የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በተባለው መጽሐፍ ለማጥናት ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎችን መርዳት
1. የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለው መጽሐፍ መጀመሪያ ላይ የሁሉንም ሰዎች ትኩረት ሊስብ ይችላል? አብራራ።
1 አንድ ሰው የይሖዋ አገልጋይ መሆን ከፈለገ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ማወቅ አለበት። ይሁን እንጂ አንዳንድ ሰዎች የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች አይደሉም፤ በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን እንደ አምላክ ቃል አድርገው አይቀበሉም። ሌሎች ደግሞ ጨርሶ በአምላክ የማያምኑና ለመጽሐፍ ቅዱስ ምንም አክብሮት የሌላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። መጀመሪያ ላይ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ ለመቀበል ፍላጎት የሌላቸውን ሰዎች ለመርዳት የትኞቹ መሣሪያዎች ይጠቅሙናል? ከዚህ በታች የቀረቡት ሐሳቦች 20 በሚያህሉ አገሮች ውስጥ ያሉ አስፋፊዎች በሰጡት አስተያየት ላይ የተመሠረቱ ናቸው።
2. አንድ ሰው በአምላክ እንደማያምን ከነገረን ምን ነገር ለማወቅ ጥረት ማድረግ አለብን? ለምንስ?
2 በአምላክ ለማያምኑ፦ አንድ ሰው በአምላክ እንደማያምን ከነገረን ምክንያቱ ምን እንደሆነ ማወቅ ጠቃሚ ነው። በዝግመተ ለውጥ ስለሚያምን ነው? በአምላክ ላይ እምነት እንዳይኖረው ያደረገው በዓለም ላይ የሚታየው የፍትሕ መዛባት ወይም በሃይማኖቶች ውስጥ የሚታየው ግብዝነት ነው? በአምላክ ማመን ትክክል እንዳልሆነ በሚነገርበት አገር ስላደገ ነው? አምላክ የለም ብሎ በግትርነት ባይናገርም በአምላክ ማመን አስፈላጊ እንዳልሆነ ይሰማው ይሆን? በርካታ አስፋፊዎች “በፊቱንም እንዲህ ይሰማህ ነበር?” የሚል ጥያቄ ማቅረብ ግለሰቡ የሚሰማውን እንዲናገር እንደሚያነሳሳው ተገንዘበዋል። ሲናገር ሳታቋርጡ በጥሞና አዳምጡት። ግለሰቡ በአምላክ የማያምነው ለምን እንደሆነ መረዳታችን ምን ምላሽ እንደምንሰጥና የትኛውን ጽሑፍ ማበርከት እንዳለብን ለመወሰን ይረዳናል።—ምሳሌ 18:13
3. ለምናነጋግረው ሰውም ሆነ ለሚያምንባቸው ነገሮች አክብሮት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
3 መልስ ስንሰጥ ግለሰቡ፣ የእሱን አመለካከት እያጣጣልንበት እንደሆነ እንዳይሰማው ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖር አንድ አስፋፊ እንዲህ ብሏል፦ “አንድ ሰው የፈለገውን ነገር የማመን መብት ያለው መሆኑን አምኖ መቀበልና ይህን መብቱን ማክበር በጣም አስፈላጊ ነው። ሰዎችን ለመርታት ጥረት ከማድረግ ይልቅ፣ ቆም ብለው እንዲያስቡና የራሳቸው መደምደሚያ ላይ እንዲደርሱ የሚረዱ ጥያቄዎችን መጠቀም የተሻለ ነው።” አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ብዙውን ጊዜ የቤቱን ባለቤት ምላሽ ካዳመጠ በኋላ “ይህን ጉዳይ በዚህ መልኩስ አስበውት ያውቃሉ?” የሚል ጥያቄ በማንሳት ሐሳቡን ማካፈል እንደሚጀምር ተናግሯል።
4. የቡድሂስት እምነት ተከታዮችን መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?
4 አብዛኞቹ የቡድሂስት እምነት ተከታዮች ስለ አምላክ የሚነገረው ነገር እንግዳ ይሆንባቸዋል። በብሪታንያ የሚገኙ አንዳንድ አስፋፊዎች እንዲህ ላሉ ሰዎች ለመመሥከር ላስቲንግ ፒስ ኤንድ ሃፒነስ—ሃው ቱ አቴይን ኢት የተባለው ብሮሹር ጠቃሚ እንደሆነ ተገንዝበዋል። በመግቢያው ሐሳብ ላይ ከተወያዩ በኋላ “በእርግጥ ከሁሉ በላይ የሆነ ፈጣሪ አለ?” በሚለው ክፍል ላይ ውይይት ያደርጋሉ፤ ከዚያም “ለመላው የሰው ዘር በረከት የሚያስገኝ መመሪያ የያዘ መጽሐፍ” የሚለውን ክፍል ይወያዩበታል። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ ለቤቱ ባለቤት የሚያስተዋውቁት ከዚያ በኋላ ነው፤ በዚህ ወቅት “በአምላክ መኖር የማታምን ቢሆንም እንኳ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ መመሪያዎችን ስለያዘ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህ ይጠቅምሃል” የሚል ሐሳብ ያቀርቡለታል። ቻይናውያን በብዛት በሚገኙበት አካባቢ የሚያገለግል በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ያለ አንድ አቅኚ እንዲህ ብሏል፦ “በክልላችን ውስጥ ያሉ ብዙ ሰዎች ማንበብ ይወዳሉ። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ተመልሰን ልንጠይቃቸው ከመምጣታችን በፊት ጽሑፉን ሙሉ በሙሉ አንብበው ይጠብቁናል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የሚባለው ምን እንደሆነ ላይገባቸው ይችላል። ስለዚህ በመጀመሪያው ቀን፣ ምሥራች የተባለውን ብሮሹር እሰጣቸዋለሁ፤ ይህ ብሮሹር የተዘጋጀው ውይይት ለመጀመር በሚያነሳሳ መንገድ ነው።” በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በቻይንኛ ቋንቋ የሚመሩ ጉባኤዎች በሚገኙበት ወረዳ የሚያገለግል አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች፣ ሰዎቹን ባናገርንበት በዚያው ዕለት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ ማስተዋወቅ እንደሚቻል ተናግሯል። ይሁን እንጂ ጥናት ስናስጀምራቸው ስለ አምላክ ከሚናገረው ከምዕራፍ 1 ከመጀመር ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስን ከሚያስተዋውቀው ከምዕራፍ 2 መጀመሩ የተሻለ እንደሆነ ገልጿል።
5. ትዕግሥተኛ መሆን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
5 አንዳንድ ሰዎች በአምላክ ለማመን ጊዜ ስለሚፈጅባቸው ትዕግሥተኛ መሆን በጣም አስፈላጊ ነው። በመጀመሪያው ቀን ያደረግነው ውይይት ብቻ ግለሰቡ በፈጣሪ መኖር እንዲያምን አያደርገው ይሆናል። ይሁን እንጂ በጊዜ ሂደት፣ ‘ፈጣሪ ሳይኖር አይቀርም’ ብሎ ሊያስብ አሊያም ሌሎች በፈጣሪ መኖር እንዲያምኑ የሚያደርጋቸው ምን እንደሆነ ሊገነዘብ ይችል ይሆናል።
6. አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለመመርመር ፍላጎት የማይኖራቸው ለምን ሊሆን ይችላል?
6 ፍላጎት ለሌላቸው ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ለማያምኑ ሰዎች፦ ብዙውን ጊዜ አንድ ሰው፣ አምላክ እንዳለ ቢያምንም መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን ስለማይቀበል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን ትምህርቶች ለማወቅ ፍላጎት ላይኖረው ይችላል። ይህ ሰው ያደገው የክርስትና እምነት በሌለበት አገር በመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ከሕዝበ ክርስትና ጋር የተያያዘ እንደሆነ አድርጎ ያስብ ይሆናል። ወይም ደግሞ በሚኖርበት አካባቢ ያሉ ሰዎች ክርስቲያን ነን ቢሉም ለሃይማኖት ቦታ እንደማይሰጡ ሲመለከት መጽሐፍ ቅዱስን ማወቅ ምንም አይጠቅመኝም ብሎ ይወስን ይሆናል። ታዲያ እንዲህ ያሉ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን የመመርመር ፍላጎት እንዲያድርባቸውና ውሎ አድሮም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በተባለው መጽሐፍ ለማጥናት ፈቃደኛ እንዲሆኑ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?
7. ብዙውን ጊዜ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን የመመርመር ፍላጎት እንዲያድርባቸው ለማድረግ የተሻለው ዘዴ ምንድን ነው?
7 የግሪክ ቅርንጫፍ ቢሮ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለማወቅ ፍላጎት የሌላቸውን ሰዎች ለመርዳት ከሁሉ የተሻለው ዘዴ በቀጥታ መጽሐፍ ቅዱስን ከፍቶ የያዘውን ሐሳብ ማሳየት ነው። ብዙ አስፋፊዎች፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው መልእክት እነሱ ከሚናገሩት ከየትኛውም ሐሳብ የበለጠ በአንድ ሰው ልብ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ተገንዝበዋል። (ዕብ. 4:12) በርካታ ሰዎች የአምላክን ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ማየታቸው መጽሐፍ ቅዱስን የመመርመር ፍላጎት እንዲያድርባቸው አድርጓል።” በሕንድ ያለው ቅርንጫፍ ቢሮ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ብዙ ሂንዱዎች ስለ ሕይወትና ስለ ሞት እውነቱን ማወቅ ያስደስታቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ የመደብ ልዩነት የሌለበት ዓለም እንደሚመጣ የሚሰጠውን ተስፋም በጣም ይወዱታል።” አስፋፊዎች፣ በአካባቢው ያሉ ሰዎችን የሚያሳስቧቸውን ነገሮች መጥቀሳቸውም የአምላክ መንግሥት እነዚህን ችግሮች ለማስተካከል እርምጃ እንደሚወስድ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ለማሳየት አጋጣሚ ይከፍትላቸዋል።
8. በሕዝበ ክርስትና ምክንያት ለመጽሐፍ ቅዱስ መጥፎ አመለካከት ያዳበሩ ሰዎችን ለመርዳት ምን ማለት እንችላለን?
8 አንድ ሰው በሕዝበ ክርስትና ትምህርቶች ምክንያት ለመጽሐፍ ቅዱስ መጥፎ አመለካከት እንዳዳበረ ከተገነዘብክ፣ ሕዝበ ክርስትና ስለ መጽሐፍ ቅዱስና ስለሚያስተምራቸው ትምህርቶች የተሳሳተ መልእክት እንደምታስተላልፍ ግለጽለት። በሕንድ ያለው ቅርንጫፍ ቢሮ “አንዳንድ ጊዜ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ለአብያተ ክርስቲያናት በአደራ እንዳልተሰጣቸው ሰዎች እንዲገነዘቡ መርዳት ያስፈልገናል” ሲል ጽፏል። ሂንዱዎች የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው? እንዴትስ ልታገኘው ትችላለህ? የተባለው ብሮሹር ክፍል 4 ላይ ያለው አብያተ ክርስቲያናት የአምላክን ቃል ለመበረዝና ለማጥፋት እንደሞከሩ የሚገልጸው ሐሳብ እንደሚነካቸው ተስተውሏል። በብራዚል የሚኖር አንድ አቅኚ በአገልግሎት ላይ ለሚያገኘው ሰው እንዲህ ይላል፦ “መጽሐፍ ቅዱስ ስለያዘው ሐሳብ ይበልጥ ለማወቅ ለምን ጥረት አታደርግም? ብዙ ሰዎች የአንድ ሃይማኖት አባል መሆን ሳያስፈልጋቸው ቀና አስተሳሰብ ይዘው መጽሐፍ ቅዱስን እየመረመሩ ነው። አንተም ይህን ብታደርግ ያልጠበቅኸው ነገር ልታገኝ ትችላለህ።”
9. አንድ ሰው መጀመሪያ ላይ ለመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ፍላጎት ባይኖረው ተስፋ መቁረጥ የሌለብን ለምንድን ነው?
9 ይሖዋ የእያንዳንዱን ሰው ልብ ይመለከታል። (1 ሳሙ. 16:7፤ ምሳሌ 21:2) ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎችን ወደ እውነተኛው አምልኮ ይስባቸዋል። (ዮሐ. 6:44) እንዲህ ካሉት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ስለ አምላክም ሆነ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ፈጽሞ አልተማሩም። አገልግሎታችን እነዚህ ሰዎች “እንዲድኑ እንዲሁም የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ” የሚያስችል አጋጣሚ ይፈጥርላቸዋል። (1 ጢሞ. 2:4) በመሆኑም አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ለሚያስተምራቸው ነገሮች መጀመሪያ ላይ ፍላጎት ባይኖራቸው ተስፋ አትቁረጡ! ፍላጎታቸውን ለመቀስቀስ በቋንቋችሁ የተዘጋጁ መሣሪያዎችን ተጠቀሙ። ከጊዜ በኋላ ውይይቱን ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? በተባለው መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጠናት በምንጠቀምበት ዋነኛ መጽሐፍ መቀጠል ትችሉ ይሆናል።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የቤቱ ባለቤት በአምላክ እንደማያምን ቢናገር እነዚህን ሐሳቦች ለመጠቀም ሞክር፦
• “እንዲህ የሚሰማህ ከልጅነትህ ጀምሮ ነው?” የሚል ጥያቄ በማንሳት ምክንያቱን ለማወቅ ሞክር።
• ቡድሂስት ከሆነ ደግሞ ላስቲንግ ፒስ ኤንድ ሃፒነስ—ሃው ቱ አቴይን ኢት በተባለው ብሮሹር ከገጽ 9-12 ወይም አምላክ ስለ እኛ በእርግጥ ያስባል? በተባለው ብሮሹር ከገጽ 4-9 ላይ ያሉ ሐሳቦችን ተጠቀም።
• በዝግመተ ለውጥ የሚያምን ከሆነ የሚከተሉት ጽሑፎች ሊረዱት ይችላሉ፦
“ንድፍ አውጪ አለው?” የሚለው ንቁ! ላይ የሚወጣው ተከታታይ ዓምድ
አስደናቂ የፍጥረት ሥራዎች የአምላክን ክብር ይገልጣሉ (እንግሊዝኛ) የተባለው ቪዲዮ
ብሮሹሮች፦ ኤ ሳትስፋይንግ ላይፍ—ሃው ቱ አቴይን ኢት ክፍል 4፤ ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው? እና የሕይወት አመጣጥ—መልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች
• በዓለም ላይ በሚታየው የፍትሕ መጓደልና መከራ ምክንያት በአምላክ ላይ ያለውን እምነት ያጣ ከሆነ የሚከተሉትን ጽሑፎች መጠቀም ጥሩ ነው፦
ኢዝ ዜር ኤ ክሪኤተር ሁ ኬርስ አባውት ዩ? የተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 10
ብሮሹሮች፦ አምላክ ስለ እኛ በእርግጥ ያስባልን? ክፍል 6 እና የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው? ክፍል 6
• የቤቱ ባለቤት ‘አምላክ ሳይኖር አይቀርም’ የሚል አመለካከት እንደያዘ ካስተዋልክ ጊዜ ሳታጠፋ ጥናቱን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በተባለው መጽሐፍ ለመቀጠል ጥረት አድርግ። ጥናቱን ከምዕራፍ 2 ወይም ለቤቱ ባለቤት ተስማሚ ነው ብለህ ከምታስበው ሌላ ርዕስ መጀመሩ የተሻለ ሊሆን ይችላል።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የቤቱ ባለቤት በመጽሐፍ ቅዱስ የማያምን ከሆነ የሚከተሉትን ጽሑፎች ለመጠቀም ሞክር፦
• መጻሕፍት፦ ላይፍ—ሃው ዲድ ኢት ጌት ሂር? ባይ ኢቮሉሽን ኦር ባይ ክሪኤሽን? ምዕራፍ 17 እና 18 ወይም መጽሐፍ ቅዱስ—የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? ምዕራፍ 8 እና 9 ወይም ለሰው ሁሉ የሚሆን መጽሐፍ የተባለውን ብሮሹር ከገጽ 14-17
• ለሂንዱዎች ኋይ ሹድ ዊ ዎርሺፕ ጎድ ኢን ላቭ ኤንድ ትሩዝ የተባለውን ብሮሹር ወይም ማመራመር መጽሐፍ ገጽ 22
• ለአይሁዳውያን ዊል ዜር ኤቨር ቢ ኤ ዎርልድ ዊዝአውት ዎር? የተባለውን ብሮሹር ከገጽ 3-11 ወይም ማመራመር መጽሐፍ ከገጽ 22-23
• የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች መከተል ያለውን ጥቅም አስረዳ። መጽሐፍ ቅዱስ ጠቃሚ መመሪያ እንደያዘ ለማስረዳት የሚከተሉትን ጽሑፎች መጠቀም ትችላለህ፦
ንቁ! ላይ የሚወጣው “ለቤተሰብ” የሚለው ተከታታይ ዓምድ
መጽሐፍ ቅዱስ—በአንተ ሕይወት ውስጥ ያለው ኃይል (እንግሊዝኛ) የተባለው ቪዲዮ
ብሮሹሮች፦ ከአምላክ የተላከ ምሥራች! ትምህርት 9 እና 11፤ ለሰው ሁሉ የሚሆን መጽሐፍ ከገጽ 22-26 እና ኤ ሳትስፋይንግ ላይፍ—ሃው ቱ አቴይን ኢት ክፍል 2
ለቡድሂስቶች ዘ ፓዝዌይ ቱ ፒስ ኤንድ ሃፒነስ የተባለውን ብሮሹር ከገጽ 3-7 ወይም ማመራመር ከገጽ 21-22
ለሙስሊሞች ሪል ፌይዝ—ዩር ኪ ቱ ኤ ሃፒ ላይፍ የተባለውን ብሮሹር ክፍል 3 ወይም ለሰው ሁሉ የሚሆን መጽሐፍ የተባለውን ብሮሹር ከገጽ 22-26፤ ማመራመር ከገጽ 23-24
የምትሰብከው፣ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጭፍን ጥላቻ ባለበት አካባቢ ከሆነ የምታካፍላቸው ጥበብ ያዘሉ ምክሮች ምንጭ ምን እንደሆነ መጀመሪያ ላይ አለመናገሩ የተሻለ ነው፤ በተደጋጋሚ ተመላልሶ መጠይቅ ካደረግህ በኋላ ይህንን ማድረግ ትችላለህ።
• የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ያገኙት እንዴት እንደሆነ ግለጽ። በዚህ ረገድ የሚከተሉት ጽሑፎች ይረዱሃል፦
መጽሐፍ ቅዱስ—የእውነትና የትንቢት መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) የተባለው ቪዲዮ
ለሰው ሁሉ የሚሆን መጽሐፍ የተባለው ብሮሹር ከገጽ 27-29
• ግለሰቡ በአንዳንድ ጉዳዮች ዙሪያ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚችል ጥያቄ ካነሳ ቶሎ ብለህ ጥናቱን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በተባለው መጽሐፍ ለመቀጠል ጥረት አድርግ።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የቤቱ ባለቤት “በአምላክ አላምንም” ቢልህ እንዲህ ማለት ትችላለህ፦
• “ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው ብዬ እንዳምን ያደረገኝ ምን እንደሆነ በአጭሩ ብነግርዎት ደስ ይለኛል።” ከዚያም ከማመራመር መጽሐፍ ገጽ 83-85 ላይ አንዳንድ ሐሳቦችን አካፍለው ወይም ጥሩ ሐሳብ ያገኘህበትን ጽሑፍ እንደምታመጣለት በመንገር ቀጠሮ ያዝ።
• “እንደው አምላክ ቢኖር ግን ምን ዓይነት ባሕርይ ያለው እንዲሆን ይፈልጋሉ?” ብዙ ሰዎች አፍቃሪ፣ ፍትሐዊ፣ መሐሪና የማያዳላ ወደ ሆነ አምላክ መቅረብ እንደሚቀላቸው ይናገራሉ። ከዚያም አምላክ እንዲህ ዓይነት ባሕርያት እንዳሉት ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አሳየው። (የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 1 ከአንቀጽ 6 ጀምሮ ያሉትን ሐሳቦች መጠቀም ይቻል ይሆናል።)
የቤቱ ባለቤት “በመጽሐፍ ቅዱስ አላምንም” ቢል እንዲህ ማለት ትችላለህ፦
• “እንዲህ ያለ አመለካከት ያላቸው ብዙ ሰዎች አሉ። አንዳንዶቹ መጽሐፍ ቅዱስ ከሳይንስ ጋር እንደሚጋጭ ወይም በውስጡ የሚገኙትን መመሪያዎች ተግባራዊ ማድረግ እንደማይቻል ይሰማቸዋል። ከዚህ በፊት መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ አጋጣሚ አግኝተው ነበር? [መልስ እንዲሰጥ ዕድል ስጠው። ከዚያም ለሰው ሁሉ የሚሆን መጽሐፍ በተባለው ብሮሹር ገጽ 3 ላይ ያለውን የመግቢያ ሐሳብ አሳየውና ብሮሹሩን አበርክትለት።] ሃይማኖቶች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት አዛብተው የሚያስተላልፉ መሆኑ ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ጠቃሚ እንደሆነ እንዳይሰማቸው አድርጓል። በሚቀጥለው ጊዜ ስመጣ በገጽ 4 እና 5 ላይ ያሉትን ይህን የሚያሳዩ ምሳሌዎችን እንወያይባቸዋለን።”
• “ብዙ ሰዎች የእርስዎ ዓይነት አመለካከት አላቸው። ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እኔን የሚያስገርመኝ ምን እንደሆነ ባሳይዎት ደስ ይለኛል። [መጽሐፍ ቅዱስ ከሳይንስ አንጻር ትክክል እንደሆነ የሚያሳዩትን ኢዮብ 26:7ን ወይም ኢሳይያስ 40:22ን አንብብ።] በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ደስተኛ የቤተሰብ ሕይወት እንዲኖረን የሚረዱ ጥበብ ያዘሉ ምክሮችን ይዟል። በሚቀጥለው ጊዜ በዚህ ዙሪያ አንድ ጥቅስ አሳይዎታለሁ።”
• “ሐሳብዎን ስለነገሩኝ በጣም አመሰግናለሁ። አምላክ ለሰው ልጆች መጽሐፍ ጽፎ ቢሆን ምን ነገሮች ያካትታል ብለው ያስባሉ?” ከዚያም እሱ ከሰጠው ሐሳብ ጋር የሚስማማ ጥቅስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንብብለት።