የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር የሚረዳ አዲስ አምድ
1. በሚበረከተው የመጠበቂያ ግንብ እትም ላይ ምን አዲስ አምድ ይወጣል? የዚህ አምድ ዓላማስ ምንድን ነው?
1 ከጥር ወር ጀምሮ፣ ለሕዝብ በሚበረከተው የመጠበቂያ ግንብ እትም ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር የሚረዳ አዲስ አምድ መውጣት ይጀምራል። የዚህ አምድ ርዕስ “ከአምላክ ቃል ተማር” የሚል ነው። በክልላችሁ ውስጥ የምታገኟቸው አንዳንድ ሰዎች በዚህ አምድ ሥር የሚወጡትን ርዕሶች ማንበብ እንደሚፈልጉ እሙን ነው፤ ይሁንና እነዚህ ርዕሶች በዋነኝነት የተዘጋጁት ከሰዎች ጋር ውይይት ለማድረግ ታስቦ ነው።
2. ይህ አምድ ምን ገጽታዎች አሉት?
2 አምዱ ያሉት ገጽታዎች፦ በውይይቱ ወቅት የቤቱን ባለቤት ጥያቄ ለመጠየቅ እንዲያመች ዋናው ርዕስና ንዑስ ርዕሶቹ በጥያቄ መልክ ቀርበዋል። የቤቱ ባለቤት ጥቅሶችን በቀጥታ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ማንበብ እንዲችል ቁልፍ የሆኑ ጥቅሶችን በጽሑፉ ላይ ከማስፈር ይልቅ ምዕራፍና ቁጥራቸው ብቻ እንዲቀመጥ ተደርጓል። አንቀጾቹ አጫጭር ስለሆኑ በር ላይ እንደቆምን መወያየት እንችላለን። አስፈላጊ ሲሆን ጥናቱን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ወደተባለው መጽሐፍ ማሸጋገር እንድትችል በእያንዳንዱ ርዕሰ ትምህርት ላይ ይህ መጽሐፍ ተጠቅሷል።
3. ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል ይህን አምድ በር ላይ እንደቆምን ጥናት ለማስጀመር ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው?
3 እንዴት ልንጠቀምበት እንችላለን? መጽሔቶችን ስናበረክት ከርዕሰ ትምህርቱ አጠቃላይ ይዘት በመነሳት የቤቱን ባለቤት የማወቅ ፍላጎት የሚቀሰቅስ ጥያቄ መጠየቅ እንችላለን። ለምሳሌ የጥር 1, 2011 እትም መጽሐፍ ቅዱስ ስላለው ጠቀሜታ ያብራራል። እንዲህ በማለት መጠየቅ ትችላለህ፦ “መጽሐፍ ቅዱስን የሚመለከቱት እንደ አምላክ ቃል ነው ወይስ እንዲሁ ጥሩ መጽሐፍ እንደሆነ አድርገው ነው? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።] በዚህ ጉዳይ ዙሪያ አንድ ትኩረት የሚስብ ነገር ላሳይዎት።” የመጀመሪያውን ጥያቄ አሳየውና ከጥያቄው በታች ያለውን አንቀጽ አንብብ፤ ከዚያም በአንቀጹ ላይ ያለውን ጥቅስ አንብብ። ጥያቄውን በድጋሚ አንብብና የቤቱ ባለቤት ምን ሐሳብ እንዳለው ጠይቀው። ለውይይት የቀረቡትን ጥያቄዎች በመጠቀም ሁኔታው በፈቀደ መጠን የተወሰኑ ቁጥሮችን ለመሸፈን ጥረት አድርግ። ተሰናብተህ ከመሄድህ በፊት የሚቀጥለው ተራ ቁጥር ላይ ያለውን ጥያቄ አሳየውና ሌላ ጊዜ ተመልሰህ በመምጣት ውይይቱን ለመቀጠል ቁርጥ ያለ ቀጠሮ ያዝ። ቀጣዩን እትም እስክታመጣለት ድረስ በየሳምንቱ እየሄድክ በቀሩት ነጥቦች ላይ ለመወያየት ጥረት አድርግ። ሌላው አማራጭ ደግሞ የቤቱ ባለቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምር ቀጥተኛ ግብዣ ማቅረብ ነው። ከዚያም መጽሔቱ ላይ ያለውን ርዕስ አውጥተህ ጥናት እንዴት እንደሚጠና አሳየው።
4. ተመላልሶ መጠየቅ ስናደርግ እነዚህን ርዕሶች እንዴት ልንጠቀምባቸው እንችላለን?
4 ይህን አዲስ አምድ የመጽሔት ደንበኞቻችን ጋ ስንሄድ እንዲሁም ተመላልሶ መጠየቅ ስናደርግ ውጤታማ በሆነ መንገድ ልንጠቀምበት እንችላለን። እንዲህ ማለት እንችላለን፦ “ይህ የመጠበቂያ ግንብ እትም አዲስ አምድ አለው። እስቲ ይህን አዲስ አምድ እንዴት ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ላሳይዎት።” ይህ አዲስ ተከታታይ ርዕሰ ትምህርት ብዙ አዳዲስ ሰዎች “የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ” እንዲረዳቸው እንጸልያለን።—1 ጢሞ. 2:4