ወዲያውኑ ተከታትላችሁ እርዷቸው
ድረ ገጻችን በአዲስ መልክ ከተዘጋጀ ወዲህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲመራላቸው በድረ ገጹ አማካኝነት የሚጠይቁ ሰዎች ቁጥር በጣም ጨምሯል። በቅርቡ የተጀመረው የአደባባይ ምሥክርነትም ተመሳሳይ ጥያቄ የሚያቀርቡ ሰዎች ቁጥር እንዲጨምር አስተዋጽኦ አድርጓል። ቅርንጫፍ ቢሮው እነዚህ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኙ ያደርጋል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው በjw.org አማካኝነት እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ቢያቀርብ በአብዛኛው በሁለት ቀናት ውስጥ ግለሰቡ በሚኖርበት ክልል ያሉ የጉባኤ ሽማግሌዎች ከቅርንጫፍ ቢሮው መልእክት ይደርሳቸዋል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ጥያቄ ያቀረቡ አንዳንድ ሰዎች ለበርካታ ሳምንታት ማንም ሰው እንዳላነጋገራቸው ሪፖርት ተደርጓል። ግለሰቡ ፍላጎቱ ከመጥፋቱ በፊት እርዳታ እንዲያገኝ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?—ማር. 4:14, 15
ከክልላችሁ ውጭ የሚኖር ፍላጎት ያለው ሰው ካገኛችሁ እባካችሁ ተከታትላችሁ እርዱት (S-43) የተባለውን ቅጽ ወዲያውኑ ሞልታችሁ እጅግ ቢዘገይ በቀጣዩ የጉባኤ ስብሰባ ወቅት ለጉባኤያችሁ ጸሐፊ መስጠት ይኖርባችኋል። ከዚያም ጸሐፊው በአንድ ወይም በሁለት ቀናት ውስጥ ይህን መረጃ፣ ለሚመለከተው ጉባኤ አሊያም jw.org ላይ “ጉባኤ” (Congregation) በሚለው ሥር ገብቶ ለቅርንጫፍ ቢሮው መላክ ይኖርበታል። ሽማግሌዎች ድረ ገጹን አዘውትረው መከታተል ይኖርባቸዋል። አንድን ሰው ተከታትለው እንዲረዱት የሚገልጽ መልእክት ከደረሳቸው ግለሰቡን ወዲያውኑ ተከታትለው መርዳት አለባቸው። አንድ አስፋፊ ግለሰቡን እንዲያነጋግረው ከተመደበ ለዚህ ጉዳይ ቅድሚያ መስጠት ይኖርበታል። ግለሰቡን ቤቱ ማግኘት ካልቻላችሁ ከአጭር ማስታወሻ ጋር አድራሻችሁን ትታችሁለት መሄድ ትችላላችሁ።