መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ዘመናችን የደረሰው እንዴት ነው? ክፍል አንድ
ክፍል 2 እና 3 በመስከረም 15 እና በጥቅምት 15 እትሞች ላይ በተከታታይ ይወጣሉ።
በአንዲት ትንሽ ክፍል ውስጥ አንድ አታሚ ከወጣት ረዳቶቹ ጋር ሆኖ ባዶ የወረቀት ገጾችን በጥንቃቄ በማተሚያው ላይ በማስቀመጥ ከእንጨት የተሠራውን ማተሚያቸውን ያንቀሳቅሳሉ። ወረቀቶቹ ሲወጡም የታተመውን ገጽ አንስተው ይመለከታሉ። ከዚያም ወረቀቶቹ እንዲደርቁ እያጠፉ ከአንዱ ግድግዳ እስከሌላው ግድግዳ ድረስ በተዘረጋው ሲባጎ ላይ ያንጠለጥሏቸዋል።
ድንገት በሩ በኃይል ተንኳኳ። የተደናገጠው አታሚ የበሩን መቀርቀሪያ ሲከፍት ብዙ የታጠቁ ወታደሮች ተንጋግተው ገቡ። ከዚያም እጅግ የተወገዘውን ሕገ ወጥ ጽሑፍ ማለትም በተራው ሕዝብ ቋንቋ የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ መፈለግ ጀመሩ!
በጣም ዘግይተዋል። ይህ ነገር እንደሚከሰት አስቀድመው የተገነዘቡት ተርጓሚና ረዳቱ ወደዚች ክፍል ተሯሩጠው መጥተው የቻሉትን ያክል ገጾች በእቅፋቸው አፋፍሰው በመሸሽ ወደ ሪይን ወንዝ አካባቢ ደርሰዋል። ቢያንስ ከፊሉን ሥራቸውን አድነዋል።
ይህ ተርጓሚ ዊልያም ቲንደል ሲሆን የታገደበትን የእንግሊዝኛ “አዲስ ኪዳን” ትርጉም በ1525 በጀርመን ኮሎኝ ከተማ ለማተም እየሞከረ ነበር። ቲንደል የገጠመው እንግዳ ነገር አልነበረም። መጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ ከተጠናቀቀበት ጊዜ ወዲህ ባሉት 1,900 የሚያክሉ ዓመታት በሙሉ ብዙ ወንዶችና ሴቶች የአምላክን ቃል ለመተርጎምና ለማሠራጨት ሲሉ ያልከፈሉት መሥዋዕትነት የለም። ዛሬ ያለነው ሰዎችም ከእነርሱ ሥራ ተጠቃሚዎች ሆነናል። እነዚህ ሰዎች ምን ሠርተዋል? ዛሬ በእጃችን ያለው መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ዘመናችን የደረሰው እንዴት ነው?
የጥንቱ መጽሐፍ ቅዱስን የመገልበጥና የመተርጎም ሥራ
በየዘመኑ የኖሩት የአምላክ እውነተኛ አገልጋዮች ለቃሉ ከፍተኛ ግምት ነበራቸው። ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ እንዲህ ሲል አረጋግጧል:- “የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ከእነርሱ በፊት እንደነበሩት አይሁዳውያን ቅዱሳን መጻሕፍትን ማንበብ በጣም አስፈላጊ ነው የሚል እምነት ነበራቸው። ሐዋርያቱ የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል (ማቴ 4.4፤ 5.18፤ ሉቃ 24.44፤ ዮሐ 5.39) ከብ[ሉይ] ኪ[ዳን] ጋር ጥሩ ትውውቅ አዳብረው ነበር፤ ይህም ረዘም ላለ ጊዜ በአንክሮ ያነቡና ያጠኑ እንደነበር ያሳያል። ከዚህም በላይ ደቀ መዛሙርቶቻቸው እንዲሁ እንዲያደርጉ አጥብቀው አሳስበዋል (ሮሜ 15.4፤ 2 ጢሞ 3.15-17)።”
ይህንን ለማድረግ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች መዘጋጀት ነበረባቸው። ይህ ሥራ በቅድመ ክርስትና ዘመን በአብዛኛው የሚከናወነው በሙያው ከፍተኛ ልምድ በነበራቸው ‘የተካኑ ጸሐፊዎች’ አማካኝነት ሲሆን እነዚህ ሰዎች ስህተት እንዳይሠሩ በጣም ይጠነቀቁ ነበር። (ዕዝራ 7:6, 11, 12) እንከን የለሽ ሥራ ለመሥራት ያደረጉት ተጋድሎ ከእነርሱ በኋላ ለመጡት የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ አዘጋጅዎች ሁሉ ከፍተኛ ጥራት ያለው ሥራ እንዲሠሩ ጥሩ አርዓያ ሆኗቸዋል።
ይሁንና በአራተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ አንድ ፈታኝ ሁኔታ ተፈጠረ። ታላቁ እስክንድር የዓለም ሕዝብ በሙሉ የግሪክን ባሕል እንዲማር ለማድረግ ቆርጦ ተነሣ። የታላቁ እስክንድር ድል ተራው ግሪክኛ ወይም ኮይኔ በመላው መካከለኛው ምሥራቅ የጋራ መግባቢያ ቋንቋ እንዲሆን አድርጓል። በዚህም ምክንያት ብዙ አይሁዳውያን የዕብራይስጥን ቋንቋ ንባብ ሳይማሩ በማደጋቸው ቅዱሳን ጽሑፎችን ማንበብ አልቻሉም። በመሆኑም በ280 ከዘአበ ገደማ ከዕብራውያን የተውጣጣ አንድ የምሁራን ቡድን በዕብራይስጥ ቋንቋ የሚገኘውን መጽሐፍ ቅዱስ በሰፊው ወደሚሠራበት የኮይኔ ቋንቋ ለመተርጎም በግብጽ እስክንድርያ ተሰባሰበ። የትርጉም ሥራቸው ሰፕቱጀንት የሚል ስያሜ አገኘ፤ የቃሉ ትርጉም በላቲን “ሰባ” ማለት ሲሆን በሥራው ተካፍለዋል ተብለው የሚታሰቡትን ተርጓሚዎች ቁጥር የሚያመለክት ነው። የትርጉም ሥራው የተጠናቀቀው በ150 ከዘአበ ነበር።
የዕብራይስጥ ቋንቋ ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት በፍልስጤም ምድር ይሠራበት ነበር። ይሁንና በዚህ ቦታም ሆነ ራቅ ብለው በሚገኙት በቀሩት የሮማ ክፍለ ግዛቶች የገነነው የኮይኔ ቋንቋ ነበር። በመሆኑም ክርስቲያኖቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በተቻለ መጠን በተለያዩ ብሔራት ውስጥ ያሉትን ብዙ ሰዎች ለመጥቀም ሲሉ በተራው ግሪክኛ ተጠቅመዋል። በተጨማሪም ከሰፕቱጀንት ትርጉም በብዛት ጠቅሰዋል፣ ከዚያ የተወሰዱ አንዳንድ መግለጫዎችንም ተጠቅመዋል።
የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ቀናተኛ ሚስዮናውያን ስለነበሩ በሰፕቱጀንት ትርጉም ተጠቅመው ኢየሱስ ከረጅም ጊዜ አንስቶ ሲጠበቅ የነበረው መሲሕ መሆኑን ለማስረዳት ብዙ ጊዜ አልፈጀባቸውም። ይህም ነገር አይሁዳውያኑን ስላስቆጣቸው በአንዳንድ ምንባቦች ላይ ለውጥ በማድረግ ክርስቲያኖችን ማስረጃ ለማሳጣት በማሰብ በግሪክኛ ቋንቋ አዲስ ትርጉም ለማዘጋጀት ተነሳሡ። ለምሳሌ ያህል የሰፕቱጀንት ትርጉም በኢሳይያስ 7:14 ላይ ስለ መሲሑ እናት የሚገልጸውን ትንቢታዊ ቃል ሲያስቀምጥ “ድንግል” የሚል ትርጉም ባለው የግሪክኛ ቃል ተጠቅሟል። አዲሱ ትርጉም ደግሞ “ወጣት ሴት” የሚል ትርጉም ያለው ሌላ የግሪክኛ ቃል ተጠቅሟል። ክርስቲያኖች በሰፕቱጀንት ትርጉም መጠቀማቸውን በመቀጠላቸው አይሁዳውያኑ የጀመሩትን ዘዴ እርግፍ አድርገው ትተው ሰዎች ፊታቸውን ወደ ዕብራይስጡ ጽሑፍ እንዲያዞሩ ማበረታታት ጀመሩ። አይሁዳውያኑ ይህን ማድረጋቸው የዕብራይስጥ ቋንቋ ሕያው ሆኖ እንዲቀጥል በማስቻሉ ከጊዜ በኋላ ለተሠሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች እጅግ ጠቅሟል።
የመጀመሪያዎቹ መጽሐፍ አዘጋጂዎች የሆኑት ክርስቲያኖች
የጥንቶቹ ቀናተኛ ክርስቲያኖች የቻሉትን ያክል በእጅ የተገለበጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ለማዘጋጀት ቆርጠው ተነስተው ነበር። በጥቅልሎች መጠቀምን አቁመው እንደ ዛሬዎቹ መጻሕፍት ገጽ ያላቸውን የኮዴክስ ጽሑፎች ለመጀመሪያ ጊዜ አዘጋጅተዋል። የኮዴክስ ጽሑፍ ጥቅሶቹን በፍጥነት ለማግኘት አመቺ ከመሆኑም በላይ በአንዲት ጥቅልል ውስጥ ሊሠፍር ከሚችለው ነገር የበለጠ ብዙ ነገር በአንድ ጥራዝ ውስጥ ማካተት ይቻላል። ለምሳሌ ያህል አንድ የኮዴክስ ጥራዝ መላውን የግሪክኛ ቅዱስ ጽሑፍ ወይም ጠቅላላውን መጽሐፍ ቅዱስ ሊይዝ ይችላል።
የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል የተደመደመው ከሐዋርያት መካከል መጨረሻ በሕይወት የቆየው ዮሐንስ በጻፋቸው መጻሕፍት በ98 እዘአ ገደማ ነው። ራይላንድ ፓፒረስ 457 (P52) በመባል የሚታወቀው ከ125 እዘአ ቀደም ብሎ የተዘጋጀው የዮሐንስ ወንጌል ቁራጭ ተገኝቷል። የሰማዕቱ ጀስቲን ተማሪ የነበረው ታሸን ከ150 እስከ 170 እዘአ ባሉት ዓመታት መካከል ዲያቴሳሮን የተሰኘውንና በዛሬው መጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ከሚገኙት አራት ወንጌሎች ያጠናቀረውን ስለ ኢየሱስ ሕይወት የሚገልጽ ዘገባ አዘጋጅቷል።a ይህም እነዚህ አራት ወንጌሎች ብቻ ትክክለኛ ናቸው ብሎ ያምን እንደነበርና በወቅቱም እነዚህ ወንጌሎች ተሠራጭተው እንደነበር የሚጠቁም ነው። በ170 እዘአ ገደማ ዛሬ ሙራቶሪያን ፍራግመንት በመባል የሚታወቀውና ካሉት የ“አዲስ ኪዳን” መጻሕፍት ዝርዝር ሁሉ ጥንታዊ የሆነው ቅጂ ተዘጋጀ። ይህ ሙራቶሪያን ፍራግመንት አብዛኛዎቹን የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች መጻሕፍት ስም ይዘረዝራል።
የክርስትና እምነት መስፋፋቱ ብዙም ሳይቆይ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች እንዲሁም የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም እንዲዘጋጅ የሚያስገድድ ሆነ። እንደ አርሜንያ፣ ኮፕቲክ፣ ጆርጅያ እና ሲርያ ባሉት ቋንቋዎች በርከት ያሉ ትርጉሞች ተዘጋጁ። ብዙውን ጊዜም ለዚሁ ዓላማ ሲባል ሆሄያት ማዘጋጀት አስፈልጓል። ለምሳሌ ያህል በአራተኛው መቶ ዘመን የሮማ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ የነበረው ኡልፊላስ መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጎም ሲል የጎቲክ ሆሄያትን እንደፈለሰፈ ይነገርለታል። ይሁን እንጂ የነገሥት መጻሕፍት የጎትን ሕዝብ የጦረኝነት መንፈስ ያበረታታሉ ብሎ ስላሰበ ከትርጉሙ ውስጥ አውጥቷቸዋል። ይሁንና እርሱ እንደዚያ ማድረጉ “ክርስትናን የተቀበሉት” የጎት ሰዎች በ410 እዘአ ሮምን በምርኮ ከመበዝበዝ እንዲታቀቡ አላደረገም!
የላቲንና የስላቮን መጽሐፍ ቅዱሶች
በዚህ መሃል የላቲን ቋንቋ ጉልህ ስፍራ እያገኘ በመምጣቱ ጥንታዊ የላቲን ትርጉሞች ብቅ አሉ። ይሁን እንጂ በአተረጓጎም ስልታቸውም ሆነ በትክክለኛነታቸው ይለያዩ ነበር። በመሆኑም በ382 እዘአ ሊቀ ጳጳስ ዳማሰስ ጸሐፊያቸው ጄሮም አስተማማኝ የሆነ የላቲን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያዘጋጅ ጠየቁት።
ጄሮም የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን የላቲን ትርጉሞች በመመርመር ሥራውን ጀመረ። ይሁን እንጂ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች መተርጎም ያለባቸው ከመጀመሪያው የዕብራይስጥ ጽሑፍ ነው የሚል ጽኑ እምነት ነበረው። በመሆኑም በ386 እዘአ የዕብራይስጥ ቋንቋ ለማጥናትና በሥራው የሚረዳው ረቢ ለማግኘት ወደ ቤተ ልሔም ሄደ። ይህም በቤተ ክርስቲያን አካባቢ ከፍተኛ ውዝግብ አስነስቷል። በዚያ ዘመን የኖረውን አውጉስቲንን ጨምሮ አንዳንዶች ሰፕቱጀንት በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ እንደሆነ አድርገው ያምኑ ስለነበር ጄሮም “እርዳታ ለማግኘት ወደ አይሁዳውያን በመሄዱ” አወገዙት። ጄሮም በጀመረው ጎዳና ወደ ፊት በመግፋት በ400 እዘአ ሥራውን አጠናቀቀ። ጄሮም ቅዱሳን ጽሑፎች በመጀመሪያ የተጻፉባቸው ቋንቋዎችና መዛግብት ወደሚገኙበት ምንጭ ቀረብ ብሎ መጽሐፍ ቅዱስን በዘመኑ ሕያው ወደነበረው ቋንቋ በመተርጎም ከአንድ ሺህ ዓመታት በፊት ለዘመናዊው የትርጉም ሥራ ፈር ቀዷል። የትርጉም ሥራው ቩልጌት ወይም ቀላል ትርጉም በመባል የሚታወቅ ሲሆን ሰዎች ለብዙ መቶ ዘመናት ሲገለገሉበት ቆይተዋል።
በዚሁ ጊዜ በምሥራቃውያኑ የሕዝበ ክርስትና ወገኖች ዘንድ የሰፕቱጀንትን ትርጉምም ሆነ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን ማንበብ የሚችሉ ብዙዎች ነበሩ። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ የስላቮን ወይም የስላቭ ቤተሰብ የሆኑ ቋንቋዎችና ቀበሌኛዎች በምሥራቅ አውሮፓ አካባቢዎች እየተዘወተሩ መጡ። በ863 እዘአ ሲሪል እና መቶድየስ የተባሉ ሁለት ግሪክኛ ተናጋሪ የሆኑ ወንድማማቾች ዛሬ በቼክ ሪፐብሊክ ውስጥ ወደምትገኘው ሞራቪያ ሄዱ። እዚያም መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቱ የስላቮን ቋንቋ መተርጎም ጀመሩ። ይህንንም ለማድረግ ሲሉ ከጊዜ በኋላ ሲሪል ከሚለው ቃል በመነሳት ሲሪሊክ የሚል ስያሜ ባገኘው ፊደል የተተካውን የግላጎቲክ ፊደል አዘጋጁ። የዛሬዎቹ የሩሲያ፣ ዩክሬን፣ ሰርቢያ እና ቡልጋሪያ ሆሄያት የተገኙት ከዚሁ ፊደል ነው። በስላቮን ቋንቋ የተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ በዚያ አካባቢ ያሉትን ሰዎች ለብዙ ዘመናት አገልግሏል። ይሁንና ከጊዜ በኋላ ቋንቋዎች እየተለወጡ ሲሄዱ አብዛኛዎቹ ሰዎች ይህን ቋንቋ ለመረዳት ተቸገሩ።
የዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ አልጠፋም
ከስድስተኛው እስከ አሥረኛው መቶ ዘመን እዘአ ባለው በዚህ ጊዜ ውስጥ ማሶሬቶች በመባል የሚታወቅ የአይሁዳውያን ቡድን የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠብቆ ለማቆየት የሚያስችል ቅጂዎችን የመገልበጥ ዘዴ አዘጋጀ። ትክክለኛ የሆነውን ጽሑፍ ጠብቀው ለማቆየት በማሰብ በጥንት ጽሑፎች መካከል ያለውን ልዩነት ለማነጻፀር እያንዳንዱን መስመርና ፊደል ሳይቀር ይቆጥሩ ነበር። ሆኖም ድካማቸው ከንቱ ሆኖ አልቀረም። አንድ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል ዛሬ ያለው የማሶሬቶች ጽሑፍ ከ250 ከዘአበ እስከ 50 እዘአ ባለው ጊዜ ውስጥ ከተጻፉት የሙት ባሕር ጥቅልሎች ጋር ሲወዳደር በመካከል ከ1,000 ዓመታት የሚበልጥ የጊዜ ልዩነት ቢኖርም ምንም የመሠረተ ትምህርት ልዩነት አይታይም።b
በጥቅሉ ሲታይ መካከለኛው ዘመንና የጨለማው ዘመን አውሮፓ ውስጥ ተመሳሳይ የሆነን ወቅት የሚያመለክቱ ናቸው። በዚህ ጊዜ ማንበብና መማር በብዙሐኑ ዘንድ ያን ያህል ቦታ አልነበረውም። የኋላ ኋላ አብዛኛዎቹ ቀሳውስት ሳይቀሩ የቤተ ክርስቲያኒቱን የላቲን ቋንቋ ማንበብ ተስኗቸዋል፤ እንዲያውም ብዙውን ጊዜ የራሳቸውን ቋንቋ እንኳን ማንበብ አይችሉም ነበር። አይሁዶች በአውሮፓ ውስጥ በአንድ አካባቢ ታጉረው እንዲኖሩ የተደረገውም በዚሁ ወቅት ነበር። አይሁዳውያን እንዲህ ተገልለው እንዲኖሩ መደረጋቸው መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበት የዕብራይስጥ ቋንቋ እውቀት ተጠብቆ እንዲቆይ በከፊል አስተዋጽኦ አድርጓል። ይሁን እንጂ በወቅቱ በአይሁዳውያኑ ላይ በነበረው ስሜታዊ ጥላቻና ጥርጣሬ የተነሣ የአይሁዳውያኑ የቋንቋ እውቀት በአብዛኛው በዚያ ሕብረተሰብ ዘንድ ብቻ ተወስኖ ቀርቷል። በምዕራብ አውሮፓም የግሪክኛ ቋንቋ ትምህርት እያሽቆለቆለ ሄዶ ነበር። ዌስተርን ቸርች ለጄሮም የላቲን ቩልጌት ትርጉም ከፍተኛ ግምት መስጠቱ ይህንን ሁኔታ አባብሶታል። በማሶሬቶች ዘመን ማብቂያ ላይ ላቲን እየከሰመ ቢሄድም ይህ ትርጉም ብቸኛው አስተማማኝ ትርጉም እንደሆነ ተደርጎ ይታመን ነበር። በዚህ መንገድ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የማወቁ ፍላጎት ቀስ በቀስ እያደገ ሲመጣ ታላቅ የቅራኔ መድረክ ተከፈተ።
የመጽሐፍ ቅዱስ የትርጉም ሥራ ተቃውሞ ገጠመው
በ1079 ሊቀ ጳጳስ ግሪጎሪ ሰባተኛ በመካከለኛው ዘመን ቤተ ክርስቲያን ካወጣቻቸው ብዙ ድንጋጌዎች መካከል የመጀመሪያ የሆነውንና በአገሬው ቋንቋ ትርጉም ማዘጋጀትን አንዳንድ ጊዜም ይዞ መገኘትን የሚከለክለውን እገዳ አወጣ። በስሎቫን ቋንቋ ቅዳሴ እንዲደረግ ከፈቀድኩ ቅዱስ ጽሑፉ በከፊል እንዲተረጎም ያስፈልጋል ብሎ ስላሰበ በስሎቫን ቋንቋ ቅዳሴ ማድረግን ከለከለ። ከጥንቶቹ ክርስቲያኖች አቋም ፈጽሞ ተቃራኒ የሆነ አመለካከት በመያዝ “በአንዳንድ ቦታዎች ቅዱሳን ጽሑፎች ምሥጢር መሆናቸው ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ያስደስተዋል” ሲል ጽፏል። የቤተ ክርስቲያንም ኦፊሴላዊ አቋም ይኸው ስለነበር መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብን የሚያበረታቱ ሰዎች አደገኛ እንደሆኑ ተደርገው ይታዩ ነበር።
ሁኔታው አስቸጋሪ ቢሆንም የመጽሐፍ ቅዱስን ቅጂ የማዘጋጀቱና በተራው ሕዝብ ቋንቋ የመተርጎሙ ሥራ ቀጥሎ ነበር። በብዙ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ትርጉሞች በአውሮፓ ውስጥ በድብቅ ተሠራጩ። እስከ 1400 አጋማሽ ድረስ በአውሮፓ ውስጥ ተንቀሳቃሽ ማተሚያዎች ስላልተሠሩ እነዚህ ሁሉ በእጅ የተገለበጡ ቅጂዎች ነበሩ። ይሁን እንጂ ቅጂዎቹ በጣም ውድና ቁጥራቸውም ውስን በመሆኑ አንድ ተራ ነዋሪ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ክፍል ወይም ጥቂት ገጾች ብቻ ቢያገኝ እንኳን በጣም ይደሰት ነበር። አንዳንዶች በጣም ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን አልፎ ተርፎም ጠቅላላውን የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ሳይቀር በቃላቸው ያጠኑ ነበር!
ሆኖም ከጊዜ በኋላ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ተሐድሶ እንዲካሄድ የሚጠይቁ መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴዎች ይደረጉ ጀመር። የአምላክ ቃል በእያንዳንዱ ሰው ዕለታዊ ሕይወት ውስጥ ስላለው ጠቀሜታ ያገኙት አዲስ ግንዛቤ ለእነዚህ እንቅስቃሴዎች በከፊል አስተዋጽኦ አድርጓል። እነዚህ እንቅስቃሴዎችና በሕትመቱ መስክ የታየው እድገት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ምን ውጤት ይኖራቸው ይሆን? በመግቢያችን ላይ የጠቀስነው ዊልያም ቲንደልና የትርጉም ሥራውስ የት ደርሰው ይሆን? ይህንን ልብ የሚያንጠለጥል ታሪክና እስከ ዘመናችን ድረስ ያለውን ሁኔታ ወደፊት በሚወጡት እትሞች ላይ እንቀጥላለን።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ እና ትራክት ማኅበር የተዘጋጀው እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው የተባለው መጽሐፍ በአራቱ ወንጌሎች መካከል ያለውን ስምምነት የሚያረጋግጥ ዘመናዊ ምሳሌ ነው።
b ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የተዘጋጀውን ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለውን (የእንግሊዝኛ) መጽሐፍ ጥራዝ 2 ገጽ 315 ተመልከት።
[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ግራፍ]
በመጽሐፍ ቅዱስ የሥርጭት ታሪክ ቁልፍ የሆኑ ዘመናት
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ከዘመናችን አቆጣጠር በፊት (ከዘአበ)
የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች የተጠናቀቁበት 443 ከዘአበ ገደማ
400 ከዘአበ
ታላቁ እስክንድር (በ323 ከዘአበ ሞተ)
300 ከዘአበ
ሰፕቱጀንት በ280 ከዘአበ ገደማ ተጀመረ
200 ከዘአበ
100 ከዘአበ አብዛኞቹ የሙት ባሕር ጥቅልሎች 100 ከዘአበ እስከ 68 እዘአ ገደማ
እንደ ዘመናችን አቆጣጠር (እዘአ)
ኢየሩሳሌም የጠፋችበት ዘመን 70 እዘአ
የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች የተጠናቀቁት በ98 እዘአ
100 እዘአ
የዮሐንስ የራይላንድ ፓፒረስ (በ125 እዘአ ተዘጋጀ)
200 እዘአ
300 እዘአ
400 እዘአ የጄሮም የላቲን ቩልጌት 400 እዘአ ገደማ
500 እዘአ
600 እዘአ
የማሶሬቶች ጽሑፍ ተዘጋጀ
700 እዘአ
800 እዘአ
በ863 እዘአ በሞራቪያ የሲሪል ቋንቋ ትርጉም ተዘጋጀ
900 እዘአ
1000 እዘአ
በአገሬው ቋንቋ በተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ በ1079 እዘአ እገዳ ተጣለ
1100 እዘአ
1200 እዘአ
1300 እዘአ
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጥንት ክርስቲያኖች የኮዴክስ ጽሑፎችን በማዘጋጀት ረገድ ቀዳሚ ሆነዋል
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጄሮም የዕብራይስጥ ቋንቋ ለማጥናት ወደ ቤተ ልሔም ሄዶ ነበር