የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • bt ምዕ. 23 ገጽ 181-188
  • “የማቀርበውን የመከላከያ መልስ ስሙ”

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • “የማቀርበውን የመከላከያ መልስ ስሙ”
  • ‘ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ መመሥከር’
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • “አምላክን አመሰገኑ” (የሐዋርያት ሥራ 21:18-20ሀ)
  • ብዙዎች አሁንም “ለሕጉ ቀናተኞች ናቸው” (የሐዋርያት ሥራ 21:20ለ, 21)
  • “የተወራው ሁሉ ከንቱ መሆኑ” ይታወቃል (የሐዋርያት ሥራ 21:22-26)
  • “ይህ ሰው መኖር የማይገባው” ነው! (የሐዋርያት ሥራ 21:27 እስከ 22:30)
  • “ፈሪሳዊ ነኝ” (የሐዋርያት ሥራ 23:1-10)
  • በከፍተኛ ባለሥልጣናት ፊት ለምሥራቹ መሟገት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2016
  • የአንባቢያን ጥያቄዎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • የጥንት ክርስቲያኖችና የሙሴ ሕግ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2003
  • አትፍራ፣ ይሖዋ ረዳትህ ነው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2020
ለተጨማሪ መረጃ
‘ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ መመሥከር’
bt ምዕ. 23 ገጽ 181-188

ምዕራፍ 23

“የማቀርበውን የመከላከያ መልስ ስሙ”

ጳውሎስ በቁጣ በተሞላው ሕዝብና በሳንሄድሪን ፊት ለእውነት ተሟገተ

በሐዋርያት ሥራ 21:18 እስከ 23:10 ላይ የተመሠረተ

1, 2. ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም የመጣው ለምንድን ነው? እዚያስ ምን ፈታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሙታል?

ኢየሩሳሌም! ጳውሎስ ወደዚህች ከተማ ተመልሷል፤ በሰው በተጨናነቁት ጠባብ ጎዳናዎቿ ላይ እየተዘዋወረ ነው። መቼም የኢየሩሳሌምን ያህል በይሖዋ አምልኮ የዘመናት ታሪክ ያስቆጠረ ሌላ ከተማ የለም። አብዛኞቹ ነዋሪዎቿም በከተማቸው የቀድሞ ገናና ታሪክ ይኩራራሉ። በዚያ የሚኖሩ ብዙ ክርስቲያኖችም እንኳ የጥንቱን ወግ ልማድ መተው እንደማይፈልጉ ጳውሎስ ያውቃል፤ ወደፊት እየገሰገሰ ካለው የይሖዋ ዓላማ ጋር እኩል መጓዝ እንደሚከብዳቸው አስተውሏል። ገና በኤፌሶን ሳለ ይህችን ታላቅ ከተማ በድጋሚ መጎብኘት የፈለገው ለዚህ ነው፤ ወንድሞቹ ቁሳዊ እርዳታ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ እገዛም እንደሚያስፈልጋቸው ተሰምቶታል። (ሥራ 19:21) ጳውሎስ አደጋ ሊያጋጥመው እንደሚችል ቢያውቅም ወደዚህ ለመምጣት ያወጣውን ዕቅድ አልለወጠም።

2 ታዲያ ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ምን ያጋጥመው ይሆን? አንዱ ፈተና የሚመጣው ከክርስቶስ ተከታዮች ነው፤ ስለ ጳውሎስ በሰሙት አሉባልታ የተነሳ ቅር ተሰኝተዋል። ከክርስቶስ ጠላቶች ደግሞ ገና ከዚህ የከፉ ፈተናዎች ያጋጥሙታል። እነዚህ ሰዎች የሐሰት ክሶች ይሰነዝሩበታል፣ ይደበድቡታል እንዲሁም እንደሚገድሉት ይዝቱበታል። በጳውሎስ ሕይወት ውስጥ የተፈጠሩት እነዚህ ነውጦች ስለ እምነቱ ለመናገር አጋጣሚ ይከፍቱለታል። ፈተናዎቹን በትሕትና፣ በድፍረትና በእምነት የተወጣበት መንገድ ዛሬ ላሉ ክርስቲያኖች ግሩም ምሳሌ ይሆናል። ከእሱ የምናገኘውን ትምህርት እስቲ እንመልከት።

“አምላክን አመሰገኑ” (የሐዋርያት ሥራ 21:18-20ሀ)

3-5. (ሀ) ጳውሎስ በኢየሩሳሌም በተካሄደው በየትኛው ስብሰባ ላይ ተገኝቷል? በስብሰባው ላይ የተነሳው ጉዳይስ ምን ነበር? (ለ) ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ከሚገኙ ሽማግሌዎች ጋር ካደረገው ስብሰባ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

3 ጳውሎስና የጉዞ ጓደኞቹ ኢየሩሳሌም በደረሱ ማግስት፣ የጉባኤውን ሽማግሌዎች ለማግኘት ሄዱ። በሕይወት ካሉት ሐዋርያት መካከል የአንዳቸውም ስም በዚህ ዘገባ ላይ አልተጠቀሰም፤ በወቅቱ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለማገልገል ሄደው ሊሆን ይችላል። የኢየሱስ ወንድም ያዕቆብ ግን አሁንም እዚያ ነው። (ገላ. 2:9) ጳውሎስ ‘ከሽማግሌዎቹ ሁሉ’ ጋር ያደረገውን ስብሰባ የመራው ያዕቆብ ሳይሆን አይቀርም።—ሥራ 21:18

4 ጳውሎስ ለሽማግሌዎቹ ሰላምታ ካቀረበ በኋላ “እሱ ባከናወነው አገልግሎት አማካኝነት አምላክ በአሕዛብ መካከል የፈጸማቸውን ነገሮች በዝርዝር ይተርክላቸው ጀመር።” (ሥራ 21:19) ወንድሞች በሰሙት ነገር በጣም ተበረታተው እንደሚሆን መገመት እንችላለን። ዛሬም እኛ በሌሎች አገሮች ከስብከቱ ሥራ ጋር በተያያዘ ስለተገኘው እድገት ስንሰማ እንደሰታለን።—ምሳሌ 25:25

5 ጳውሎስ በንግግሩ መሃል፣ ከአውሮፓ ይዞ ስለመጣው መዋጮ ሳይጠቅስ አይቀርም። ርቀው በሚገኙ አገሮች የሚኖሩ ወንድሞች ስላሳዩት አሳቢነት ሲሰሙ እነዚያ ሽማግሌዎች ልባቸው በደስታ ተሞልቶ መሆን አለበት። ዘገባው የጳውሎስን ሪፖርት ካዳመጡ በኋላ “አምላክን አመሰገኑ” ይላል። (ሥራ 21:20ሀ) ዛሬም በተመሳሳይ አደጋ የደረሰባቸው ወይም በጠና የታመሙ ክርስቲያኖች፣ የእምነት ባልንጀሮቻቸው በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ሲረዷቸውና ሲያጽናኗቸው ልባቸው በጥልቅ ይነካል።

ብዙዎች አሁንም “ለሕጉ ቀናተኞች ናቸው” (የሐዋርያት ሥራ 21:20ለ, 21)

6. ጳውሎስ ምን ችግር መከሰቱን ሰማ?

6 ከዚያም ሽማግሌዎቹ ጳውሎስን በቀጥታ የሚመለከት ችግር በይሁዳ መከሰቱን ገለጹለት። እንዲህ አሉት፦ “ወንድም፣ ከአይሁዳውያን መካከል በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አማኞች እንዳሉ ታውቃለህ፤ ደግሞም ሁሉም ለሕጉ ቀናተኞች ናቸው። እነሱም አንተ በአሕዛብ መካከል ያሉት አይሁዳውያን ሁሉ ልጆቻቸውን እንዳይገርዙም ሆነ የቆየውን ልማድ እንዳይከተሉ በመንገር የሙሴን ሕግ እንዲተዉ ስታስተምር እንደቆየህ ስለ አንተ የሚወራውን ወሬ ሰምተዋል።”a—ሥራ 21:20ለ, 21

7, 8. (ሀ) በይሁዳ የነበሩ ብዙ ክርስቲያኖች ምን የተሳሳተ አመለካከት ነበራቸው? (ለ) አንዳንድ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች የነበራቸው የተሳሳተ አስተሳሰብ እንደ ክህደት ሊቆጠር የማይችለው ለምንድን ነው?

7 የሙሴ ሕግ ከተሻረ ከ20 ዓመት በላይ አልፎታል፤ ታዲያ አሁንም ለሕጉ የሚቀኑ ብዙ ክርስቲያኖች ሊኖሩ የቻሉት እንዴት ነው? (ቆላ. 2:14) በ49 ዓ.ም. ሐዋርያትና ሽማግሌዎች በኢየሩሳሌም ከተሰበሰቡ በኋላ ለጉባኤዎች ደብዳቤ ልከው ነበር፤ በደብዳቤው ላይም ከአሕዛብ የመጡ አማኞች መገረዝም ሆነ የሙሴን ሕግ መጠበቅ እንደማያስፈልጋቸው ገልጸዋል። (ሥራ 15:23-29) ይሁን እንጂ ደብዳቤው አይሁዳውያን አማኞችን በተመለከተ የሚጠቅሰው ነገር የለም፤ ደግሞም አብዛኞቹ የሙሴ ሕግ እንደተሻረ አልገባቸውም።

8 እነዚህ አይሁዳውያን አማኞች እንዲህ ዓይነት የተሳሳተ አስተሳሰብ ስላላቸው ክርስቲያኖች አይደሉም ማለት ነው? በፍጹም። እነዚህ ሰዎች ከባዕድ አምልኮ የመጣን ሃይማኖታዊ ልማድ መከተላቸውን ለመቀጠል እየሞከሩ አይደለም። እነዚህ አይሁዳውያን አማኞች ከፍ አድርገው የሚመለከቱትን ሕግ ቀድሞውንም ቢሆን የሰጣቸው ይሖዋ ነው። በሕጉ ውስጥ ከአጋንንት ጋር ንክኪ ያለው ወይም የተሳሳተ ነገር የለም። ሆኖም ሕጉ ከተሻረው ቃል ኪዳን ጋር የተያያዘ ነበር፤ ክርስቲያኖች ደግሞ በአዲሱ ቃል ኪዳን ሥር ናቸው። በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያለው አምልኮ ለማቅረብ የሕጉን ቃል ኪዳን ማክበር አስፈላጊ መሆኑ ቀርቷል። ለሕጉ የሚቀኑት ዕብራውያን አማኞች፣ የክርስቲያን ጉባኤን በተመለከተ ያልገቧቸው ነገሮች ነበሩ፤ ከዚህም ሌላ ይሖዋ ለጉባኤው ባደረገው አዲስ ዝግጅት ላይ እምነት አልነበራቸውም። ደረጃ በደረጃ እየተገለጠ ከሚሄደው እውነት ጋር አስተሳሰባቸውን ማስማማት ያስፈልጋቸው ነበር።b—ኤር. 31:31-34፤ ሉቃስ 22:20

“የተወራው ሁሉ ከንቱ መሆኑ” ይታወቃል (የሐዋርያት ሥራ 21:22-26)

9. ጳውሎስ የሙሴን ሕግ በተመለከተ ምን አስተምሯል?

9 ጳውሎስ፣ በአሕዛብ መካከል የሚኖሩ አይሁዳውያን “ልጆቻቸውን እንዳይገርዙም ሆነ የቆየውን ልማድ እንዳይከተሉ” እያስተማረ እንደሆነ የተወራበት ነገርስ? ጳውሎስ የአሕዛብ ሐዋርያ ነው፤ አሕዛብ ሕጉን የመጠበቅ ግዴታ እንደሌለባቸው የተላለፈውን ውሳኔ ለእነሱ መንገሩ አይቀርም። ከአሕዛብ የመጡ አማኞች መገረዝና የሙሴን ሕግ ማክበር እንዳለባቸው ለማሳመን የሚሞክሩ ሰዎች ሲያጋጥሙት ደግሞ ስህተታቸውን አጋልጧል። (ገላ. 5:1-7) በሌላ በኩል ደግሞ ጳውሎስ በሄደባቸው ከተሞች ለሚኖሩ አይሁዳውያንም ምሥራቹን ሰብኳል። መልእክቱን ለተቀበሉት አይሁዳውያን የኢየሱስ ሞት ሕጉን እንደሻረውና ሰው የሚጸድቀው በእምነት እንጂ ሕጉን በመጠበቅ እንዳልሆነ አስረድቷቸው መሆን አለበት።—ሮም 2:28, 29፤ 3:21-26

10. ጳውሎስ ከሕጉና ከግርዘት ጋር በተያያዘ ምን ሚዛናዊ አመለካከት ነበረው?

10 አንዳንድ የአይሁዳውያን ልማዶችን ለመከተል ለምሳሌ በሰንበት ሥራ ላለመሥራት ወይም አንዳንድ ምግቦችን ላለመብላት የመረጡ ክርስቲያኖች ነበሩ፤ ጳውሎስ በዚህ አልነቀፋቸውም። (ሮም 14:1-6) ግርዘትን በተመለከተም ያወጣው ደንብ የለም። እንዲያውም ጳውሎስ የጢሞቴዎስ አባት ግሪካዊ ስለሆነ አይሁዳውያን ጢሞቴዎስን በጥርጣሬ እንዳያዩት ሲል ገርዞታል። (ሥራ 16:3) ግርዘት ለግለሰቦች ምርጫ የተተወ ጉዳይ ነበር። ጳውሎስ የገላትያ ክርስቲያኖችን “በፍቅር የሚመራ እምነት እንጂ መገረዝ ወይም አለመገረዝ ፋይዳ የለውም” ብሏቸዋል። (ገላ. 5:6) ይሁንና ሕጉን ለማክበር ብሎ መገረዝ ወይም በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ግርዘት አስፈላጊ እንደሆነ መናገር ስህተት ነው፤ ይህን የሚያደርግ ግለሰብ እምነት ጎድሎታል።

11. ሽማግሌዎቹ ለጳውሎስ ምን ምክር ሰጡት? ሆኖም ጳውሎስ ለማድረግ ፈቃደኛ የሚሆናቸው ወይም የማይሆናቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

11 በጳውሎስ ላይ የተወራው ነገር ትክክል ባይሆንም አይሁዳውያን ክርስቲያኖች በሰሙት ነገር ተረብሸዋል። በመሆኑም ሽማግሌዎቹ እንዲህ የሚል ምክር ሰጡት፦ “ስእለት ያለባቸው አራት ሰዎች በእኛ ዘንድ አሉ። እነዚህን ሰዎች ይዘህ በመሄድ ከእነሱ ጋር የመንጻት ሥርዓት ፈጽም፤ ራሳቸውንም እንዲላጩ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ክፈልላቸው። ይህን ካደረግክ በአንተ ላይ የተወራው ሁሉ ከንቱ መሆኑንና አንተም ሕጉን እያከበርክ በሥርዓት እንደምትኖር ሁሉም ሰው ያውቃል።”c—ሥራ 21:23, 24

12. ጳውሎስ የኢየሩሳሌም ሽማግሌዎች ምክር ሲሰጡት እሺ ባይና ተባባሪ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

12 ጳውሎስ የችግሩ ዋና መንስኤ ስለ እሱ የተወራው አሉባልታ ሳይሆን አይሁዳውያን አማኞች ለሙሴ ሕግ ያላቸው ቅንዓት እንደሆነ በመግለጽ መቃወም ይችል ነበር። ይሁን እንጂ አምላክ ያወጣቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች እስካልተጣሱ ድረስ ሽማግሌዎቹ ያሉትን ለማድረግ ፈቃደኛ ሆኗል። ቀደም ሲል “እኔ ራሴ በሕግ ሥር ባልሆንም እንኳ በሕግ ሥር ያሉትን እማርክ ዘንድ በሕግ ሥር ላሉት በሕግ ሥር እንዳለሁ ሆንኩ” በማለት ጽፎ ነበር። (1 ቆሮ. 9:20) በዚህ ወቅት ጳውሎስ ከኢየሩሳሌም ሽማግሌዎች ጋር በመተባበር “በሕግ ሥር” እንዳለ ሆኗል። ከሽማግሌዎች ጋር በመተባበርና እኔ ያልኩት ካልሆነ ብሎ ድርቅ ከማለት በመቆጠብ ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል።—ዕብ. 13:17

ምስሎች፦ 1. ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ያሉ ሽማግሌዎች የሚሰጡትን መመሪያ ሲያዳምጥ። 2. በዘመናችን ሽማግሌዎች ስብሰባ ሲያደርጉ፤ ሽማግሌዎቹ እጃቸውን ሲያወጡ አንድ ወንድም ትኩር ብሎ እየተመለከታቸው ነው።

ጳውሎስ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች እስካልተጣሱ ድረስ የሌሎችን ሐሳብ ይቀበል ነበር። አንተስ?

የሮም ሕግና የሮም ዜጎች

የሮም ባለሥልጣናት በቅኝ ተገዢዎቻቸው አስተዳደራዊ ጉዳዮች ውስጥ ያን ያህል ጣልቃ አይገቡም። በጥቅሉ ሲታይ አይሁዳውያን የሚተዳደሩት በራሳቸው ሕግ ነበር። የሮም ባለሥልጣናት በጳውሎስ ጉዳይ ጣልቃ የገቡት፣ ሐዋርያው ቤተ መቅደሱ ውስጥ በመታየቱ የተፈጠረው ሁከት የከተማዋን ሰላም እንዳያደፈርስ ስለሰጉ ብቻ ነው።

የሮም ዜግነት የሌለው ሰው በሮም ግዛት ውስጥ ያለው መብት ውስን ነበር። ባለሥልጣናቱ የሮም ዜግነት ያላቸውን ሰዎች የሚይዙበት መንገድ ግን ይለያል።f የሮም ዜግነት የሚያስገኛቸው መብቶች አሉ፤ እነዚህ መብቶች በመላው የሮም ግዛት ውስጥ ይከበሩ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ አንድን ሮማዊ ያለፍርድ ማሰር ወይም መደብደብ በሕግ የተከለከለ ነው፤ ይህ ሕጋዊ መብት የሌላቸው ባሪያዎች ብቻ ናቸው። በተጨማሪም የሮም ዜግነት ያላቸው ሰዎች፣ አንድ የአውራጃ ገዢ በትክክል እንዳልፈረደላቸው ከተሰማቸው በሮም ለሚገኘው ንጉሠ ነገሥት ይግባኝ የማለት መብት ነበራቸው።

የሮም ዜግነት ማግኘት የሚቻልባቸው የተለያዩ መንገዶች ነበሩ። የመጀመሪያው በመወለድ ነው። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ንጉሠ ነገሥታት፣ የሮም ዜግነትን ለግለሰቦች ወይም በአንድ ከተማ አሊያም አውራጃ ውስጥ ለሚኖሩ ነፃ ሰዎች በሙሉ ይሰጣሉ፤ ይህን የሚያደርጉት ለሮም መንግሥት ለሰጡት አገልግሎት ወሮታ ለመክፈል ነው። አንድ ባሪያ፣ የሮም ዜጋ ከሆነ ሰው ነፃነቱን በገንዘብ ከገዛ ወይም ሮማዊው ነፃ ካወጣው የሮም ዜግነት ያገኛል፤ በሮማውያን ሠራዊት ውስጥ ሲያገለግል ቆይቶ በጡረታ የተገለለ ወታደርም የሮም ዜግነት ያገኝ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የሮም ዜግነትን መግዛት የሚቻልባቸው ሁኔታዎች የነበሩ ይመስላል። ሮማዊው ሻለቃ ቀላውዴዎስ ሉስዮስ ጳውሎስን “እኔ ይህን የዜግነት መብት የገዛሁት ብዙ ገንዘብ አውጥቼ ነው” ብሎታል። በምላሹም ጳውሎስ “እኔ ግን በመወለድ አገኘሁት” ብሏል። (ሥራ 22:28) ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ከጳውሎስ ወንድ ቅድመ አያቶች አንዱ በሆነ መንገድ የሮም ዜግነት አግኝቶ መሆን አለበት፤ ዜግነቱን ያገኘው እንዴት እንደሆነ ግን በእርግጠኝነት ማወቅ አይቻልም።

f በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. ይሁዳ ውስጥ የሮም ዜግነት ያላቸው ብዙ ሰዎች የነበሩ አይመስልም። በሮም ቅኝ ግዛቶች ውስጥ ለሚኖሩ ለሁሉም ሰዎች የዜግነት መብት የተሰጠው በሦስተኛው መቶ ዘመን ነው።

“ይህ ሰው መኖር የማይገባው” ነው! (የሐዋርያት ሥራ 21:27 እስከ 22:30)

13. (ሀ) አንዳንድ አይሁዳውያን ቤተ መቅደሱ ውስጥ ሁከት ያስነሱት ለምንድን ነው? (ለ) ጳውሎስ ከሞት ሊተርፍ የቻለው እንዴት ነው?

13 ቤተ መቅደሱ ውስጥ ነገሮች እንደታሰበው በሰላም አልተከናወኑም። ስእለቱ የሚፈጸምባቸው ቀናት ሊጠናቀቁ ሲቃረቡ ከእስያ የመጡ አይሁዳውያን ጳውሎስን አዩት፤ ‘ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ሰዎችን ወደ ቤተ መቅደሱ አምጥቷል’ የሚል የሐሰት ክስ በመሰንዘር ሁከት አስነሱ። ሮማዊው ሻለቃ ጣልቃ ባይገባ ኖሮ ጳውሎስን ደብድበው ይገድሉት ነበር። ሻለቃው ጳውሎስን በቁጥጥር ሥር አዋለው። ጳውሎስ በዚህ ወቅት የተነጠቀውን ነፃነት መልሶ የሚያገኘው ከአራት ዓመት በኋላ ነው። የተጋረጠበት አደጋም በዚሁ ቢያበቃ አንድ ነገር ነበር፤ ግን ይህ አልሆነም። ሻለቃው በጳውሎስ ላይ ጥቃት የሰነዘሩት ለምን እንደሆነ ሲጠይቃቸው አይሁዳውያኑ የተለያዩ ክሶች አቀረቡ። ሻለቃው ከጫጫታው የተነሳ ምንም የተጨበጠ ነገር ማግኘት አልቻለም። ውጥረቱ እየተባባሰ ሲመጣ ወታደሮቹ ጳውሎስን ተሸክመው ወሰዱት። ጳውሎስና ሮማውያኑ ወታደሮች ወደ ጦር ሰፈሩ ሲቃረቡ ጳውሎስ ሻለቃውን “ለሕዝቡ እናገር ዘንድ እንድትፈቅድልኝ እለምንሃለሁ” አለው። (ሥራ 21:39) ሻለቃው በሐሳቡ በተስማማ ጊዜ ጳውሎስ በድፍረት ለእምነቱ የመከላከያ ሐሳብ ማቅረብ ጀመረ።

14, 15. (ሀ) ጳውሎስ ለአይሁዳውያኑ ምን አስረዳቸው? (ለ) ሮማዊው ሻለቃ አይሁዳውያኑ የተቆጡበትን ምክንያት ለማወቅ ምን እርምጃዎች ወሰደ?

14 ጳውሎስ ንግግሩን የጀመረው “የማቀርበውን የመከላከያ መልስ ስሙ” በማለት ነው። (ሥራ 22:1) በዕብራይስጥ ቋንቋ ሲናገር ሕዝቡ ጸጥ ብለው ማዳመጥ ጀመሩ። ጳውሎስ፣ የክርስቶስ ተከታይ የሆነው ለምን እንደሆነ በግልጽ አስረዳቸው። አይሁዳውያኑ ከፈለጉ ሊያረጋግጧቸው የሚችሉ አንዳንድ ነጥቦችን በዘዴ ጠቀሰ። የተማረው ገማልያል በተባለ ስመ ጥር መምህር እግር ሥር ተቀምጦ ነው፤ የክርስቶስን ተከታዮች ያሳድድም ነበር፤ በዚያ ከተገኙት ሰዎች አንዳንዶቹ ይህን ሳያውቁ አይቀሩም። ይሁን እንጂ ወደ ደማስቆ እየተጓዘ ሳለ፣ ከሞት የተነሳው ክርስቶስ በራእይ ተገልጦለት አናገረው። ከጳውሎስ ጋር የሚጓዙት ሰዎች ኃይለኛ ብርሃን አይተዋል፣ ድምፅም ሰምተዋል፤ ምን እንደተባለ ግን አላስተዋሉም። (ሥራ 9:7፤ 22:9 የግርጌ ማስታወሻ) ጳውሎስ ከዚያ በኋላ ማየት ስለተሳነው አብረውት የነበሩት ሰዎች እየመሩ ወደ ደማስቆ ወሰዱት። እዚያ ሲደርስ ሐናንያ የተባለ በአካባቢው ባሉ አይሁዳውያን ዘንድ የታወቀ ሰው በተአምር የጳውሎስን ዓይን አበራለት።

15 ቀጥሎም ጳውሎስ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ከተመለሰ በኋላ ኢየሱስ ቤተ መቅደሱ ውስጥ እንደተገለጠለት ተናገረ። አይሁዳውያኑ ይህን ሲሰሙ በጣም ተናደው “ይህ ሰው መኖር የማይገባው ስለሆነ ከምድር ገጽ ይወገድ!” ብለው ጮኹ። (ሥራ 22:22) ሻለቃው የጳውሎስን ሕይወት ለማትረፍ ሲል ወደ ጦር ሰፈሩ እንዲያስገቡት አደረገ። አይሁዳውያኑ በጳውሎስ ላይ ይህን ያህል ያስቆጣቸው ምን እንደሆነ ማወቅ ስለፈለገም እየተገረፈ እንዲመረመር አዘዘ። ይሁንና ጳውሎስ ሕጋዊ ከለላ ማግኘት የሚችልበትን እርምጃ ወሰደ፤ የሮም ዜጋ መሆኑን አሳወቀ። በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ አገልጋዮችም የሕግ ከለላ ለማግኘት በሚያስችሏቸው ዝግጅቶች በመጠቀም ለእምነታቸው ጥብቅና ይቆማሉ። (“የሮም ሕግና የሮም ዜጎች” የሚለውን ሣጥን እንዲሁም “በዘመናችን የተደረጉ የሕግ ፍልሚያዎች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ሻለቃው፣ ጳውሎስ ሮማዊ መሆኑን ሲሰማ ስለ እሱ መረጃ ለማግኘት ሌላ መንገድ መጠቀም እንዳለበት ተገነዘበ። በነጋታው የአይሁዳውያን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሆነው የሳንሄድሪን ሸንጎ እንዲሰበሰብ አዘዘ፤ ጳውሎስንም ፊታቸው አቀረበው።

በዘመናችን የተደረጉ የሕግ ፍልሚያዎች

እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ሁሉ በዘመናችን ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችም በስብከት ሥራቸው ላይ የሚጣሉ እገዳዎች እንዲነሱላቸው ለማድረግ ሲሉ ማንኛውንም ሕጋዊ መንገድ ይጠቀማሉ። ‘ለምሥራቹ ለመሟገትና በሕግ የጸና እንዲሆን ለማድረግ’ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ያደርጋሉ።—ፊልጵ. 1:7

በ1920ዎቹና በ1930ዎቹ ዓመታት በመቶዎች የሚቆጠሩ ወንድሞች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በማሰራጨታቸው ታስረዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በ1926 በጀርመን 897 ወንድሞች በቁጥጥር ሥር ውለው ፍርዳቸውን እየተጠባበቁ ነበር። በወቅቱ በርካታ የፍርድ ቤት ሙግቶች ስለነበሩ በጀርመን ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የሕግ ክፍል ማቋቋም አስፈልጓል። በ1930ዎቹ ዓመታት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ብቻ በየዓመቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወንድሞች ከቤት ወደ ቤት በመስበካቸው ምክንያት ይታሰሩ ነበር። በ1936 ይህ አኃዝ ወደ 1,149 አሻቀበ። ለወንድሞች የሕግ ምክር አገልግሎት መስጠት እንዲቻል በዩናይትድ ስቴትስም የሕግ ክፍል ተቋቋመ። ከ1933 እስከ 1939 የሩማንያ የይሖዋ ምሥክሮች 530 ክሶች ተመሥርተውባቸዋል። ይሁን እንጂ ለሩማንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ በማለት ብዙ ጊዜ ጥሩ ውጤት ማግኘት ተችሏል። በሌሎች በርካታ አገሮችም ተመሳሳይ ሁኔታዎች ተከስተዋል።

አንዳንድ ክርስቲያኖች ደግሞ ፍርድ ቤት የቀረቡት፣ የገለልተኝነት አቋማቸውን በሚያስጥሱ እንቅስቃሴዎች ለመካፈል ሕሊናቸው እንደማይፈቅድላቸው በመግለጻቸው ነው። (ኢሳ. 2:2-4፤ ዮሐ. 17:14) ተቃዋሚዎች፣ ‘በመንግሥት ላይ ዓመፅ ያነሳሳሉ’ የሚል የሐሰት ክስ በወንድሞች ላይ ሰንዝረዋል፤ ይህም ሥራቸው ሙሉ በሙሉ እንዲታገድ ያደረገበት ጊዜ አለ። ይሁንና ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ በርካታ መንግሥታት፣ የይሖዋ ምሥክሮች ምንም ዓይነት ስጋት እንደማይፈጥሩባቸው ተገንዝበዋል።g

g የይሖዋ ምሥክሮች በተለያዩ አገሮች ስላገኟቸው የፍርድ ቤት ድሎች ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የአምላክ መንግሥት እየገዛ ነው! የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 15 እና የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 30 ተመልከት።

“ፈሪሳዊ ነኝ” (የሐዋርያት ሥራ 23:1-10)

16, 17. (ሀ) ጳውሎስ በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት ሲናገር ምን እንደተከሰተ ግለጽ። (ለ) ጳውሎስ በጥፊ በተመታበት ወቅት ትሕትና ያሳየው እንዴት ነው?

16 ጳውሎስ በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት ያቀረበውን የመከላከያ ሐሳብ የጀመረው እንዲህ በማለት ነው፦ “ወንድሞች፣ እኔ እስከዚህ ቀን ድረስ በአምላክ ፊት ሙሉ በሙሉ ንጹሕ ሕሊና ይዤ ተመላልሻለሁ።” (ሥራ 23:1) ሆኖም ንግግሩን ከዚያ በላይ መቀጠል አልቻለም። ዘገባው አክሎ እንደሚናገረው “ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ፣ ጳውሎስ አጠገብ የቆሙት ሰዎች አፉን እንዲመቱት አዘዘ።” (ሥራ 23:2) እንዴት ያለ ንቀት ነው! ደግሞስ እንዴት ያለ ፍርደ ገምድልነት ነው! የመከላከያ ሐሳብ ለማቅረብ እንኳ ዕድል ሳይሰጠው ውሸታም ያለው ያህል ነው! ጳውሎስ የሚከተለውን ምላሽ መስጠቱ ምንም አያስደንቅም፦ “አንተ በኖራ የተለሰንክ ግድግዳ! አምላክ አንተን ይመታሃል። በሕጉ መሠረት በእኔ ላይ ለመፍረድ ተቀምጠህ ሳለ አንተ ራስህ ሕጉን በመጣስ እንድመታ ታዛለህ?”—ሥራ 23:3

17 በዚህ ጊዜ በቦታው ከቆሙት መካከል አንዳንዶቹ ደነገጡ! የደነገጡት ግን ጳውሎስ በመመታቱ ሳይሆን በሰጠው መልስ ነበር። “የአምላክን ሊቀ ካህናት ትሳደባለህ?” አሉት። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ፣ የሰጠው መልስ በትሕትናና ለሕጉ አክብሮት በማሳየት ረገድ ጥሩ ትምህርት የሚሆናቸው ነው። “ወንድሞች፣ እኔ እኮ ሊቀ ካህናት መሆኑን አላወቅኩም። ምክንያቱም ‘በሕዝብህ ገዢ ላይ ክፉ ቃል አትናገር’ ተብሎ ተጽፏል” አላቸው።d (ሥራ 23:4, 5፤ ዘፀ. 22:28) አሁን ጳውሎስ ለየት ያለ ዘዴ ተጠቀመ። የሳንሄድሪን አባላት ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን መሆናቸውን ስላወቀ እንዲህ አላቸው፦ “ወንድሞች፣ እኔ ከፈሪሳውያን የተወለድኩ ፈሪሳዊ ነኝ። ለፍርድ የቀረብኩት በሙታን ትንሣኤ ተስፋ በማመኔ ነው።”—ሥራ 23:6

አንድ ወንድም ለአንድ ቄስ እየመሠከረ ነው፤ ቄሱ በራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንድን ጥቅስ በትኩረት እየተመለከተ ነው።

ከእኛ የተለየ ሃይማኖታዊ አመለካከት ካላቸው ሰዎች ጋር ስንወያይ እንደ ጳውሎስ በጋራ የሚያስማሙንን ነጥቦች እናነሳለን

18. ጳውሎስ ፈሪሳዊ ነኝ ያለው ለምንድን ነው? እኛስ ከሰዎች ጋር ስንወያይ ተመሳሳይ ዘዴ ልንጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?

18 ጳውሎስ ፈሪሳዊ ነኝ ያለው ለምንድን ነው? ‘ከፈሪሳውያን ስለተወለደ’ ማለትም የፈሪሳውያን ሃይማኖታዊ ቡድን አባል ከሆነ ቤተሰብ ስለመጣ ነው። ከዚህ የተነሳ ብዙዎች አሁንም የሚያዩት እንደ ፈሪሳዊ ነው።e ይሁን እንጂ ጳውሎስ ይህን ሲል ፈሪሳውያን ስለ ትንሣኤ ያላቸውን አመለካከት ይቀበላል ማለት ነው? ፈሪሳውያን፣ ሰው ሲሞት ነፍሱ እንደማትሞት እንዲሁም የጻድቅ ነፍስ እንደገና ሥጋዊ አካል ለብሳ እንደምትኖር ያምናሉ። ጳውሎስ እንዲህ ያለ አመለካከት አልነበረውም። እሱ የሚያምነው ኢየሱስ ያስተማረውን ትንሣኤ ነው። (ዮሐ. 5:25-29) ይሁንና ጳውሎስ ከፈሪሳውያን ጋር የሚያስማማው ነገር አለ፤ ከሰዱቃውያን በተቃራኒ ከሞት ባሻገር የመኖር ተስፋ እንዳለ ያምናል። እኛም የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶችን ከሚከተሉ ሰዎች ጋር ስንወያይ ተመሳሳይ ዘዴ መጠቀም እንችላለን። ልክ እንደ እነሱ እኛም በአምላክ እንደምናምን ልንገልጽላቸው እንችላለን። እርግጥ እነሱ የሚያምኑት በሥላሴ ሊሆን ይችላል፤ እኛ ደግሞ የምናምነው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተጠቀሰው አምላክ ነው። ይሁንና እነሱም እኛም በአምላክ ማመናችን ያመሳስለናል።

19. የሳንሄድሪን ሸንጎ በትርምስ የተበተነው ለምንድን ነው?

19 ጳውሎስ የተናገረው ሐሳብ በሳንሄድሪን ሸንጎ መካከል ክፍፍል ፈጠረ። ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “ከፍተኛ ሁከት ተፈጠረ፤ ከፈሪሳውያን ወገን የሆኑ አንዳንድ ጸሐፍት ተነስተው እንዲህ ሲሉ አጥብቀው ተከራከሩ፦ ‘በዚህ ሰው ላይ ምንም ጥፋት አላገኘንም፤ መንፈስ ወይም መልአክ አናግሮት ከሆነ ግን . . . ።’” (ሥራ 23:9) ጳውሎስን መልአክ አናግሮት ይሆናል የሚለው ሐሳብ በራሱ ሰዱቃውያንን የሚያስቆጣ ነው! ምክንያቱም በመላእክት አያምኑም። (“ሰዱቃውያንና ፈሪሳውያን” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ውዝግቡ እየከረረ ሲሄድ ሮማዊው ሻለቃ በድጋሚ ጣልቃ በመግባት ሐዋርያውን ታደገው። (ሥራ 23:10) ይሁንና ጳውሎስ አሁንም ቢሆን አደጋ አጥልቶበታል። ከዚህ በኋላስ ምን ያጋጥመው ይሆን? ይህን በሚቀጥለው ምዕራፍ እንመለከታለን።

ሰዱቃውያንና ፈሪሳውያን

የአይሁዳውያን የአስተዳደር ምክር ቤትና ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሆነው ሳንሄድሪን በዋነኝነት የተዋቀረው በሁለት ተቀናቃኝ ቡድኖች ነው፤ እነሱም ሰዱቃውያንና ፈሪሳውያን ናቸው። ፍላቭየስ ጆሴፈስ የተባለው የመጀመሪያው መቶ ዘመን የታሪክ ምሁር በእነዚህ ሁለት ቡድኖች መካከል ያለውን መሠረታዊ ልዩነት አብራርቷል፤ እንደ ጆሴፈስ አባባል፣ ፈሪሳውያን በሕዝቡ ላይ በርካታ ወጎችን ይጭናሉ፤ ሰዱቃውያን ግን በሙሴ ሕግ ውስጥ ያሉትን ትእዛዛት መጠበቅ ብቻ በቂ እንደሆነ ያምናሉ። ይሁን እንጂ ሁለቱም ቡድኖች ኢየሱስን ለመቃወም ግንባር ፈጥረዋል።

የሙሴን ሕግ በጥብቅ የሚከተሉት ሰዱቃውያን በካህናቱ ዘንድ ከፍተኛ ተደማጭነት የነበራቸው ይመስላል፤ ሊቀ ካህናት የነበሩት ሐናና ቀያፋም የዚህ ሃይማኖታዊ ቡድን አባላት ሳይሆኑ አይቀሩም። (ሥራ 5:17) ይሁንና ጆሴፈስ በእነሱ ትምህርት “የሚሳቡት ሀብታሞች ብቻ” እንደሆኑ ተናግሯል።

በሌላ በኩል ደግሞ ፈሪሳውያን በተራው ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደር ችለው ነበር። ሆኖም ሕዝቡ የሙሴን ሕግ መጠበቅ ከባድ እንዲሆንበት አድርገው ነበር፤ ለምሳሌ ስለ መንጻት ሥርዓት ያወጡት ሕግ በጣም አስቸጋሪ ነበር። ከሰዱቃውያን በተለየ ፈሪሳውያን የሰዎች ዕድል አስቀድሞ እንደተወሰነ ይናገራሉ፤ ሰው ሲሞት ነፍሱ እንደማትሞት፣ ከዚህ ይልቅ የቀድሞ ሥራው ታይቶ ነፍሱ ሽልማት ወይም ቅጣት እንደምትቀበል ያምናሉ።

a በወቅቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ነበሩ፤ የሁሉንም መንፈሳዊ ፍላጎት ለማሟላት በግል መኖሪያ ቤቶች የሚሰበሰቡ በርካታ ጉባኤዎች ማቋቋም ሳያስፈልግ አልቀረም።

b ሐዋርያው ጳውሎስ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ደብዳቤ ጻፈ፤ በደብዳቤው ላይ የአዲሱን ቃል ኪዳን ብልጫ አስረግጦ ተናግሯል። አዲሱ ቃል ኪዳን አሮጌውን የሚተካ እንደሆነ በግልጽ አስረድቷል። ጳውሎስ፣ እነዚያ ክርስቲያኖች ለአይሁዳውያን ተቃዋሚዎቻቸው መልስ ለመስጠት የሚያስችሏቸው አሳማኝ ማስረጃዎች አቅርቧል፤ ከዚህም ሌላ ጳውሎስ ያቀረባቸው ጠንካራ ነጥቦች ለሙሴ ሕግ አላስፈላጊ ትኩረት የሚሰጡ ክርስቲያኖችን እምነት አጠናክረው መሆን አለበት።—ዕብ. 8:7-13

c አንዳንድ ምሁራን፣ እነዚህ ሰዎች የናዝራዊነት ስእለት እንደነበረባቸው ይናገራሉ። (ዘኁ. 6:1-21) እርግጥ ነው፣ ይህን ስእለት የሚያካትተው የሙሴ ሕግ አሁን ተሽሯል። ይሁንና እነዚህ ሰዎች የተሳሉት ለይሖዋ በመሆኑ ጳውሎስ ስእለቱን መፈጸማቸው ስህተት እንዳልሆነ አስቦ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም የሰዎቹን ወጪ መክፈሉና አብሯቸው መሄዱ ምንም ስህተት የለውም። ሰዎቹ የተሳሉት ምን ዓይነት ስእለት እንደሆነ በእርግጠኝነት ማወቅ አንችልም። ይሁንና ብዙውን ጊዜ ናዝራውያን ከኃጢአት ለመንጻት የእንስሳት መሥዋዕት ያቀርቡ እንደነበር ይታወቃል፤ የሰዎቹ ስእለት ምንም ዓይነት ይሁን፣ ጳውሎስ እንዲህ ያለውን መሥዋዕት ለማቅረብ እንደማይስማማ ጥያቄ የለውም። ፍጹም የሆነው የክርስቶስ መሥዋዕት ከቀረበ ወዲህ የእንስሳት መሥዋዕቶች ኃጢአትን ማስተሰረይ አይችሉም። ጳውሎስ ያደረገው ነገር ምንም ይሁን ምን፣ ሕሊናውን የሚያስጥስ ነገር ለማድረግ እንደማይስማማ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

d አንዳንዶች እንደሚሉት ከሆነ ጳውሎስ ሊቀ ካህናቱን ያላወቀው አጥርቶ የማየት ችግር ስለነበረበት ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ ለረጅም ጊዜ በኢየሩሳሌም ስላልነበረ በወቅቱ ያለው ሊቀ ካህናት ማን እንደሆነ አላወቀ ይሆናል። አሊያም ብዙ ሰው ስለነበር እንዲመታ ትእዛዝ የሰጠው ማን እንደሆነ መለየት ስላቃተው ሊሆን ይችላል።

e በ49 ዓ.ም. ሐዋርያትና ሽማግሌዎች፣ ‘አሕዛብ የሙሴን ሕግ ማክበር አለባቸው ወይም የለባቸውም’ በሚለው ጉዳይ ላይ ተወያይተው ነበር፤ ከመካከላቸው አንዳንዶቹ “ከፈሪሳውያን ሃይማኖታዊ ቡድን መካከል አማኞች የሆኑ” ተብለዋል። (ሥራ 15:5) እንዲህ የተባለው እነዚህ አማኞች ከዚህ ቀደም ፈሪሳዊ ስለነበሩ ሊሆን ይችላል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ