በጥቅምት ወር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር ትችላላችሁ?
1. በጥቅምት ወር የሚበረከተው ምንድን ነው?
1 በጥቅምት ወር የምናበረክተው መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን ነው። ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ለመርዳት እውነቱን ማወቅ ትፈልጋለህ? በተባለው ትራክት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንድናስጀምር ከዚህ በፊት ተበረታተን ነበር። ታዲያ በተመላልሶ መጠየቅ ወቅት እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
2. መጽሔት ላበረከትንለት ሰው ተመላልሶ መጠየቅ ስናደርግ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር እውነቱን ማወቅ በተባለ ትራክት እንዴት መጠቀም እንችላለን?
2 በትራክቱ እንዴት መጠቀም እንችላለን? እንዲህ ማለት እንችላለን፦ “ትቼልዎት የሄድኳቸው መጽሔቶች የተለያየ አስተዳደግና ሃይማኖት ያላቸው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲመረምሩ ያበረታታሉ። [እውነቱን ማወቅ ትፈልጋለህ? የተባለውን ትራክት ሰጥተነው በመጀመሪያው ገጽ ላይ ያሉትን ጥያቄዎች እናሳየዋለን።] በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መልስ ከሚያገኙ ትኩረት የሚስቡ ጥያቄዎች መካከል አንዳንዶቹ እዚህ ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል የእርስዎ ጥያቄ የሆነ አለ?” የቤቱ ባለቤት መልስ ከሰጠ በኋላ ትራክቱ ለጥያቄው የሚሰጠውን መልስ አብራችሁ ተመልከቱ፤ እንዲሁም ከተጠቀሱት ጥቅሶች መካከል አንዱን አንብቡ። ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምራቸው በርካታ ትምህርቶች መካከል ይህ አንዱ ብቻ እንደሆነ ግለጹለትና የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ ስጡት። ከዚያም ከርዕስ ማውጫው ላይ በመረጠው ምዕራፍ የመጀመሪያዎቹ አንቀጾች ላይ ውይይት ማድረግ እንችላለን። ወይም በትራክቱ ላይ ስለተወያየነው ርዕስ ተጨማሪ ሐሳብ የያዘውን ምዕራፍ እንመርጥለት ይሆናል። የሚከተሉትን እንደማጣቀሻነት ልንጠቀምባቸው እንችላለን፦
● አምላክ በእርግጥ ያስብልናል? (ከገጽ 9-11 ከአን. 6-10)
● ጦርነትና መከራ ማብቂያ ይኖራቸው ይሆን?
● ስንሞት ምን እንሆናለን?
● ሙታን ምን ተስፋ አላቸው?
● አምላክ እንዲሰማኝ እንዴት መጸለይ ይኖርብኛል?
● በሕይወቴ እውነተኛ ደስታ ማግኘት የምችለው እንዴት ነው? (ገጽ 9 ከአን. 4-5)
3. አቀራረባችንን እንደ ሁኔታው መለዋወጥ የምንችለው እንዴት ነው?
3 እርግጥ ነው፣ በመጀመሪያው ተመላልሶ መጠየቅ ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በተባለው መጽሐፍ አማካኝነት ጥናት ለማስጀመርና እንዴት እንደሚጠና ለማሳየት ሁኔታው የማይመች ከሆነ ተመልሰን ለመምጣትና ውይይታችንን ለመቀጠል ቀጠሮ መያዝ እንችላለን። እንዲሁም መጽሐፉን ከማስተዋወቃችን በፊት እንደ ሰውየው ፍላጎት ትራክቱ ውስጥ ባሉ የተለያዩ ጥያቄዎች ላይ ለመወያየት እንመርጥ ይሆናል። በጥቅምት ወር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመርና ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ‘እውነትን እንዲያውቁ’ ለመርዳት በዚህ ጠቃሚ ትራክት በሚገባ እንጠቀም።—ዮሐ. 8:31, 32