የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—ጥር 2019
ከጥር 7-13
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | የሐዋርያት ሥራ 21-22
“የይሖዋ ፈቃድ ይሁን”
(የሐዋርያት ሥራ 21:8-12) በማግስቱ ከዚያ ተነስተን ቂሳርያ ደረስን፤ በዚያም ከሰባቱ ወንዶች አንዱ ወደሆነው ወደ ወንጌላዊው ፊልጶስ ቤት ገብተን እሱ ጋ አረፍን። 9 ይህ ሰው ትንቢት የሚናገሩ አራት ያላገቡ ሴቶች ልጆች ነበሩት። 10 ለብዙ ቀናት እዚያ ከተቀመጥን በኋላ አጋቦስ የሚባል አንድ ነቢይ ከይሁዳ ወረደ። 11 ወደ እኛም መጥቶ የጳውሎስን ቀበቶ በመውሰድ የራሱን እግርና እጅ ካሰረ በኋላ እንዲህ አለ፦ “መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ ‘አይሁዳውያን የዚህን ቀበቶ ባለቤት በኢየሩሳሌም እንዲህ አድርገው ያስሩታል፤ ለአሕዛብም አሳልፈው ይሰጡታል።’” 12 ይህን ስንሰማ እኛም ሆንን በዚያ የነበሩት ደቀ መዛሙርት ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ እንለምነው ጀመር።
“የይሖዋ ፈቃድ ይሁን”
15 ጳውሎስ በፊልጶስ ቤት ባረፈበት ወቅት አጋቦስ የሚባል ሌላ የተከበረ እንግዳ መጣ። በፊልጶስ ቤት የተሰበሰቡት ሰዎች ሁሉ አጋቦስ ነቢይ መሆኑን ያውቃሉ፤ ደግሞም በቀላውዴዎስ የግዛት ዘመን ታላቅ ረሃብ እንደሚከሰት ተንብዮ ነበር። (ሥራ 11:27, 28) ሰዎቹ ‘አጋቦስ የመጣው ለምንድን ነው? ምን መልእክት ይዞ መጥቶ ይሆን?’ ብለው ሳያስቡ አይቀርም። ሁሉም በትኩረት እየተመለከቱት ሳለ የጳውሎስን መታጠቂያ ወሰደ፤ እዚህ ላይ የተጠቀሰው መታጠቂያ ገንዘብንና ሌሎች ዕቃዎችን ለመያዝ የሚያገለግል ወገብ ላይ የሚታሰር እንደ ቀበቶ ያለ ረጅም መቀነት ነው። አጋቦስ በመታጠቂያው የገዛ እግሮቹንና እጆቹን አሰረ። ከዚያም ይህን አስደንጋጭ መልእክት ተናገረ፦ “መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ ‘አይሁዳውያን የዚህን መታጠቂያ ባለቤት በኢየሩሳሌም እንዲህ አድርገው ያስሩታል፤ ለአሕዛብም አሳልፈው ይሰጡታል።’”—ሥራ 21:11
16 ትንቢቱ ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም መሄዱ የተቆረጠ ነገር መሆኑን የሚያመለክት ነበር። በተጨማሪም በዚያ ለሚገኙት አይሁዳውያን መስበኩ ‘ለአሕዛብ አልፎ’ እንዲሰጥ እንደሚያደርግ ይጠቁማል። ይህ ትንቢት በዚያ የነበሩትን ሁሉ ረበሻቸው። ሉቃስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ይህን ስንሰማ እኛም ሆንን በዚያ የሚኖሩት ደቀ መዛሙርት ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ እንለምነው ጀመር። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ‘እያለቀሳችሁ ለምን ልቤን ታባቡታላችሁ? እኔ ስለ ጌታ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመታሰር ብቻ ሳይሆን ለመሞትም እንኳ ዝግጁ መሆኔን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ’ ሲል መለሰ።”—ሥራ 21:12, 13
(የሐዋርያት ሥራ 21:13) በዚህ ጊዜ ጳውሎስ “እያለቀሳችሁ ልቤን ለምን ታባባላችሁ? እኔ ስለ ጌታ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመታሰር ብቻ ሳይሆን ለመሞትም እንኳ ዝግጁ ነኝ” ሲል መለሰ።
“የይሖዋ ፈቃድ ይሁን”
17 እስቲ ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። ሉቃስን ጨምሮ ሁሉም ወንድሞች ጳውሎስ ጉዞውን እንዳይቀጥል እየለመኑት ነው። እንዲያውም አንዳንዶቹ ያለቅሳሉ። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ባሳዩት ፍቅራዊ አሳቢነት የተነሳ ወንድሞች ‘ልቡን እንዳባቡት’ ተናገረ፤ አንዳንድ ትርጉሞች የግሪክኛውን አገላለጽ “ልቡን እንደሰበሩት” በማለት ተርጉመውታል። ጳውሎስ በጢሮስ ከወንድሞች ጋር በተገናኘ ጊዜ እንዳደረገው ሁሉ አሁንም ከአቋሙ ፍንክች አላለም፤ የእነሱ ልመናም ሆነ ለቅሶ ልቡ እንዲከፈል አላደረገም። ይልቁንም ጉዞውን መቀጠል ያለበት ለምን እንደሆነ አስረዳቸው። ያሳየው ድፍረትና ቆራጥነት እጅግ ይደነቃል! ከእሱ በፊት ኢየሱስ እንዳደረገው ሁሉ ጳውሎስም ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ቆርጦ ተነስቷል። (ዕብ 12:2) ጳውሎስ ሰማዕት የመሆን ፍላጎት የለውም፤ ሆኖም ይህ የማይቀር ከሆነ የክርስቶስ ኢየሱስ ተከታይ ሆኖ መሞቱን እንደ ክብር ይቆጥረዋል።
(የሐዋርያት ሥራ 21:14) እሱን ለማሳመን ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ በመቅረቱ “እንግዲህ የይሖዋ ፈቃድ ይሁን” ብለን ዝም አልን።
“የይሖዋ ፈቃድ ይሁን”
18 የወንድሞች ምላሽ ምን ነበር? በአጭሩ፣ ሐሳቡን አክብረውለታል ማለት ይቻላል። ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “ምክራችንን ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆን በመቅረቱ ‘እንግዲህ የይሖዋ ፈቃድ ይሁን’ ብለን ተውነው።” (ሥራ 21:14) ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄድ ለማሳመን የጣሩት ወንድሞች ሐሳባቸውን እንዲቀበል አላስገደዱትም። ሁኔታው ከባድ ቢሆንባቸውም የይሖዋን ፈቃድ በመገንዘብና በመቀበል የጳውሎስን ሐሳብ ያዳመጡ ከመሆኑም ሌላ በሐሳቡ ተስማምተዋል። ጳውሎስ የኋላ ኋላ ለሞት በሚዳርገው ጎዳና ላይ መጓዝ ጀምሯል። ወንድሞች እሱን ለማግባባት ጥረት ማድረጋቸውን ካቆሙ ጳውሎስ ሁኔታውን መቀበል ይቀለዋል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(የሐዋርያት ሥራ 21:23, 24) ስለዚህ አሁን የምንነግርህን ነገር አድርግ፦ ስእለት ያለባቸው አራት ሰዎች በእኛ ዘንድ አሉ። 24 እነዚህን ሰዎች ይዘህ በመሄድ ከእነሱ ጋር የመንጻት ሥርዓት ፈጽም፤ ራሳቸውንም እንዲላጩ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ክፈልላቸው። ይህን ካደረግክ በአንተ ላይ የተወራው ሁሉ ከንቱ መሆኑንና አንተም ሕጉን እያከበርክ በሥርዓት እንደምትኖር ሁሉም ሰው ያውቃል።
“የማቀርበውን የመከላከያ መልስ ስሙ”
10 ይሁን እንጂ ጳውሎስ በሰንበት ሥራ ከመሥራት እንደ መቆጠብና አንዳንድ ምግቦችን ከመብላት እንደ መራቅ ያሉ የአይሁዳውያን ልማዶችን ለመከተል የመረጡ ክርስቲያኖችን ስሜት ተረድቷል። (ሮም 14:1-6) ግርዘትን በተመለከተም ያወጣው ደንብ የለም። እርግጥ ጳውሎስ የጢሞቴዎስ አባት ግሪካዊ ስለሆነ አይሁዳውያን ጢሞቴዎስን በጥርጣሬ እንዳያዩት ሲል ገርዞታል። (ሥራ 16:3) ግርዘት ለግለሰቦች ምርጫ የተተወ ጉዳይ ነበር። ጳውሎስ የገላትያ ክርስቲያኖችን “ጠቃሚ የሆነው፣ በፍቅር የሚመራ እምነት እንጂ መገረዝ ወይም አለመገረዝ አይደለም” ብሏቸዋል። (ገላ. 5:6) ይሁንና በሕጉ ሥር ለመሆን ሲባል መገረዝ ወይም በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ግርዘት አስፈላጊ እንደሆነ አድርጎ ማቅረብ እምነት ማጣትን ያሳያል።
11 በጳውሎስ ላይ የተወራው ነገር ትክክል ባይሆንም አይሁዳውያን ክርስቲያኖች አሁንም በሰሙት ነገር እንደተረበሹ ናቸው። በመሆኑም ሽማግሌዎቹ እንዲህ የሚል ምክር ሰጡት፦ “ስእለት ያለባቸው አራት ሰዎች በእኛ ዘንድ አሉ። እነዚህን ሰዎች ይዘህ በመሄድ ከእነሱ ጋር የመንጻት ሥርዓት ፈጽም፤ ራሳቸውንም እንዲላጩ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ክፈልላቸው። ይህን ብታደርግ በአንተ ላይ የተወራው ሁሉ ከንቱ መሆኑንና አንተም ራስህ ሕጉን እያከበርክ በሥርዓት እንደምትኖር ሁሉም ሰው ያውቃል።”—ሥራ 21:23, 24
12 ጳውሎስ የችግሩ ዋና መንስኤ ስለ እሱ የተወራው አሉባልታ ሳይሆን አይሁዳውያን አማኞች ለሙሴ ሕግ ያላቸው ቅንዓት ነው ብሎ መቃወም ይችል ነበር። ይሁን እንጂ አምላክ ያወጣቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች እስካልጣሰ ድረስ ሽማግሌዎቹ ያሉትን ለማድረግ ፈቃደኛ ነበር። ጳውሎስ ቀደም ሲል “እኔ ራሴ በሕግ ሥር ባልሆንም እንኳ በሕግ ሥር ያሉትን እማርክ ዘንድ በሕግ ሥር ላሉት በሕግ ሥር እንዳለሁ ሆንኩ” በማለት ጽፎ ነበር። (1 ቆሮ. 9:20) በዚህ ወቅት ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ከነበሩ ሽማግሌዎች ጋር በመተባበር “በሕግ ሥር” እንዳለ ሆኗል። በዚህ መንገድ ጳውሎስ፣ ከሽማግሌዎች ጋር በመተባበርና እኔ ያልኩት ካልሆነ ብሎ ድርቅ ከማለት በመቆጠብ ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል።—ዕብ. 13:17
(የሐዋርያት ሥራ 22:16) ታዲያ አሁን ምን ትጠብቃለህ? ተነስና ተጠመቅ፤ ስሙንም እየጠራህ ኃጢአትህን ታጠብ።’
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ሥራ 22:16
ስሙንም እየጠራህ ኃጢአትህን ታጠብ፦ ወይም “ኃጢአትህን ታጠብ እንዲሁም ስሙን ጥራ።” አንድ ሰው ኃጢአቱ እንዲታጠብ የሚያደርገው የሚጠመቅበት ውኃ ሳይሆን የኢየሱስን ስም መጥራቱ ነው። የኢየሱስን ስም መጥራት ሲባል በኢየሱስ ማመንን እንዲሁም ክርስቲያናዊ ሥራዎችን በማከናወን ይህን እምነት በተግባር ማሳየትን ያካትታል።—ሥራ 10:43፤ ያዕ 2:14, 18
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(የሐዋርያት ሥራ 21:1-19) ከእነሱ በግድ ከተለያየን በኋላ በመርከብ ተሳፍረን በቀጥታ በመጓዝ ቆስ ደረስን፤ በማግስቱ ደግሞ ወደ ሮድስ አመራን፤ ከዚያም ወደ ጳጥራ ሄድን። 2 ወደ ፊንቄ የሚሻገር መርከብ ባገኘን ጊዜ ተሳፍረን ጉዟችንን ቀጠልን። 3 የቆጵሮስ ደሴት በታየችን ጊዜ በስተ ግራ ትተናት ወደ ሶርያ አመራን፤ መርከቡ ጭነቱን በጢሮስ ማራገፍ ስለነበረበት እኛም እዚያ ወረድን። 4 ደቀ መዛሙርቱን ፈልገን ካገኘን በኋላ በዚያ ሰባት ቀን ቆየን። እነሱም በመንፈስ ተመርተው ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄድ ደጋግመው ነገሩት። 5 የቆይታ ጊዜያችን ባለቀ ጊዜ ከዚያ ተነስተን ጉዟችንን ጀመርን፤ ሴቶችንና ልጆችን ጨምሮ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ከከተማዋ እስክንወጣ ድረስ ሸኙን። ከዚያም በባሕሩ ዳርቻ ተንበርክከን ጸለይን፤ 6 በኋላም ተሰነባበትን። ከዚያም እኛ ወደ መርከቡ ገባን፤ እነሱ ደግሞ ወደ ቤታቸው ተመለሱ። 7 ከጢሮስ ተነስተን በመርከብ በመጓዝ ጴጤሌማይስ ደረስን፤ እዚያም ለወንድሞች ሰላምታ ካቀረብን በኋላ አብረናቸው አንድ ቀን ቆየን። 8 በማግስቱ ከዚያ ተነስተን ቂሳርያ ደረስን፤ በዚያም ከሰባቱ ወንዶች አንዱ ወደሆነው ወደ ወንጌላዊው ፊልጶስ ቤት ገብተን እሱ ጋ አረፍን። 9 ይህ ሰው ትንቢት የሚናገሩ አራት ያላገቡ ሴቶች ልጆች ነበሩት። 10 ለብዙ ቀናት እዚያ ከተቀመጥን በኋላ አጋቦስ የሚባል አንድ ነቢይ ከይሁዳ ወረደ። 11 ወደ እኛም መጥቶ የጳውሎስን ቀበቶ በመውሰድ የራሱን እግርና እጅ ካሰረ በኋላ እንዲህ አለ፦ “መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ ‘አይሁዳውያን የዚህን ቀበቶ ባለቤት በኢየሩሳሌም እንዲህ አድርገው ያስሩታል፤ ለአሕዛብም አሳልፈው ይሰጡታል።’” 12 ይህን ስንሰማ እኛም ሆንን በዚያ የነበሩት ደቀ መዛሙርት ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ እንለምነው ጀመር። 13 በዚህ ጊዜ ጳውሎስ “እያለቀሳችሁ ልቤን ለምን ታባባላችሁ? እኔ ስለ ጌታ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመታሰር ብቻ ሳይሆን ለመሞትም እንኳ ዝግጁ ነኝ” ሲል መለሰ። 14 እሱን ለማሳመን ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ በመቅረቱ “እንግዲህ የይሖዋ ፈቃድ ይሁን” ብለን ዝም አልን። 15 ከዚህ በኋላ ለጉዞው ተዘጋጅተን ወደ ኢየሩሳሌም መጓዝ ጀመርን። 16 በቂሳርያ ከሚኖሩት ደቀ መዛሙርት አንዳንዶቹ ወደምናርፍበት ሰው ቤት እኛን ለመውሰድ አብረውን ሄዱ፤ ይህ ሰው ምናሶን የተባለ የቆጵሮስ ሰው ሲሆን ከቀድሞዎቹ ደቀ መዛሙርት አንዱ ነበር። 17 ኢየሩሳሌም በደረስን ጊዜ ወንድሞች በደስታ ተቀበሉን። 18 በማግስቱም ጳውሎስ ከእኛ ጋር ወደ ያዕቆብ ሄደ፤ ሽማግሌዎቹም ሁሉ በዚያ ነበሩ። 19 ሰላምታ ካቀረበላቸውም በኋላ፣ እሱ ባከናወነው አገልግሎት አማካኝነት አምላክ በአሕዛብ መካከል የፈጸማቸውን ነገሮች በዝርዝር ይተርክላቸው ጀመር።
ከጥር 14-20
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | የሐዋርያት ሥራ 23-24
“ዓመፅ አነሳሽና መቅሰፍት ተብሎ ተከሰሰ”
(የሐዋርያት ሥራ 23:12) በነጋም ጊዜ አይሁዳውያን በጳውሎስ ላይ በማሴር እሱን እስኪገድሉ ድረስ እህል ውኃ ላለመቅመስ ተማማሉ።
(የሐዋርያት ሥራ 23:16) ይሁን እንጂ የጳውሎስ የእህቱ ልጅ አድብተው ጥቃት ለመሰንዘር እንዳሰቡ በመስማቱ ወደ ጦር ሰፈሩ ገብቶ ጉዳዩን ለጳውሎስ ነገረው።
“አይዞህ፣ አትፍራ!”
5 ጳውሎስ ያገኘው ማበረታቻ ወቅታዊ ነበር። በሚቀጥለው ቀን ከ40 በላይ የሚሆኑ አይሁዳውያን ወንዶች “በጳውሎስ ላይ በማሴር እሱን እስኪገድሉ ድረስ እህል ውኃ የሚባል ነገር ላለመቅመስ ተማማሉ።” እነዚህ አይሁዳውያን ‘ሴራ ለመፈጸም መማማላቸው’ ሐዋርያውን ለመግደል ምን ያህል ቆርጠው እንደተነሱ ያሳያል። ሴራቸውን ተግባራዊ ማድረግ ካቃታቸው እርግማን ወይም ክፉ ነገር እንደሚደርስባቸው ተሰምቷቸው ነበር። (ሥራ 23:12-15) የሰዎቹ ዕቅድ አንዳንድ ጉዳዮችን በትክክል ማጣራት የፈለጉ በማስመሰል ጳውሎስ ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግበት በድጋሚ ወደ ሳንሄድሪን እንዲመጣ ማድረግ ነበር፤ ዕቅዱ የካህናት አለቆቹንና የሽማግሌዎቹን ይሁንታ አግኝቶ ነበር። ጳውሎስ እዚያ ከመድረሱ በፊት ግን የሴራው ጠንሳሾች ጥቃት ሰንዝረው እሱን ለመግደል መንገድ ላይ አድፍጠው ይጠባበቃሉ።
6 ይሁን እንጂ የጳውሎስ እህት ልጅ ስለዚህ ሴራ ሲሰማ ጉዳዩን ለጳውሎስ ነገረው። ጳውሎስ ደግሞ ይህ ወጣት ሁኔታውን ለሮማዊው ሻለቃ ለቀላውዴዎስ ሉስዮስ እንዲነግረው አደረገ። (ሥራ 23:16-22) በስም ያልተጠቀሰው ይህ የጳውሎስ እህት ልጅ እንዳደረገው ሁሉ ከራሳቸው ይልቅ የአምላክን ሕዝቦች ደህንነት የሚያስቀድሙና የመንግሥቱን ጉዳዮች ለማራመድ በታማኝነት የሚችሉትን ሁሉ የሚያደርጉ ደፋር ወጣቶችን ይሖዋ እንደሚወዳቸው ምንም ጥርጥር የለውም።
(የሐዋርያት ሥራ 24:2) በተጠራም ጊዜ ጠርጡለስ እንዲህ ሲል ይከሰው ጀመር፦ “ክቡር ፊሊክስ ሆይ፣ በአንተ አማካኝነት ብዙ ሰላም አግኝተናል፤ አስተዋይነትህም ለዚህ ሕዝብ መሻሻል አስገኝቷል፤
(የሐዋርያት ሥራ 24:5, 6) ይህ ሰው መቅሰፍት ሆኖብናል፤ በዓለም ባሉት አይሁዳውያን ሁሉ መካከል ዓመፅ ያነሳሳል፤ ከዚህም ሌላ የናዝሬታውያን ኑፋቄ ቀንደኛ መሪ ነው። 6 በዚህ ላይ ደግሞ ቤተ መቅደሱን ለማርከስ ሲሞክር ስላገኘነው ያዝነው።
“አይዞህ፣ አትፍራ!”
10 ጳውሎስ ከሳሾቹ ከኢየሩሳሌም እስኪመጡ ድረስ በቂሳርያ ባለው “በሄሮድስ ቤተ መንግሥት ውስጥ በጥበቃ ሥር ሆኖ እንዲቆይ” ተደረገ። (ሥራ 23:35) ከአምስት ቀን በኋላ ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ፣ ጠርጡለስ የሚባል ጠበቃና የተወሰኑ ሽማግሌዎች መጡ። ጠርጡለስ በመጀመሪያ፣ ፊሊክስ ለአይሁዳውያን እያከናወነ ላለው ሥራ ምስጋና አቀረበ፤ ይህን ያደረገው እሱን ለመሸንገልና በእሱ ለመወደድ ብሎ እንደሆነ ግልጽ ነው። ከዚያም ጠርጡለስ ወደ ጉዳዩ በመግባት “ይህ ሰው መቅሰፍት ሆኖብናል፤ በዓለም ባሉት አይሁዳውያን ሁሉ መካከል ዓመፅ ያነሳሳል፤ ከዚህም ሌላ የናዝሬታውያን ኑፋቄ ቀንደኛ መሪ ነው፤ በዚህ ላይ ደግሞ ቤተ መቅደሱን ለማርከስ ሲሞክር አግኝተን ይዘነዋል” ሲል ጳውሎስን ወነጀለው። የተቀሩት አይሁዳውያንም “የተባለው ነገር ሁሉ ትክክል መሆኑን በመግለጽ በውንጀላው ተባበሩ።” (ሥራ 24:5, 6, 9) ዓመፅ ማነሳሳት፣ የአንድ አደገኛ ኑፋቄ ቀንደኛ መሪ መሆንና ቤተ መቅደሱን ማርከስ የሞት ፍርድ ሊያስበይኑ የሚችሉ ከባድ ክሶች ናቸው።
(የሐዋርያት ሥራ 24:10-21) አገረ ገዢውም እንዲናገር በጭንቅላቱ ምልክት በሰጠው ጊዜ ጳውሎስ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ለብዙ ዓመታት ለዚህ ሕዝብ ፈራጅ ሆነህ ስታገለግል መቆየትህን አውቃለሁ፤ በመሆኑም ስለ ራሴ የመከላከያ መልስ የማቀርበው በደስታ ነው። 11 ለአምልኮ ወደ ኢየሩሳሌም ከወጣሁ ከ12 ቀን እንደማይበልጥ አንተው ራስህ ማረጋገጥ ትችላለህ፤ 12 እንዲሁም በቤተ መቅደሱ ከማንም ጋር ስከራከርም ሆነ በምኩራቦች ወይም በከተማው ውስጥ ሕዝቡን ለዓመፅ ሳነሳሳ አላገኙኝም። 13 በተጨማሪም አሁን ላቀረቡብኝ ክስ ሁሉ ምንም ማስረጃ ሊያቀርቡልህ አይችሉም። 14 ይሁን እንጂ በሕጉና በነቢያት የተጻፉትን ነገሮች ሁሉ ስለማምን እነሱ ኑፋቄ ብለው የሚጠሩትን የሕይወት መንገድ እንደምከተልና በዚህም መንገድ ለአባቶቼ አምላክ ቅዱስ አገልግሎት እንደማቀርብ አልክድም። 15 ደግሞም እነዚህ ሰዎች ራሳቸው ተስፋ እንደሚያደርጉት ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች ከሞት እንደሚነሱ በአምላክ ተስፋ አደርጋለሁ። 16 በዚህ የተነሳ በአምላክም ሆነ በሰው ፊት ንጹሕ ሕሊና ይዤ ለመኖር ሁልጊዜ ጥረት አደርጋለሁ። 17 ከብዙ ዓመታት በኋላም ለወገኖቼ ምጽዋት ለመስጠትና ለአምላክ መባ ለማቅረብ መጣሁ። 18 በቤተ መቅደሱ ውስጥ ያገኙኝ የመንጻት ሥርዓት ፈጽሜ ይህንኑ ሳደርግ እንጂ ከብዙ ሕዝብ ጋር ሆኜ ሁከት ሳነሳሳ አልነበረም። ሆኖም ከእስያ አውራጃ የመጡ አንዳንድ አይሁዳውያን ነበሩ፤ 19 እነሱ እኔን የሚከሱበት ነገር ካላቸው እዚህ ፊትህ ተገኝተው ሊከሱኝ ይገባ ነበር። 20 ወይም እዚህ ያሉት ሰዎች በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት በቀረብኩበት ጊዜ ያገኙብኝ ጥፋት ካለ እነሱ ራሳቸው ይናገሩ፤ 21 በመካከላቸው ቆሜ በነበረበት ጊዜ ድምፄን ከፍ አድርጌ ‘ዛሬ በፊታችሁ ለፍርድ የቀረብኩት በሙታን ትንሣኤ በማመኔ ነው!’ ብዬ ከመናገር በቀር ያደረግኩት ነገር የለም።”
“አይዞህ፣ አትፍራ!”
13 እኛም ከአምልኮታችን ጋር በተያያዘ የመንግሥት ባለሥልጣናት ፊት እንድንቀርብ ቢደረግና ችግር ፈጣሪዎች፣ ዓመፅ ቆስቋሾች ወይም “የአደገኛ ኑፋቄ” አባላት እንደሆንን ተደርጎ የሐሰት ክስ ቢሰነዘርብን ጳውሎስ የተወልንን ግሩም ምሳሌ መከተል እንችላለን። ጳውሎስ፣ ጠርጡለስ እንዳደረገው የሽንገላ ቃላት በመናገር በአገረ ገዢው ዘንድ ለመወደድ አልሞከረም። ጳውሎስ የመረጋጋት መንፈስ ነበረው፤ ደግሞም አክብሮት አሳይቷል። ሐቁን በግልጽ የተናገረ ከመሆኑም በላይ ማስረጃዎቹን በጥበብ አቅርቧል። ጳውሎስ ቤተ መቅደሱን አርክሷል ብለው የከሰሱት “ከእስያ አውራጃ የመጡ አንዳንድ አይሁዳውያን” በዚህ ችሎት ፊት አለመቅረባቸውን እንዲሁም ከሕግ አኳያ እነሱን ፊት ለፊት የመጋፈጥና ክሳቸውን የመስማት አጋጣሚ ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቅሷል።—ሥራ 24:18, 19
14 ከሁሉ በላይ ደግሞ ጳውሎስ ስለሚያምንባቸው ነገሮች ምሥክርነት ከመስጠት ወደኋላ አላለም። ሐዋርያው ሳንሄድሪን ፊት በቀረበበት ወቅት ከፍተኛ ሁከት እንዲነሳ ያደረገውን ጉዳይ ይኸውም በትንሣኤ ላይ ያለውን እምነት በድጋሚ በድፍረት ተናግሯል። (ሥራ 23:6-10) ጳውሎስ የመከላከያ መልስ ሲሰጥ የትንሣኤን ተስፋ ጎላ አድርጎ ገልጿል። ለምን? ይህን ያደረገው ስለ ኢየሱስና እሱ ከሞት ስለመነሳቱ ምሥክርነት እየሰጠ ስለነበረ ነው፤ ይህ ደግሞ ተቃዋሚዎቹ የማይቀበሉት ጉዳይ ነው። (ሥራ 26:6-8, 22, 23) አዎ፣ ይህ አወዛጋቢ ጉዳይ ከትንሣኤ በተለይ ደግሞ በኢየሱስና በእሱ ትንሣኤ ከማመን ጋር የተያያዘ ነበር።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(የሐዋርያት ሥራ 23:6) ጳውሎስ ግማሾቹ ሰዱቃውያን ግማሾቹ ደግሞ ፈሪሳውያን መሆናቸውን ስላወቀ በሳንሄድሪን ሸንጎ ውስጥ ድምፁን ከፍ አድርጎ “ወንድሞች፣ እኔ ከፈሪሳውያን የተወለድኩ ፈሪሳዊ ነኝ። ለፍርድ የቀረብኩት በሙታን ትንሣኤ ተስፋ በማመኔ ነው” ሲል ተናገረ።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ሥራ 23:6
ፈሪሳዊ ነኝ፦ ጳውሎስን ያዳምጡት ከነበሩት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ስለ እሱ ያውቁ ነበር። (ሥራ 22:5) እነዚህ ሰዎች፣ ጳውሎስ ከፈሪሳውያን የተወለደ መሆኑን የተናገረው፣ ቀደም ሲል እሱም ፈሪሳዊ እንደነበረ እንዲሁም ልክ እንደ እነሱ በትንሣኤ እንደሚያምን ለመግለጽ እንደሆነ ሳይገነዘቡ አይቀሩም። ጳውሎስ ፈሪሳዊ መሆኑን ሲገልጽ ያልሆነውን መስሎ ለመታየት እየሞከረ እንዳልነበረ የሳንሄድሪን አባላት የሆኑት ፈሪሳውያን ገብቷቸው ነበር፤ እነዚህ ሰዎች ጳውሎስ ቀናተኛ ክርስቲያን መሆኑን በሚገባ ያውቃሉ። ይሁንና እዚህ ጥቅስ ላይ ጳውሎስ ፈሪሳዊ መሆኑን የገለጸው ከሰዱቃውያን ይልቅ ከፈሪሳውያን ጋር የሚስማማበት ነገር እንዳለ ለማሳየት ይመስላል፤ ፈሪሳውያንም እንደ ጳውሎስ በትንሣኤ ያምናሉ። ይህም በቦታው ከነበሩት ፈሪሳውያን ጋር የሚያግባባው መሠረት ለመጣል አስችሎታል። ጳውሎስ ይህን አወዛጋቢ ርዕስ ያነሳው ከሳንሄድሪን አባላት አንዳንዶቹ እሱ ባቀረበው ሐሳብ እንዲስማሙ ሊያደርግ እንደሚችል አስቦ ሊሆን ይችላል፤ ደግሞም ያሰበው ተሳክቶለታል። (ሥራ 23:7-9) ጳውሎስ በሥራ 23:6 ላይ ራሱን የገለጸበት መንገድ፣ ከጊዜ በኋላ በንጉሥ አግሪጳ ፊት ስለ ራሱ መከላከያ ሲያቀርብ ከተናገረው ሐሳብ ጋርም ይስማማል። (ሥራ 26:5) በተጨማሪም በፊልጵስዩስ ለነበሩት የእምነት ባልንጀሮቹ ከሮም በጻፈው ደብዳቤ ላይ ፈሪሳዊ እንደነበረ ገልጿል። (ፊልጵ 3:5) ቀደም ሲል ፈሪሳዊ የነበሩ ሌሎች ክርስቲያኖች በሥራ 15:5 ላይ የተገለጹበት መንገድም ትኩረት የሚስብ ነው።
(የሐዋርያት ሥራ 24:24) ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ፊሊክስ አይሁዳዊት ከሆነችው ሚስቱ ከድሩሲላ ጋር መጣ፤ ጳውሎስንም አስጠርቶ በክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ማመን ሲናገር አዳመጠው።
(የሐዋርያት ሥራ 24:27) ይሁንና ሁለት ዓመት ካለፈ በኋላ ፊሊክስ በጶርቅዮስ ፊስጦስ ተተካ፤ በዚህ ጊዜ ፊሊክስ በአይሁዳውያን ዘንድ ተወዳጅነት ማትረፍ ስለፈለገ ጳውሎስን እንደታሰረ ተወው።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ሥራ 24:24
ድሩሲላ፦ በሥራ 12:1 ላይ የተጠቀሰው የቀዳማዊ ሄሮድስ አግሪጳ ሦስተኛና የመጨረሻ ሴት ልጅ ናት። ድሩሲላ የተወለደችው በ38 ዓ.ም. ገደማ ሲሆን የዳግማዊ አግሪጳና የበርኒቄ እህት ናት። (ከቃላት መፍቻው ላይ “ሄሮድስ” የሚለውን ተመልከት።) አገረ ገዢው ፊሊክስ ለድሩሲላ ሁለተኛ ባሏ ነው። የመጀመሪያ ባሏ የኤሜሳ ንጉሥ የሆነው ሶርያዊው አዚዘስ ነበር፤ ሆኖም እሱን ፈትታ በ54 ዓ.ም. ገደማ በ16 ዓመቷ ፊሊክስን አገባች። ጳውሎስ “ስለ ጽድቅ፣ ራስን ስለ መግዛትና ስለሚመጣው ፍርድ” ለፊሊክስ በተናገረበት ወቅት ድሩሲላ በቦታው ተገኝታ ሊሆን ይችላል። (ሥራ 24:25) ፊሊክስ ሥልጣኑን ለፊስጦስ ሲያስረክብ “በአይሁዳውያን ዘንድ ተወዳጅነት ማትረፍ ስለፈለገ” ጳውሎስን እንደታሰረ ተወው፤ አንዳንዶች ይህን ያደረገው አይሁዳዊት የሆነችውን ወጣት ሚስቱን ለማስደሰት ብሎ እንደሆነ ይናገራሉ።—ሥራ 24:27
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(የሐዋርያት ሥራ 23:1-15) ጳውሎስ የሳንሄድሪንን ሸንጎ ትኩር ብሎ እየተመለከተ “ወንድሞች፣ እኔ እስከዚህ ቀን ድረስ በአምላክ ፊት ሙሉ በሙሉ ንጹሕ ሕሊና ይዤ ተመላልሻለሁ” አለ። 2 በዚህ ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ፣ ጳውሎስ አጠገብ የቆሙት ሰዎች አፉን እንዲመቱት አዘዘ። 3 ጳውሎስም “አንተ በኖራ የተለሰንክ ግድግዳ! አምላክ አንተን ይመታሃል። በሕጉ መሠረት በእኔ ላይ ለመፍረድ ተቀምጠህ ሳለ አንተ ራስህ ሕጉን በመጣስ እንድመታ ታዛለህ?” አለው። 4 አጠገቡ የቆሙትም “የአምላክን ሊቀ ካህናት ትሳደባለህ?” አሉት። 5 ጳውሎስም “ወንድሞች፣ እኔ እኮ ሊቀ ካህናት መሆኑን አላወቅኩም። ምክንያቱም ‘በሕዝብህ ገዢ ላይ ክፉ ቃል አትናገር’ ተብሎ ተጽፏል” አላቸው። 6 ጳውሎስ ግማሾቹ ሰዱቃውያን ግማሾቹ ደግሞ ፈሪሳውያን መሆናቸውን ስላወቀ በሳንሄድሪን ሸንጎ ውስጥ ድምፁን ከፍ አድርጎ “ወንድሞች፣ እኔ ከፈሪሳውያን የተወለድኩ ፈሪሳዊ ነኝ። ለፍርድ የቀረብኩት በሙታን ትንሣኤ ተስፋ በማመኔ ነው” ሲል ተናገረ። 7 ይህን በመናገሩ በፈሪሳውያንና በሰዱቃውያን መካከል ግጭት ተፈጥሮ ጉባኤው ለሁለት ተከፈለ። 8 ምክንያቱም ሰዱቃውያን ትንሣኤም፣ መልአክም፣ መንፈሳዊ ፍጥረታትም የሉም ይሉ የነበረ ሲሆን ፈሪሳውያን ግን በእነዚህ ነገሮች ያምኑ ነበር። 9 ስለዚህ ከፍተኛ ሁከት ተፈጠረ፤ ከፈሪሳውያን ወገን የሆኑ አንዳንድ ጸሐፍት ተነስተው እንዲህ ሲሉ አጥብቀው ተከራከሩ፦ “በዚህ ሰው ላይ ምንም ጥፋት አላገኘንም፤ መንፈስ ወይም መልአክ አናግሮት ከሆነ ግን . . . ።” 10 በመካከላቸው የተፈጠረው ግጭት እየከረረ ሲሄድ የሠራዊቱ ሻለቃ ጳውሎስን እንዳይገነጣጥሉት ፈርቶ ወታደሮቹ ወርደው ከመካከላቸው ነጥቀው እንዲያመጡትና ወደ ጦር ሰፈሩ እንዲያስገቡት አዘዘ። 11 ሆኖም በዚያኑ ዕለት ሌሊት ጌታ በጳውሎስ አጠገብ ቆሞ እንዲህ አለው፦ “አይዞህ፣ አትፍራ! ምክንያቱም በኢየሩሳሌም ስለ እኔ በሚገባ እንደመሠከርክ ሁሉ በሮምም ልትመሠክርልኝ ይገባል።” 12 በነጋም ጊዜ አይሁዳውያን በጳውሎስ ላይ በማሴር እሱን እስኪገድሉ ድረስ እህል ውኃ ላለመቅመስ ተማማሉ። 13 ይህን ሴራ ለመፈጸም የተማማሉት ሰዎች ቁጥራቸው ከ40 በላይ ነበር። 14 እነሱም ወደ ካህናት አለቆቹና ወደ ሽማግሌዎቹ ሄደው እንዲህ አሉ፦ “ጳውሎስን እስክንገድል ድረስ አንዳች እህል ላለመቅመስ ጽኑ መሐላ ተማምለናል። 15 ስለዚህ እናንተ ከሳንሄድሪን ሸንጎ ጋር ሆናችሁ የጳውሎስን ጉዳይ ይበልጥ ማጣራት የምትፈልጉ በማስመሰል እሱን ወደ እናንተ እንዲያመጣው ለሠራዊቱ ሻለቃ ንገሩት። ይሁንና እኛ እዚህ ከመድረሱ በፊት እሱን ለመግደል ተዘጋጅተን እንጠብቃለን።”
ከጥር 21-27
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | የሐዋርያት ሥራ 25-26
“ጳውሎስ ወደ ቄሳር ይግባኝ አለ፤ ከዚያም ለንጉሥ ሄሮድስ አግሪጳ መሠከረ”
(የሐዋርያት ሥራ 25:11) በእርግጥ ጥፋተኛ ሆኜ ከተገኘሁና ለሞት የሚያበቃ ነገር ፈጽሜ ከሆነ ከሞት ልዳን አልልም፤ እነዚህ ሰዎች ያቀረቡብኝ ክስ ሁሉ መሠረተ ቢስ ከሆነ ግን እነሱን ለማስደሰት ብሎ ማንም ሰው እኔን ለእነሱ አሳልፎ የመስጠት መብት የለውም። ወደ ቄሳር ይግባኝ ብያለሁ!”
“ወደ ቄሳር ይግባኝ ብያለሁ!”
6 ፊስጦስ አይሁዳውያኑን ለማስደሰት የነበረው ፍላጎት ጳውሎስን ለሞት ሊዳርገው ይችላል። ስለዚህ ጳውሎስ የሮም ዜጋ መሆኑ ባስገኘለት መብት ለመጠቀም መረጠ። ፊስጦስን እንዲህ አለው፦ “እኔ ልዳኝበት በሚገባኝ በቄሳር የፍርድ ወንበር ፊት ቆሜያለሁ። አንተ ራስህ በሚገባ እንደደረስክበት በአይሁዳውያን ላይ የፈጸምኩት ምንም በደል የለም። . . . ወደ ቄሳር ይግባኝ ብያለሁ!” አንዴ ይግባኝ ከተባለ ደግሞ በአብዛኛው ሐሳብን መቀየር አይቻልም። ፊስጦስ “ወደ ቄሳር ይግባኝ ስላልክ ወደ ቄሳር ትሄዳለህ” የሚል መልስ መስጠቱ ይህን ጎላ አድርጎ ያሳያል። (ሥራ 25:10-12) ጳውሎስ ለከፍተኛ የሕግ አካል ይግባኝ ማለቱ ዛሬ ላሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች አርዓያ ሆኖ ያገለግላል። ተቃዋሚዎች “በሕግ ስም ችግር” ለመፍጠር ጥረት በሚያደርጉበት ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ለምሥራቹ ጥብቅና ለመቆም ሲሉ ሕጉ በሚሰጣቸው መብቶች ይጠቀማሉ።—መዝ. 94:20 NW
(የሐዋርያት ሥራ 26:1-3) አግሪጳ ጳውሎስን “ስለ ራስህ እንድትናገር ተፈቅዶልሃል” አለው። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ እጁን ዘርግቶ እንዲህ ሲል የመከላከያ መልሱን ይሰጥ ጀመር፦ 2 “ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፣ አይሁዳውያን በእኔ ላይ ያቀረቡትን ክስ ሁሉ በተመለከተ ዛሬ በአንተ ፊት የመከላከያ መልስ መስጠት በመቻሌ እጅግ ደስተኛ ነኝ፤ 3 በተለይ ደግሞ አንተ የአይሁዳውያንን ልማዶችና በመካከላቸው ያሉትን ክርክሮች ሁሉ ጠንቅቀህ ታውቃለህ። ስለዚህ በትዕግሥት እንድታዳምጠኝ እለምንሃለሁ።
“ወደ ቄሳር ይግባኝ ብያለሁ!”
10 ጳውሎስ ንጉሥ አግሪጳ የአይሁዳውያንን ልማዶችና በመካከላቸው ያሉትን ክርክሮች ጠንቅቆ የሚያውቅ መሆኑን በመግለጽ በእሱ ፊት የመከላከያ ሐሳቡን የማቅረብ አጋጣሚ በማግኘቱ ለንጉሡ በአክብሮት ምስጋና አቀረበ። ከዚያም ጳውሎስ “በአምልኮ ሥርዓታችን ውስጥ ወግ አጥባቂ የሆነውን ቡድን በመከተል ፈሪሳዊ ሆኜ [ኖሬአለሁ]” በማለት ስለ ቀድሞ ሕይወቱ ተናገረ። (ሥራ 26:5) ጳውሎስ ፈሪሳዊ ሳለ የመሲሑን መምጣት በተስፋ ይጠባበቅ ነበር። አሁን ደግሞ ክርስቲያን እንደመሆኑ መጠን ለረጅም ዘመን ሲጠበቅ የነበረው መሲሕ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን በድፍረት ገለጸ። በዚህ ዕለት ጳውሎስ ለፍርድ የቀረበው እሱም ሆነ ከሳሾቹ በጋራ በሚያምኑበት ጉዳይ ማለትም አምላክ ለአባቶቻቸው የገባው ቃል እንደሚፈጸም ተስፋ በማድረጉ ነው። ጳውሎስ የሰጠው ማብራሪያ አግሪጳ ይበልጥ በትኩረት እንዲያዳምጠው አነሳስቶታል።
11 ጳውሎስ ከዚህ ቀደም በክርስቲያኖች ላይ የጭካኔ ድርጊት መፈጸሙን በማስታወስ እንዲህ ብሏል፦ “እኔ ራሴ የናዝሬቱ ኢየሱስን ስም በተቻለኝ መጠን መቃወም እንዳለብኝ አድርጌ አስብ ነበር፤ . . . በእነሱ [በክርስቶስ ተከታዮች] ላይ እጅግ ተቆጥቼ በሌሎች ከተሞች ያሉትን እንኳ ሳይቀር እስከ ማሳደድ ደርሻለሁ።” (ሥራ 26:9-11) ጳውሎስ እንዲህ ሲል እያጋነነ አልነበረም። በክርስቲያኖች ላይ ያደረሰውን ከባድ ስደት ብዙዎች ያውቃሉ። (ገላ. 1:13, 23) አግሪጳ ‘ታዲያ ይህ ሰው እንዲለወጥ ያደረገው ምንድን ነው?’ ብሎ ሳይገረም አይቀርም።
12 ጳውሎስ በመቀጠል የተናገራቸው ሐሳቦች መልሱን ይዘዋል፦ “ከካህናት አለቆች ሥልጣንና ተልእኮ ተቀብዬ ወደ ደማስቆ እየተጓዝኩ ሳለ ንጉሥ ሆይ፣ እኩለ ቀን ሲሆን በመንገድ ላይ ከፀሐይ ብርሃን የበለጠ ድምቀት ያለው ከሰማይ የመጣ ብርሃን በእኔና አብረውኝ በሚጓዙት ሰዎች ዙሪያ ሲያበራ አየሁ። ሁላችንም መሬት ላይ በወደቅን ጊዜ አንድ ድምፅ በዕብራይስጥ ቋንቋ ‘ሳኦል፣ ሳኦል ለምን ታሳድደኛለህ? መውጊያውን መራገጥህን ከቀጠልክ ለአንተው የባሰ ይሆንብሃል’ ሲለኝ ሰማሁ። እኔም ‘ጌታዬ፣ አንተ ማን ነህ?’ አልኩ። ጌታም እንዲህ አለኝ፦ ‘እኔ አንተ የምታሳድደኝ ኢየሱስ ነኝ።’”—ሥራ 26:12-15
13 ጳውሎስ ይህን ተአምራዊ ራእይ ከማየቱ በፊት በምሳሌያዊ አነጋገር ‘መውጊያውን ሲራገጥ’ ነበር። አንድ የጭነት ከብት ጫፉ ሹል የሆነውን የበሬ መውጊያ በመራገጥ ሳያስፈልግ ራሱን እንደሚጎዳ ሁሉ ጳውሎስም የአምላክን ፈቃድ በመቃወም በራሱ ላይ መንፈሳዊ ጉዳት አድርሷል። ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ወደ ደማስቆ ይጓዝ ለነበረው ለጳውሎስ በመገለጥ የተሳሳተ አቅጣጫ ይከተል የነበረው ይህ ልበ ቅን ሰው አስተሳሰቡን እንዲለውጥ አድርጎታል።—ዮሐ. 16:1, 2
14 በእርግጥም ጳውሎስ በሕይወቱ ውስጥ ሥር ነቀል ለውጦች አድርጓል። አግሪጳን እንዲህ ብሎታል፦ “ከሰማይ ለተገለጠልኝ ነገር አልታዘዝም አላልኩም፤ ከዚህ ይልቅ በመጀመሪያ በደማስቆ ላሉ ቀጥሎም በኢየሩሳሌምና በመላው የይሁዳ አገር ሁሉ ለሚገኙ ከዚያም ለአሕዛብ ንስሐ እንዲገቡና ለንስሐ የሚገባ ሥራ በመሥራት ወደ አምላክ እንዲመለሱ የሚያሳስበውን መልእክት ማዳረሴን ቀጠልኩ።” (ሥራ 26:19, 20) ጳውሎስ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ እኩለ ቀን ላይ በራእይ በተገለጠለት ዕለት የሰጠውን ተልእኮ ለበርካታ ዓመታት ሲፈጽም ቆይቷል። ታዲያ ምን ውጤት አግኝቷል? ጳውሎስ ለሰበከላቸው ምሥራች ጥሩ ምላሽ የሰጡ ሰዎች ሥነ ምግባር የጎደለው ብልሹ አኗኗራቸውን ትተው ወደ አምላክ ተመልሰዋል። እነዚህ ሰዎች ጥሩ ዜጎች መሆናቸው ሰዎች ለሕግና ለሥርዓት አክብሮት እንዲኖራቸው አስተዋጽኦ አበርክቷል።
15 ሆኖም እነዚህ መልካም ውጤቶች ጳውሎስን ለሚቃወሙት አይሁዳውያን ምንም ማለት አልነበሩም። ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “አይሁዳውያኑ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የያዙኝና ሊገድሉኝ የሞከሩት በዚህ የተነሳ ነው። ይሁን እንጂ ከአምላክ እርዳታ በማግኘቴ እስከዚህ ቀን ድረስ ለትንሹም ሆነ ለትልቁ መመሥከሬን ቀጥያለሁ።”—ሥራ 26:21, 22
16 እኛም እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ለእምነታችን “መልስ ለመስጠት ዘወትር ዝግጁዎች” መሆን አለብን። (1 ጴጥ. 3:15) ለዳኞችና ለገዢዎች ስለ እምነታችን ስንናገር ጳውሎስ ንጉሥ አግሪጳና ፊስጦስ ፊት ቀርቦ ሲናገር የተጠቀመበትን ዘዴ መከተላችን ሊጠቅመን ይችላል። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የራሳችንንም ሆነ ለመልእክታችን ምላሽ የሰጡ ሰዎችን ሕይወት በመቀየር የተሻልን ሰዎች እንድንሆን የረዳን እንዴት እንደሆነ በአክብሮት መግለጽ እንችላለን፤ በዚህ መንገድ የእነዚህን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ልብ መንካት እንችል ይሆናል።
(የሐዋርያት ሥራ 26:28) አግሪጳም ጳውሎስን “በአጭር ጊዜ ውስጥ አሳምነህ ክርስቲያን ልታደርገኝ እኮ ምንም አልቀረህም” አለው።
“ወደ ቄሳር ይግባኝ ብያለሁ!”
18 ይሁንና ጳውሎስ ለአገረ ገዢው የሚሰጠው መልስ አለው፦ “ክቡር ፊስጦስ ሆይ፣ ማበዴስ አይደለም፤ እኔ እየተናገርኩ ያለሁት እውነተኛና ከጤናማ አእምሮ የሚመነጭ ቃል ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ በነፃነት እያናገርኩት ያለሁት ንጉሥ ስለ እነዚህ ነገሮች በሚገባ ያውቃል፤ . . . ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፣ በነቢያት ታምናለህ? እንደምታምን አውቃለሁ።” በዚህ ጊዜ አግሪጳ “በአጭር ጊዜ ውስጥ አሳምነህ ክርስቲያን ልታደርገኝ እኮ ምንም አልቀረህም” ሲል መለሰለት። (ሥራ 26:25-28) ንጉሡ ይህን የተናገረው ከልቡ ይሁንም አይሁን ጳውሎስ የሰጠው ምሥክርነት ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሮበት እንደነበር ያሳያል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(የሐዋርያት ሥራ 26:14) ሁላችንም መሬት ላይ በወደቅን ጊዜ አንድ ድምፅ በዕብራይስጥ ቋንቋ ‘ሳኦል፣ ሳኦል ለምን ታሳድደኛለህ? መውጊያውን መቃወምህን ከቀጠልክ ለአንተው የባሰ ይሆንብሃል’ ሲለኝ ሰማሁ።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ሥራ 26:14
መውጊያውን መቃወም፦ መውጊያ አንድን እንስሳ ወደ ፊት እንዲሄድ ለመቀስቀስ የሚያገለግል ጫፉ ሹል የሆነ ዘንግ ነው። (መሳ 3:31) “መውጊያውን መቃወም” የሚለው አገላለጽ በግሪክኛ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ የሚገኝ ምሳሌያዊ አባባል ነው። ይህ አባባል በመውጊያው ጎንተል ሲደረግ መልሶ የሚራገጥን እልኸኛ በሬ እንድናስብ ያደርገናል፤ እንስሳው ይህን ማድረጉ እንደሚጎዳው የታወቀ ነው። ሳኦል ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት እንዲህ ዓይነት አካሄድ ይከተል ነበር። ጳውሎስ፣ ይሖዋ አምላክ የሚደግፋቸውን የኢየሱስ ተከታዮች በማሳደድ በራሱ ላይ ጉዳት የሚያስከትል ጎዳና እየተከተለ ነበር። (ከሥራ 5:38, 39 እና 1ጢሞ 1:13, 14 ጋር አወዳድር።) በመክ 12:11 ላይ ‘የበሬ መውጊያ’ የጥበበኞችን ቃላት ለማመልከት በምሳሌያዊ መንገድ የተሠራበት ሲሆን እንዲህ ያሉት ቃላት አድማጩ የሚሰጠውን ምክር እንዲሰማ ያነሳሱታል።
nwt የቃላት መፍቻ
የከብት መውጊያ። ገበሬዎች አንድን ከብት ወደ ፊት እንዲሄድ ለመቀስቀስ የሚጠቀሙበት ጫፉ ላይ ሹል ብረት ያለው ዘንግ ነው። የከብት መውጊያ አንድ ሰው የተሰጠውን ጥበብ ያዘለ ምክር በተግባር እንዲያውል ሊያነሳሳው ከሚችል የጠቢብ ሰው ቃል ጋር ተመሳስሏል። “መውጊያውን መቃወም” የሚለው አገላለጽ አንድ ዓመፀኛ በሬ ሲወጋ መውጊያውን ለመራገጥ የሚያደርገውን ሙከራ የሚያሳይ ሲሆን እንዲህ ማድረጉ በሬውን ለበለጠ ጉዳት ይዳርገዋል።—ሥራ 26:14፤ መሳ 3:31
(የሐዋርያት ሥራ 26:27) ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፣ በነቢያት ታምናለህ? እንደምታምን አውቃለሁ።”
ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት እንዲቀበሉ እርዷቸው
14 ጳውሎስ፣ አግሪጳ አይሁዳዊ ነኝ ይል እንደነበር ያውቃል። ስለዚህ አግሪጳ ስለ አይሁድ እምነት የነበረውን ግንዛቤ በመጠቀም “ነቢያትና ሙሴ ይሆን ዘንድ ያለውን” ማለትም የመሲሑን ሞትና ትንሣኤ አስመልክተው “ከተናገሩት በቀር አንድ ስንኳ የተናገርሁት የለም” በማለት አስረዳ። (የሐዋርያት ሥራ 26:22, 23) ከዚያም በቀጥታ አግሪጳን “ነቢያትን ታምናለህን?” በማለት ጠየቀው። አግሪጳ አጣብቂኝ ውስጥ ገባ። በነቢያት አላምንም ቢል የአይሁድ እምነት ተከታይ መሆኑ ጥያቄ ውስጥ ይገባል። በጳውሎስ ሐሳብ ከተስማማ ደግሞ እሱን እንደደገፈ ሊቆጠርበትና ክርስቲያን ሊባል ነው። ጳውሎስ ‘እንድታምናቸው አውቃለሁ’ በማለት የራሱን ጥያቄ መለሰ። (የሐዋርያት ሥራ 26:27) አግሪጳ ምን ብሎ ይሆን? “አንተ እኮ በዚህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ክርስቲያን ልታደርገኝ ነው!” አለው። (የሐዋርያት ሥራ 26:28 የ1980 ትርጉም) ምንም እንኳን አግሪጳ ክርስትናን ባይቀበልም ጳውሎስ የተናገረው ነገር በተወሰነ መጠን ልቡን እንደነካው አያጠራጥርም።—ዕብራውያን 4:12
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(የሐዋርያት ሥራ 25:1-12) ፊስጦስም ወደ አውራጃው ከመጣና ኃላፊነቱን ከተረከበ ከሦስት ቀን በኋላ ከቂሳርያ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። 2 የካህናት አለቆችና አንዳንድ የታወቁ አይሁዳውያንም በጳውሎስ ላይ ያላቸውን ክስ ለእሱ አቀረቡ። ከዚያም ፊስጦስን ይለምኑት ጀመር፤ 3 ጳውሎስን ወደ ኢየሩሳሌም በማስመጣት እንዲተባበራቸው ጠየቁት። ይህን ያሉት ግን መንገድ ላይ አድፍጠው ጳውሎስን ሊገድሉት አስበው ስለነበር ነው። 4 ይሁን እንጂ ፊስጦስ፣ ጳውሎስ እዚያው ቂሳርያ ታስሮ እንደሚቆይና እሱ ራሱም በቅርቡ ወደዚያ እንደሚመለስ ነገራቸው። 5 “በመሆኑም ከእናንተ መካከል ሥልጣን ያላቸው ከእኔ ጋር ይውረዱና ሰውየው ያጠፋው ነገር ካለ ይክሰሱት” አላቸው። 6 ስለዚህ ፊስጦስ ከስምንት ወይም ከአሥር ቀን ያልበለጠ ጊዜ ከእነሱ ጋር ካሳለፈ በኋላ ወደ ቂሳርያ ወረደ፤ በማግስቱም በፍርድ ወንበር ላይ ተቀምጦ ጳውሎስን እንዲያመጡት አዘዘ። 7 ጳውሎስ በቀረበ ጊዜ ከኢየሩሳሌም የመጡት አይሁዳውያን በዙሪያው ቆመው በማስረጃ ያልተደገፉ በርካታ ከባድ ክሶች አቀረቡበት። 8 ጳውሎስ ግን “እኔ በአይሁዳውያን ሕግ ላይም ሆነ በቤተ መቅደሱ ወይም በቄሳር ላይ ምንም የፈጸምኩት በደል የለም” ሲል የመከላከያ መልሱን ሰጠ። 9 ፊስጦስም በአይሁዳውያን ዘንድ ተወዳጅነት ማትረፍ ስለፈለገ ጳውሎስን “ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተህ ስለዚህ ጉዳይ እዚያ እኔ ባለሁበት መዳኘት ትፈልጋለህ?” ሲል ጠየቀው። 10 ጳውሎስ ግን እንዲህ አለ፦ “እኔ ልዳኝበት በሚገባኝ በቄሳር የፍርድ ወንበር ፊት ቆሜአለሁ። አንተ ራስህ በሚገባ እንደተገነዘብከው በአይሁዳውያን ላይ የፈጸምኩት ምንም በደል የለም። 11 በእርግጥ ጥፋተኛ ሆኜ ከተገኘሁና ለሞት የሚያበቃ ነገር ፈጽሜ ከሆነ ከሞት ልዳን አልልም፤ እነዚህ ሰዎች ያቀረቡብኝ ክስ ሁሉ መሠረተ ቢስ ከሆነ ግን እነሱን ለማስደሰት ብሎ ማንም ሰው እኔን ለእነሱ አሳልፎ የመስጠት መብት የለውም። ወደ ቄሳር ይግባኝ ብያለሁ!” 12 በዚህ ጊዜ ፊስጦስ ከአማካሪዎቹ ጋር ከተመካከረ በኋላ “ወደ ቄሳር ይግባኝ ስላልክ ወደ ቄሳር ትሄዳለህ” ሲል መለሰለት።
ከጥር 28–የካቲት 3
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | የሐዋርያት ሥራ 27-28
“ጳውሎስ በመርከብ ወደ ሮም ተጓዘ”
(የሐዋርያት ሥራ 27:23, 24) ቅዱስ አገልግሎት የማቀርብለትና ንብረቱ የሆንኩለት አምላክ የላከው መልአክ ትናንት ሌሊት አጠገቤ ቆሞ 24 ‘ጳውሎስ ሆይ፣ አትፍራ። ቄሳር ፊት መቅረብ ይገባሃል፤ አምላክ ለአንተ ሲል ከአንተ ጋር የሚጓዙት ሰዎች ሁሉ እንዲተርፉ ያደርጋል’ ብሎኛል።
“ከእናንተ አንድም ነፍስ አይጠፋም”
15 ጳውሎስ በመርከቡ ላይ ለነበሩ በርካታ ሰዎች ‘አምላክ ስለገባው የተስፋ ቃል’ ሳይመሠክርላቸው አልቀረም። (ሥራ 26:6፤ ቆላ. 1:5) የመርከብ መሰበር አደጋ ተደቅኖባቸው ባለበት በዚህ ወቅት ደግሞ በሕይወት እንደሚተርፉ የሚያሳይ አሳማኝ ማስረጃ ሊነግራቸው ነው። እንዲህ አለ፦ “[አንድ] መልአክ ትናንት ሌሊት አጠገቤ ቆሞ ‘ጳውሎስ፣ አትፍራ። ቄሳር ፊት መቅረብ ይገባሃል፤ አምላክ ለአንተ ሲል ከአንተ ጋር የሚጓዙት ሰዎችም ሁሉ በቸርነቱ እንዲተርፉ ያደርጋል’ ብሎኛል።” ከዚያም እንዲህ ሲል አሳሰባቸው፦ “ስለዚህ እናንተ ሰዎች፣ አይዟችሁ! ምክንያቱም ይህ የተነገረኝ ነገር በትክክል እንደሚፈጸም በአምላክ ላይ እምነት አለኝ። ይሁን እንጂ ከአንዲት ደሴት ዳርቻ ጋር መላተማችን የግድ ነው።”—ሥራ 27:23-26
(የሐዋርያት ሥራ 28:1, 2) እኛም በደህና ወደ የብስ ደረስን፤ ደሴቲቱም ማልታ ተብላ እንደምትጠራ አወቅን። 2 የአካባቢው ነዋሪዎችም የተለየ ደግነት አሳዩን። ዝናብ መዝነብ ጀምሮ ስለነበረና ብርድ ስለነበር እሳት በማቀጣጠል ሁላችንንም በደግነት አስተናገዱን።
“ከእናንተ አንድም ነፍስ አይጠፋም”
18 ከአደጋው የተረፉት ሰዎች ያሉት ከሲሲሊ በስተ ደቡብ በምትገኘው በማልታ ደሴት እንደሆነ ተገነዘቡ። (“ማልታ የምትገኘው የት ነው?” የሚል ርዕስ ያለውን በገጽ 209 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።) ባዕድ ቋንቋ የሚናገሩት የደሴቲቱ ነዋሪዎች “በሰብዓዊነት ተነሳስተው ልዩ ደግነት” አሳዩአቸው። (ሥራ 28:2) የባሕር ዳርቻው ላይ የደረሱት መንገደኞች በውኃ ርሰው እየተንቀጠቀጡ ስለነበር የማልታ ሰዎች እሳት አነደዱላቸው። ይህም ብርዱንና ዝናቡን እንዲቋቋሙ አስችሏቸዋል። በተጨማሪም እሳቱ ለአንድ ተአምር መፈጸም ምክንያት ሆኗል።
“ከእናንተ አንድም ነፍስ አይጠፋም”
21 ፑፕልዮስ የሚባለው ሀብታም ባለርስት የሚኖረው በዚህ አካባቢ ነበር። በማልታ የሚገኘው ዋናው ሮማዊ ባለሥልጣን እሱ ሳይሆን አይቀርም። ሉቃስ ይህን ግለሰብ “የደሴቲቱ አስተዳዳሪ” ሲል የገለጸው ሲሆን በማልታ ቋንቋ በተቀረጹ ሁለት ጽሑፎች ላይ ይኸው የማዕረግ ስም ይገኛል። ፑፕልዮስ ጳውሎስንና ጓደኞቹን ለሦስት ቀናት በእንግድነት ተቀበላቸው። ይሁንና የፑፕልዮስ አባት ታሞ ነበር። በዚህ ጊዜም ቢሆን ሉቃስ በሽታውን በትክክል ገልጾታል። ሰውየው “ትኩሳትና ተቅማጥ ይዞት ተኝቶ” እንደነበር ሲጽፍ በሽታው የሚያስከትለውን የጤና ቀውስ በትክክል አስፍሯል። ጳውሎስ ጸልዮ እጁን ከጫነበት በኋላ ሰውየው ተፈወሰ። የአካባቢው ነዋሪዎች በተፈጸመው ተአምር በጥልቅ ከመነካታቸው የተነሳ ጳውሎስ እንዲፈውሳቸው ሌሎች በሽተኞችን ይዘው መጡ፤ ከዚህም ሌላ ጳውሎስና ጓደኞቹ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማሟላት ስጦታ አመጡላቸው።—ሥራ 28:7-10
(የሐዋርያት ሥራ 28:16, 17) በመጨረሻም ሮም በደረስን ጊዜ ጳውሎስ አንድ ወታደር እየጠበቀው ብቻውን እንዲኖር ተፈቀደለት። 17 ይሁን እንጂ ከሦስት ቀን በኋላ የአይሁዳውያንን ታላላቅ ሰዎች አንድ ላይ ጠራ። ሰዎቹም በተሰበሰቡ ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ “ወንድሞች፣ ምንም እንኳ ሕዝቡን ወይም የአባቶቻችንን ልማድ የሚጻረር ነገር ያልፈጸምኩ ቢሆንም በኢየሩሳሌም አስረው ለሮማውያን አሳልፈው ሰጥተውኛል።
‘የተሟላ ምሥክርነት መስጠት’
10 አንድ ላይ ሲጓዙ የነበሩት መንገደኞች በመጨረሻ ሮም ደረሱ፤ ከዚያም “ጳውሎስ አንድ ወታደር እየጠበቀው ብቻውን እንዲኖር ተፈቀደለት።” (ሥራ 28:16) የቁም እስረኛ የሆነ ሰው እንዳያመልጥ በአብዛኛው ከጠባቂው ጋር በሰንሰለት እንዲቆራኝ ይደረግ ነበር። ያም ቢሆን ጳውሎስ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ ስለሆነ በሰንሰለት መታሰሩ ዝም ሊያሰኘው አይችልም። በመሆኑም ከጉዞው ድካም ለሦስት ቀን ብቻ ካረፈ በኋላ ራሱን ለማስተዋወቅና ምሥክርነት ለመስጠት ሲል በሮም ያሉትን የአይሁዳውያንን ታላላቅ ሰዎች ጠራ።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(የሐዋርያት ሥራ 27:9) ረጅም ጊዜ በመቆየታችንና የስርየት ቀን ጾም እንኳ ሳይቀር በማለፉ፣ ወቅቱ በባሕር ላይ ለመጓዝ አደገኛ ነበር፤ በመሆኑም ጳውሎስ አንድ ሐሳብ አቀረበ፤
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ሥራ 27:9
የስርየት ቀን ጾም፦ ቃል በቃል “ጾሙ።” እዚህ ላይ “ጾም” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል በሙሴ ሕግ ውስጥ የታዘዘውን ብቸኛ ጾም ይኸውም ከዓመታዊው የስርየት ቀን (ዮም ኪፑር ተብሎም ይጠራል፤ ዕብራይስጥ፣ ዮም ሃክኪፕፑሪም፣ “የመሸፈኛ ቀን”) ጋር የተያያዘውን ጾም ያመለክታል። (ዘሌ 16:29-31፤ 23:26-32፤ ዘኁ 29:7፤ ከቃላት መፍቻው ላይ “የስርየት ቀን” የሚለውን ተመልከት።) ከስርየት ቀን ጋር በተያያዘ የሚሠራበት “ራስን ማጎሳቆል” የሚለው አገላለጽ፣ መጾምን ጨምሮ የራስን ፍላጎት ከመፈጸም መቆጠብን የሚያሳዩ የተለያዩ ድርጊቶችን ሊያመለክት ይችላል። (ዘሌ 16:29 ግርጌ) ሥራ 27:9 ላይ “ጾም” የሚለው ቃል መጠቀሱ በስርየት ቀን ራስን ለማጎሳቆል ከሚደረጉት ነገሮች ዋነኛው መጾም መሆኑን ያመለክታል። የስርየት ቀን ጾም የሚውለው በመስከረም መገባደጃ ወይም በጥቅምት መጀመሪያ አካባቢ ነው።
(የሐዋርያት ሥራ 28:11) ከሦስት ወር በኋላም “የዙስ ልጆች” የሚል ዓርማ ባለው መርከብ ጉዞ ጀመርን። ይህ መርከብ ከእስክንድርያ የመጣ ሲሆን ክረምቱን ያሳለፈው በዚህች ደሴት ነበር።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ሥራ 28:11
የዙስ ልጆች፦ በግሪካውያንና በሮማውያን አፈ ታሪክ መሠረት “የዙስ ልጆች” (ግሪክኛ፣ ዲዮስኩሪ) ካስተርና ፖለክስ ሲሆኑ ዙስ (ጁፒተር) የተባለው አምላክ እና ሌዳ የተባለችው የስፓርታ ንግሥት መንታ ወንዶች ልጆች ናቸው። የዙስ ልጆች የባሕረኞች ጠባቂ እንደሆኑና ባሕር ላይ አደጋ ያጋጠማቸውን መርከበኞች እንደሚያድኑ ይታመን ነበር። የመርከቧን ዓርማ በተመለከተ እንዲህ ያለ ዝርዝር መረጃ መስፈሩ ዘገባውን የጻፈው የዓይን ምሥክር የነበረ ሰው መሆኑን ያረጋግጣል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(የሐዋርያት ሥራ 27:1-12) እኛም በመርከብ ወደ ጣሊያን እንድንሄድ ስለተወሰነ ጳውሎስንና የተወሰኑ እስረኞችን የአውግስጦስ ክፍለ ጦር አባል ለሆነ ዩልዮስ ለሚባል አንድ የጦር መኮንን አስረከቧቸው። 2 ከአድራሚጢስ ተነስቶ በእስያ አውራጃ የባሕር ዳርቻ ላይ ወደሚገኙት ወደቦች ሊሄድ በተዘጋጀ መርከብ ተሳፍረን ጉዞ ጀመርን፤ በተሰሎንቄ የሚኖረው የመቄዶንያው አርስጥሮኮስም አብሮን ነበር። 3 በማግስቱ ሲዶና ደረስን፤ ዩልዮስም ለጳውሎስ ደግነት በማሳየት ወደ ወዳጆቹ እንዲሄድና እንክብካቤ እንዲያደርጉለት ፈቀደለት። 4 ከዚያም ተነስተን በባሕር ላይ ጉዟችንን ቀጠልን፤ ነፋሱ ከፊት ለፊታችን ይነፍስ ስለነበር ቆጵሮስን ተገን አድርገን አለፍን። 5 ከዚያም በኪልቅያና በጵንፍልያ ዳርቻ በኩል ያለውን ባሕር አቋርጠን በሊቂያ ወደሚገኘው የሚራ ወደብ ደረስን። 6 በዚያም መኮንኑ ወደ ጣሊያን የሚሄድ ከእስክንድርያ የመጣ መርከብ አግኝቶ አሳፈረን። 7 ከዚያም ለብዙ ቀናት በዝግታ ተጉዘን በስንት ችግር ቀኒዶስ ደረስን። ነፋሱ እንደ ልብ እንድንጓዝ ስላልፈቀደልን በስልሞና በኩል ቀርጤስን ተገን አድርገን አለፍን። 8 የባሕሩን ዳርቻ ይዘን በብዙ ችግር በመጓዝ በላሲያ ከተማ አቅራቢያ ወዳለው “መልካም ወደብ” ወደተባለ ስፍራ ደረስን። 9 ረጅም ጊዜ በመቆየታችንና የስርየት ቀን ጾም እንኳ ሳይቀር በማለፉ፣ ወቅቱ በባሕር ላይ ለመጓዝ አደገኛ ነበር፤ በመሆኑም ጳውሎስ አንድ ሐሳብ አቀረበ፤ 10 እንዲህም አላቸው፦ “እናንተ ሰዎች፣ ይህ ጉዞ በጭነቱና በመርከቡ ላይ ብቻ ሳይሆን በሕይወታችንም ላይ እንኳ ሳይቀር ከፍተኛ ጉዳትና ጥፋት ሊያስከትል እንደሚችል ይታየኛል።” 11 ይሁን እንጂ መኮንኑ ጳውሎስ የተናገረውን ከመቀበል ይልቅ የመርከቡ መሪና የመርከቡ ባለቤት የተናገሩትን ሰማ። 12 ወደቡ የክረምቱን ጊዜ በዚያ ለማሳለፍ አመቺ ስላልነበረ አብዛኞቹ ከዚያ ተነስተው ጉዟቸውን በመቀጠል እንደ ምንም ፊንቄ ወደተባለው የቀርጤስ ወደብ ደርሰው ክረምቱን እዚያ ለማሳለፍ ሐሳብ አቀረቡ፤ ይህ ወደብ ወደ ሰሜን ምሥራቅም ሆነ ወደ ደቡብ ምሥራቅ ለመሄድ የሚያስችል ነበር።