ወጣት ወንድሞች፣ የኃላፊነት ቦታ ላይ ለመድረስ እየተጣጣራችሁ ነው?
1. ታዳጊ የሆነ አንድ ወጣት በ1 ጢሞቴዎስ 3:1 ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ያለበት ከመቼ ጀምሮ ነው?
1 የኃላፊነት ቦታ ላይ ለመድረስ “የሚጣጣር ማንኛውም ሰው መልካም ሥራን ይመኛል።” (1 ጢሞ. 3:1) በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት እነዚህ ቃላት ወንድሞች በጉባኤ ውስጥ ባሉ የአገልግሎት መብቶች ላይ ለመድረስ የሚያስፈልገውን ብቃት ለማሟላት እንዲጣጣሩ የሚያበረታቱ ናቸው። ይህን ለማድረግ የግድ ትልቅ ሰው እስክትሆን ድረስ መጠበቅ አለብህ? በፍጹም፣ እንዲያውም ገና በለጋ ዕድሜህ ይህን ማድረጉ በጣም የተሻለ ነው። እንዲህ ስታደርግ ሥልጠና የምታገኝ ከመሆኑም በላይ ወደፊት በዕድሜ ከፍ ስትል የጉባኤ አገልጋይ ሆነህ ለመሾም ብቃት እንዳለህ ታስመሠክራለህ። (1 ጢሞ. 3:10) የተጠመቅህ ታዳጊ ወጣት ከሆንክ የኃላፊነት ቦታ ላይ ለመድረስ መጣጣር የምትችለው እንዴት ነው?
2. የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ማዳበር የሚቻለው እንዴት ነው? ይህን ባሕርይ በተግባር ማሳየት የሚቻለውስ እንዴት ነው?
2 የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ፦ የኃላፊነት ቦታ ላይ ለመድረስ የምትጣጣረው ለመልካም ሥራ እንጂ ማዕረግ ለማግኘት እንዳልሆነ አስታውስ። ስለዚህ ወንድሞችንና እህቶችን የመርዳት ፍላጎት አዳብር። ይህን ማድረግ የምትችልበት አንዱ መንገድ ኢየሱስ በተወው ምሳሌ ላይ ማሰላሰል ነው። (ማቴ. 20:28፤ ዮሐ. 4:6, 7፤ 13:4, 5) ሌሎችን የማገልገል ፍላጎት በውስጥህ እንዲያሳድርብህ ይሖዋን ጠይቀው። (1 ቆሮ. 10:24) በዕድሜ የገፉ ወይም የአቅም ገደብ ያለባቸውን የጉባኤህን አባላት መርዳት ትችል ይሆን? አዳራሹን ማስዋብንና መጠገንን ጨምሮ የአምልኮ ቦታዎችን ለመንከባከብ የሚደረጉ ሌሎች ዝግጅቶችን ለመደገፍ ራስህን በፈቃደኝነት ታቀርባለህ? በቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ትምህርት ቤት ክፍል እንዲያቀርቡ የተመደቡት ወንድሞች በማይኖሩበት ወቅት ተክተህ ለማቅረብ ፈቃደኛ ነህ? ሌሎችን ለመርዳት ራስህን ማቅረብህ ደስታ ያስገኝልሃል።—ሥራ 20:35
3. መንፈሳዊ ሰው መሆን ምን ጥቅሞች አሉት? መንፈሳዊነትን ማዳበር የሚቻለውስ እንዴት ነው?
3 መንፈሳዊነት፦ በጉባኤ ውስጥ ለማገልገል በዋነኝነት የሚያስፈልገው ልዩ ተሰጥኦ ወይም ተፈጥሯዊ ችሎታ ሳይሆን መንፈሳዊነት ነው። መንፈሳዊ የሆነ ሰው ነገሮችን ይሖዋና ኢየሱስ በሚያዩበት መንገድ ለማየት ይጥራል። (1 ቆሮ. 2:15, 16) “የመንፈስ ፍሬ” እንዳለው ያሳያል። (ገላ. 5:22, 23) እንዲሁም ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የሚያስቀድም ቀናተኛ ወንጌላዊ ነው። (ማቴ. 6:33) ጥሩ የግል ጥናት ልማድ በማዳበር መንፈሳዊ ባሕርያት እንዲኖሩህ ማድረግ ትችላለህ። ይህም መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ ማንበብን፣ እያንዳንዱን የመጠበቂያ ግንብና የንቁ! መጽሔት እትም ማንበብን እንዲሁም ለጉባኤ ስብሰባዎች ተዘጋጅቶ መሄድን ይጨምራል። (መዝ. 1:1, 2፤ ዕብ. 10:24, 25) ጳውሎስ ወጣቱ ጢሞቴዎስ መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርግ ሲያበረታታው “ለምታስተምረው ትምህርት ምንጊዜም ትኩረት ስጥ” በማለት ጽፎለታል። (1 ጢሞ. 4:15, 16) ስለዚህ በቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ትምህርት ቤት ክፍል እንድታቀርብ ስትመደብ ጥሩ አድርገህ ለማቅረብ የምትችለውን ሁሉ አድርግ። አገልግሎት ከመውጣትህ በፊት ተዘጋጅ እንዲሁም አዘውትረህ በአገልግሎት ተካፈል። አቅኚ እንደመሆን ወይም ቤቴል ገብቶ እንደማገልገል አሊያም ለነጠላ ወንድሞች በተዘጋጀ ትምህርት ቤት እንደመካፈል ያሉ መንፈሳዊ ግቦች አውጥተህ እዚያ ላይ ለመድረስ ጥረት አድርግ። መንፈሳዊ ሰው መሆንህ “ከወጣትነት ዕድሜ ጋር ተያይዘው ከሚመጡ ምኞቶች” ለመሸሽ ይረዳሃል።—2 ጢሞ. 2:22
4. እምነት የሚጣልበት ሰው መሆን ምን ጥቅም አለው?
4 እምነት የሚጣልበትና ታማኝ፦ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ችግር ላይ ለነበሩት ክርስቲያኖች ምግብ የማከፋፈል ሥራ የተሰጣቸው ወንድሞች “የተመሠከረላቸው” ነበሩ፤ እነዚህ ወንድሞች እምነት የሚጣልባቸውና ታማኝ በመሆን ረገድ ጥሩ ስም እንዳተረፉ ምንም ጥርጥር የለውም። በዚህ የተነሳ ሐዋርያቱ እነዚህ ወንድሞች ‘ሥራውን በአግባቡ ይሠሩት ይሆን?’ የሚል ስጋት አልነበራቸውም። ይህ ደግሞ ሐዋርያቱ ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ አስችሏቸዋል። (ሥራ 6:1-4) አንተም በጉባኤ ውስጥ አንድ ሥራ ሲሰጥህ ጥሩ አድርገህ ለመሥራት የምትችለውን ያህል ጥረት አድርግ። መርከብ እንዲገነባ የተሰጠውን መመሪያ በጥንቃቄ የጠበቀውን የኖኅን ምሳሌ ተከተል። (ዘፍ. 6:22) ታማኝነት፣ ይሖዋ ከፍ አድርጎ የሚመለከተው ባሕርይ ነው፤ ይህን ባሕርይ የምታዳብር ከሆነ መንፈሳዊ ብስለት እንዳለህ ታሳያለህ።—1 ቆሮ. 4:2፤ “ሥልጠና መስጠት ያለው ጥቅም” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
5. ወጣት ወንድሞች የኃላፊነት ቦታ ላይ ለመድረስ መጣጣር ያለባቸው ለምንድን ነው?
5 ይሖዋ በትንቢት እንደተናገረው ሰዎችን የመሰብሰቡን ሥራ እያፋጠነው ነው። (ኢሳ. 60:22) በየዓመቱ ከሩብ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ይጠመቃሉ። በርካታ አዳዲስ ሰዎች ወደ እውነት እየመጡ ከመሆኑ አንጻር የጉባኤ ኃላፊነቶችን የሚሸከሙ ብቃት ያላቸው መንፈሳዊ ወንዶች ያስፈልጋሉ። በይሖዋ አገልግሎት የሚሠራው ሥራ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ በዝቷል። (1 ቆሮ. 15:58) ታዲያ እናንት ወጣት ወንድሞች፣ የኃላፊነት ቦታ ላይ ለመድረስ እየተጣጣራችሁ ነው? ከሆነ በእርግጥም እጅግ መልካም የሆነ ሥራ እየተመኛችሁ ነው!
[በገጽ 2 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
በርካታ አዳዲስ ሰዎች ወደ እውነት እየመጡ ከመሆኑ አንጻር የጉባኤ ኃላፊነቶችን የሚሸከሙ ብቃት ያላቸው መንፈሳዊ ወንዶች ያስፈልጋሉ
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ሥልጠና መስጠት ያለው ጥቅም
ሽማግሌዎች ብቃት ላላቸው ታዳጊ ወጣት ወንድሞች ሥራና ሥልጠና የሚሰጧቸው ከሆነ ይጠቀማሉ። አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች ከስብሰባ በኋላ መድረክ ላይ ቁጭ ብሎ ለአንድ አስፋፊ ማበረታቻ እየሰጠ ነበር። ከዚያም አጠገባቸው አንድ ወጣት ልጅ እንደቆመ ሲያይ ሊያናግረው እየጠበቀው እንደሆነ ጠየቀው። ወጣቱ ወንድም ግን ምንጊዜም ስብሰባ ካለቀ በኋላ መድረኩን እንዲያጸዳ መመደቡን ገለጸለት። ወላጆቹ ወደ ቤት ለመሄድ የተዘጋጁ ቢሆንም እሱ ግን የተሰጠውን ሥራ ሳይሠራ መሄድ አልፈለገም። የወረዳ የበላይ ተመልካቹ በጣም በመደሰት መድረኩን ለቀቀለት። የወረዳ የበላይ ተመልካቹ እንዲህ ብሏል፦ “በዚያ ጉባኤ ያሉ ሽማግሌዎች ብቃት ላላቸው ወጣት ወንድሞች የጉባኤ ሥራዎችን በመስጠት የማሠልጠን ልማድ አላቸው። በዚህም ምክንያት ጉባኤውን በምጎበኝበት ወቅት ብዙውን ጊዜ ወጣት ወንድሞች አገልጋይ ሆነው እንዲሾሙ የድጋፍ ሐሳብ ያቀርባሉ።”