልሶ መጠየቅ የምታደርጉለትን ሰው ትኩረት ሊስብ የሚችለውን ነገር አስቡ። ግለሰቡ ቤተሰብ አለው? የተለያዩ ቦታዎችን መጎብኘት ያስደስተዋል? አትክልት መንከባከብ ይወዳል? ከቆዩ እትሞች ውስጥ የእሱን ትኩረት ሊስብ የሚችል ርዕስ የያዙ መጽሔቶችን ለማግኘት ጥረት አድርጉ፤ ከዚያም ተመልሳችሁ ስትሄዱ መጽሔቱን ልትሰጡት ትችላላችሁ።
በተደጋጋሚ ብትሄዱም ልታገኙት ያልቻላችሁት ፍላጎት ያለው ሰው ካለና አንድ ቀን ቤቱ ስትሄዱ ካገኛችሁት በመሃል ያልደረሱትን አንዳንድ እትሞች ልታሳዩት ትችላላችሁ።