የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • km 12/08 ገጽ 3-4
  • በአፓርታማዎች ውስጥ ‘በሚገባ መመሥከር’

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በአፓርታማዎች ውስጥ ‘በሚገባ መመሥከር’
  • የመንግሥት አገልግሎታችን—2008
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በስልክ መመስከር ብዙ ሰዎችን ማግኘት የሚቻልበት መንገድ ነው
    የመንግሥት አገልግሎታችን—1993
  • የጥያቄ ሣጥን
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2009
  • በማንኛውም ቦታ ምሥራቹን ስበኩ
    የመንግሥት አገልግሎታችን—1996
  • በምሽት ምሥክርነት ለመካፈል ሞክርሃል?
    የመንግሥት አገልግሎታችን—1996
ለተጨማሪ መረጃ
የመንግሥት አገልግሎታችን—2008
km 12/08 ገጽ 3-4

በአፓርታማዎች ውስጥ ‘በሚገባ መመሥከር’

1. ‘ምሥራቹን በሚገባ መመሥከር’ ምን ነገርን ይጨምራል?

1 እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ሁሉ እኛም ‘ምሥራቹን በሚገባ መመሥከር’ እንፈልጋለን። (ሥራ 20:24) ስለዚህ በአገልግሎት ክልላችን ውስጥ የመንግሥቱን መልእክት በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች ለመስበክ ጥረት እናደርጋለን። ይህም በአፓርታማዎች ውስጥ ለሚኖሩ በርካታ ሰዎች መስበክን ይጨምራል። አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ወዳሉ መኖሪያዎች መግባት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ በአፓርታማዎች ውስጥ በርካታ ሰዎች ስለሚኖሩ ምሥራቹን ለመስበክ የሚያስችል ግሩም አጋጣሚ ልናገኝ እንችላለን።

2. በአፓርታማዎች ላይ በምንመሠክርበት ጊዜ ዘዴኛ መሆናችንና የማመዛዘን ችሎታችንን በሚገባ መጠቀማችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

2 ወንጀልና ዓመጽ እየበዛ በመምጣቱ በአንዳንድ ቦታዎች ያሉ አፓርታማዎች ዝግ ከመሆናቸውም በላይ በዘበኞች ወይም በካሜራ ይጠበቃሉ። (2 ጢሞ. 3:1, 2) የጥበቃ ሠራተኞቹ እንግዳ የሆኑ ሰዎችን ያለ ፈቃድ እንዳያስገቡ መመሪያ ሊሰጣቸው ይችላል። በተለይ ነዋሪዎቹ ቅሬታ ካሰሙ ዘበኞቹ ግቢውን ለቅቀን እንድንሄድ ይጠይቁን ይሆናል። በመሆኑም ዘዴኛ መሆናችንና የማመዛዘን ችሎታችንን በሚገባ መጠቀማችን አስፈላጊ ነው።

3. በአፓርታማዎች ለማገልገል የተሻለ የሚሆነው ጊዜ የትኛው ነው? ለምንስ?

3 መቼ ብናገለግል ይመረጣል? በሌሎች የአገልግሎት ክልሎች እንደምናደርገው ሁሉ በአፓርታማዎች ውስጥ በምናገለግልበት ጊዜም ሰዎች ቤታቸው ሊኖሩ በሚችሉበት ጊዜ ብንሄድ ይመረጣል። አብዛኛዎቹ ነዋሪዎች ቤታቸው በማይኖሩበት ጊዜ ብንሄድ አላስፈላጊ ጥርጣሬ ሊፈጥር ይችላል። ብዙ አስፋፊዎች ሰዎች ከሥራ ወደ ቤታቸው በሚመለሱበት ሰዓት ማለትም አመሻሽ ላይ እንዲሁም ቅዳሜና እሁድ ማገልገሉ የተሻለ ሆኖ አግኝተውታል። በማለዳ በተለይ ደግሞ ቅዳሜና እሁድ በጠዋት ሄዶ ማገልገሉ ነዋሪዎቹ በጥበቃ ሠራተኞቹ ላይ ቅሬታ እንዲያሰሙ ሊያደርጋቸው ይችላል።

4, 5. ዝግ ወደሆኑ አፓርታማዎች ለመግባት ምን ዘዴ መጠቀም እንችላለን?

4 ወደ አፓርታማዎች መግባት የምንችልበት መንገድ፦ አስፋፊዎች አገልግሎት ከመጀመራቸው በፊት የአፓርታማውን የጥበቃ ሠራተኞች ማነጋገር አያስፈልጋቸውም። አፓርታማው ዝግ ከሆነና ነዋሪዎቹን ከውጭ ሆኖ ለማነጋገር የሚያስችል የመገናኛ መስመር (intercom) ካለው ገብተን እንድናነጋግረው የሚፈልግ ሰው ይኖር እንደሆነ ለመጠየቅ በዚህ መስመር መጠቀም እንችላለን። እንድንገባ ከፈቀደልን ሰው ጋር ከተነጋገርን በኋላ እንደ አፓርታማው ሁኔታ ሌሎቹንም ቤቶች በዚያው ማንኳኳት እንችል ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ ግን ከአፓርታማው ወጥተን ቀጥሎ ባለው ቤት የሚኖረውን ሰው ለማነጋገር እንደገና በመገናኛ መስመሩ መጠቀም የተሻለ ሊሆን ይችላል። በዚህ መንገድ በአንድ ጊዜ ምን ያህል ነዋሪዎችን ብናነጋግር የተሻለ እንደሚሆን ለመወሰን ሁኔታዎችን በሚገባ ማመዛዘን ይኖርብናል።

5 አንዳንድ ነዋሪዎች እዚያው በር ላይ ሆናችሁ በመገናኛ መስመሩ አማካኝነት የመጣችሁበትን ምክንያት እንድታሳውቋቸው ይፈልጉ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ወዳጃዊ በሆነ መንፈስ ራሳችሁን አስተዋውቁ። በመገናኛው መስመር ላይ የቤቱ ባለቤት ስም ተጽፎ ከሆነ ስሙን እየጠቀሳችሁ ተናገሩ። ልትናገሩ የፈለጋችሁትን መልእክት አጠር አድርጋችሁ ግለጹ። አንዳንድ አስፋፊዎች መግቢያውን ከማመራመር መጽሐፍ ላይ በቀጥታ ማንበቡ ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል።

6. በዘበኛ በሚጠበቁ አፓርታማዎች በምናገለግልበት ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

6 አፓርታማውን የሚጠብቅ ዘበኛ ካለና እንዳንገባ ከከለከለን ለእሱ ለመመሥከር ጥረት ማድረግ እንችላለን። ብዙ ዘበኞች ጽሑፎቻችንን ማንበብ ያስደስታቸዋል። እንዲያውም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ልናስጀምርና እዚያው ዘበኛ ቤት ውስጥ ልናስጠና እንችላለን። ዘበኛው ፍላጎት ያሳየን አንድ ነዋሪ ገብተን እንድናነጋግር ከፈቀደልን በአብዛኛው አጋጣሚውን አገኘን ብለን በዚያው ሌሎቹን ቤቶች ማንኳኳታችን ጥሩ አይሆንም።

7. የአገልግሎት ቦርሳችንን በተመለከተ ልናስብበት የሚገባን ጉዳይ ምንድን ነው?

7 የምንይዘው ቦርሳና ሥርዓታማነት፦ ትልቅ ቦርሳ መያዝ አላስፈላጊ ትኩረት ሊስብ ይችላል። በመሆኑም ብዙም ትኩረት የማይስብ ቦርሳ መያዝ አለዚያም ጭራሽ ቦርሳ አለመያዝ ይመረጣል። አንዳንድ አስፋፊዎች የሚያበረክቱትን ጽሑፍ እንደ ባይንደር ባለ ትንሽ መያዣ ውስጥ አድርገው ይሄዳሉ፤ መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ደግሞ በእጃቸው ወይም በኪሳቸው ይይዙታል።

8. በአፓርታማዎች ላይ በምናገለግልበት ጊዜ ቡድኑን በምን መንገድ ማደራጀት ይኖርብናል?

8 አላስፈላጊ ትኩረት እንዳንስብ በበሩ አካባቢ ወይም ግቢው ውስጥ ብዙ ሆነን መሰብሰብ አይኖርብንም። ወንጀል በሚበዛባቸው አካባቢዎች ባሉ አፓርታማዎች በምናገለግልበት ጊዜ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። (ምሳሌ 22:3) ለምሳሌ ያህል፣ በሁለት ወይም በሦስት ቡድን የተከፈሉ ጥንድ ጥንድ አስፋፊዎች በቅርብ ርቀት ሆነው እርስ በርስ እየተያዩ በአንድ መደዳ ያሉ ቤቶችን ማንኳኳት ይችላሉ። ምናልባትም አንደኛው ቡድን ሲያንኳኳ ሌላው ሊጠብቅ ይችላል።

9. ጥሩ ጠባይ ልናሳይ የምንችለው እንዴት ነው? ይህስ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

9 አንድ አፓርታማ ውስጥ በምትገቡበት ጊዜ ጫማችሁን መጥረግ እንዲሁም ከገባችሁ በኋላ በሩን በደንብ መዝጋት ይኖርባችኋል። እንዲህ ያለ ጥሩ ጠባይ በማሳየት ነዋሪዎቹ ብዙ ቅሬታ እንዳያሰሙ ማድረግ ይቻላል። አንዴ ከገባችሁ በኋላ መግቢያው አካባቢ ወዲያ ወዲህ ከማለት ይልቅ ቀጥ ብላችሁ ወደ ሊፍቱ አለዚያም ወደምታንኳኳቸው ቤቶች መሄድ ይኖርባችኋል። እንዲህ ማድረጋችሁ የሚመለከቷችሁ ሰዎች ጥርጣሬ እንዳያድርባቸው ያደርጋል።

10. በኮሪደሮች ላይ ድምፃችን እንዳይረብሽ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

10 በብዙ አፓርታማዎች፣ ድምፅ በኮሪደሮች ውስጥ በቀላሉ ሊያስተጋባ ይችላል። ስለዚህ የቤቱ ባለቤት የምትናገሩትን ነገር መስማት እስከቻለ ድረስ ድምፃችሁን በጣም ከፍ ማድረግ አያስፈልጋችሁም። ከሌሎች አስፋፊዎች ጋር በምትነጋገሩበት ጊዜ ድምፃችሁን ዝግ ማድረግ ይኖርባችኋል፤ ሆኖም ሌሎች ሰዎች ጥርጣሬ እንዳያድርባቸው በተረጋጋ መንፈስና መካከለኛ በሆነ የድምፅ ቃና ልትነጋገሩ ይገባል። አንዳንድ አስፋፊዎች ነዋሪዎችን ላለመረበሽ ሲሉ በመደዳ ከማንኳኳት ይልቅ ቤቶቹን በሙሉ አንኳኩተው እስኪጨርሱ ድረስ እያፈራረቁ አንዴ በአንዱ ጫፍ ቀጥሎ ደግሞ በሌላኛው ጫፍ ያንኳኳሉ። ከዚህም በተጨማሪ በሩን በኃይል ወይም እንደ ባለሥልጣን ማንኳኳት የቤቱን ባለቤቶች ሊያስደነግጥ ይችላል።

11. ማሾለቂያ ቀዳዳ ያለውን በር ስናንኳኳ ምን ብናደርግ የተሻለ ሊሆን ይችላል?

11 በሩ ማሾለቂያ ቀዳዳ ካለው፣ ውስጥ ያለው ሰው ሁለታችሁንም ሊያይ በሚችልበት መንገድ መቆም ይኖርባችኋል። አተኩራችሁ ወደ ቀዳዳው ተመልከቱ፤ አንድ ሰው ከውስጥ ሆኖ እየተመለከተ እንዳለ ስትረዱ ሞቅ ያለ ሰላምታ በማቅረብ መልእክታችሁን መናገር ጀምሩ። ሰውየው ‘ማን ነው?’ ብሎ ከጠየቀ የሁለታችሁንም ስም መናገራችሁ ጥሩ ይሆናል። በዚህ ጊዜ የቤቱ ባለቤት ተረጋግቶ በሩን ሊከፍት ይችላል። በሩን ባይከፍትም እንኳ እዚያው እንደቆማችሁ የያዛችሁትን መልእክት ልትነግሩት ትችላላችሁ።

12. ሰው በሌለባቸው ቤቶች ጽሑፎችን ችግር በማያስከትል ሁኔታ ማስቀመጥ የምንችለው እንዴት ነው?

12 ቤት ውስጥ ሰው በማይኖርበት ጊዜ፦ የሕንፃ ተቆጣጣሪዎች ወይም የጽዳት ሠራተኞች ጽሑፎች በኮሪደሮች ላይ ወይም ግቢ ውስጥ ወዳድቀው እንደሚያገኙ በመግለጽ በተደጋጋሚ ቅሬታ ያሰማሉ። ደጃፍ ላይ የተተወ ጽሑፍ በቀላሉ የአካባቢውን ውበት ሊያበላሽ ይችላል። ስለዚህ ሰው በሌለባቸው ቤቶች ጽሑፎችን የምናስቀምጠው አላፊ አግዳሚው ሊያያቸው በማይችል ሁኔታ መሆን አለበት።

13. ቁጡ የሆነ የቤት ባለቤት ካጋጠመን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

13 ቁጡ የቤት ባለቤቶች ሲያጋጥሙን፦ ቁጡ የሆነ የቤት ባለቤት ካጋጠመንና ዘበኞችን የመጥራት ሐሳብ እንዳለው ካስተዋልን በዚያ ወለል ላይ ያሉ ቤቶች ትተን በመሄድ ሌላ ጊዜ መመለሳችን የተሻለ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከዘበኞቹ ጋር አላስፈላጊ ውዝግብ ውስጥ ላለመግባት ስንል ሕንፃውን ሙሉ በሙሉ ለቅቀን መሄዳችን ጥበብ ሊሆን ይችላል። የቤቱ ባለቤት ዳግመኛ መጥተን ቤቱን እንዳናንኳኳ በቀጥታ ባያስጠነቅቀንም እንኳ የቤቱን ቁጥርና ሰውየው እንድናነጋግረው እንደማይፈልግ የሚገልጽ ማስታወሻ ከያዝን በኋላ የክልል ካርዱን በምንመልስበት ጊዜ ይህን ማስታወሻ አብረን መስጠት እንችላለን። በዚህ መንገድ የተመዘገቡ ቤቶችን አልፎ አልፎ በማንኳኳት የሰዎቹን ፍላጎት ለማወቅ ጥረት መደረግ ይኖርበታል።

14, 15. አንድ የአፓርታማ ተወካይ ሕንፃውን ለቅቀን እንድንወጣ ቢጠይቀን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

14 ሕንፃውን ለቅቃችሁ እንድትሄዱ በምትጠየቁበት ጊዜ፦ በአፓርታማው ውስጥ እያገለገላችሁ እያለ የጥበቃ ሠራተኞች፣ የጥገና ሠራተኞች ወይም ሌላ ማንኛውም የአፓርታማው ተወካይ ሕንፃውን ለቅቃችሁ እንድትወጡ ቢጠይቋችሁ ወዲያውኑ የተባላችሁትን ማድረጋችሁ የተሻለ ነው። በተቻለን መጠን፣ ሕጋዊ እርምጃ ወደ መውሰድ ወይም ፖሊስ ወደ መጥራት የሚያደርስ ውዝግብ ውስጥ ላለመግባት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። አብዛኛውን ጊዜ የአፓርታማ ሠራተኞች ሕንፃውን ለቅቀን እንድንወጣ የሚጠይቁን ለእኛ ጭፍን ጥላቻ ኖሯቸው ሳይሆን ሥራቸው ስለሚያስገድዳቸው ነው።

15 አንዳንድ ጊዜ አንድ የአፓርታማ ተወካይ ሕንፃውን ለቅቃችሁ እንድትወጡ ሲጠይቃችሁ የመጣችሁበትን ዓላማ ወዳጃዊ በሆነ መንፈስና በዘዴ ልታስረዱት ትችላላችሁ። (1 ጴጥ. 3:15) ነዋሪዎቹን የማስደሰትና የሕንፃውን ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት እንገነዘባለን። ምናልባት በሕንፃው ውስጥ ማገልገላችሁን እንድትቀጥሉ ይፈቅድላችሁ ይሆናል። ካልፈቀደላችሁ ግን ሙግት ሳትፈጥሩ በሰላም ተለያዩ። ሁኔታው የሚፈቅድ ከሆነና አፓርታማው ውስጥ እንግዶች አረፍ ብለው የሚጠብቁበት ቦታ ካለ በየጊዜው ጽሑፎችን እያመጣችሁ እዚያ ለማስቀመጥ ፈቃድ መጠየቅ ትችላላችሁ። (ቆላ. 4:6) እንዲህ ያሉ ሁኔታዎችንና ገጠመኞችን ለአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ ማሳወቅ ያስፈልጋል።

16. በአፓርታማዎች ውስጥ ለማገልገል በምንሞክርበት ጊዜ በተደጋጋሚ ችግሮች የሚያጋጥሙን ከሆነ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

16 ምናልባት አስፋፊዎች ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ጥበብ በመጠቀም በዚህ ሕንፃ ውስጥ ለማገልገል ሊሞክሩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ችግሩ ከቀጠለ አስፋፊዎች ራሳቸው መፍትሔ ለማግኘት ከሚሞክሩ ይልቅ ሽማግሌዎች እርዳታ ለማግኘት ቅርንጫፍ ቢሮውን ማነጋገር ይኖርባቸዋል። አስፋፊዎች በአፓርታማዎቹ ላይ ማገልገል ካልቻሉ ስልክ በመደወል፣ ደብዳቤ በመጻፍ ወይም በሌሎች መንገዶች ነዋሪዎቹን ለማነጋገር ጥረት ማድረግ ይችላሉ። አንዳንድ አስፋፊዎች፣ ሰዎች ወደ ሥራ በሚሄዱበትና ወደ ቤት በሚመለሱበት ሰዓት በሕንፃው አካባቢ ቆመው ምሥክርነት ለመስጠት ይሞክራሉ።

17. በአፓርታማዎች ውስጥ መስበክ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

17 ይህ ክፉ ሥርዓት የሚጠፋበት ጊዜ በጣም ቀርቧል። ከጥፋቱ የሚድኑት የይሖዋን ስም የሚጠሩ ሰዎች ብቻ ናቸው። “ይሁንና ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ስለ እሱ ሳይሰሙስ እንዴት ያምኑበታል?” (ሮም 10:13, 14) “የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው” በርካታ ሰዎች በአፓርታማዎች ውስጥ ይኖራሉ። (ሥራ 13:48) ዘዴኛ በመሆንና ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ በመጠቀም ምሥራቹን ልንሰብክላቸው እንችላለን።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ