‘የአምላክ ፈቃድ ይሁን’
1. የ2012 የአገልግሎት ዓመት የልዩ ስብሰባ ቀን ፕሮግራም ጭብጥ ምንድን ነው? ይህን ጉዳይ መመርመራችን አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው?
1 የተፈጠርነው የይሖዋ ፈቃድ ስለሆነ ነው። (ራእይ 4:11) በመሆኑም የተፈጠርንበት ዓላማ ግቡን እንዲመታ የአምላክን ፈቃድ መማርና በሥራ ላይ ማዋል ይኖርብናል። “የሥጋችንንና የሐሳባችንን ፈቃድ” እንድናደርግ ወይም “የአሕዛብን ፈቃድ” እንድንፈጽም ከሚገፋፋን ውስጣዊ ስሜት ጋር መታገል ስለሚያስፈልገን የአምላክን ፈቃድ ማድረግ የምናስበውን ያህል ቀላል አይደለም። (ኤፌ. 2:3፤ 1 ጴጥ. 4:3፤ 2 ጴጥ. 2:10) የአምላክን እርዳታ ካላገኘን ‘ዲያብሎስ የእሱን ፈቃድ እንድናደርግ ሕያዋን እንዳለን አጥምዶ ሊይዘን’ ይችላል። (2 ጢሞ. 2:26) የ2012 የአገልግሎት ዓመት የልዩ ስብሰባ ቀን ፕሮግራማችን፣ እያንዳንዳችን በናሙናው ጸሎት ላይ ከተካተቱት ሦስት ዋና ዋና ልመናዎች መካከል አንዱ ከሆነው ማለትም ‘ፈቃድህ ይሁን’ ከሚለው ልመና ጋር ተስማምተን መኖር እንድንችል ይረዳናል። (ማቴ. 6:9, 10) የስብሰባው ጭብጥ “የአምላክ ፈቃድ ይሁን” የሚል ነው።
2. በፕሮግራሙ ወቅት መልስ የሚያገኙት ጥያቄዎች የትኞቹ ናቸው?
2 መልስ የሚያገኙ ጥያቄዎች፦ ትምህርቱን በምታዳምጡበት ወቅት ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ሞክሩ፦ የአምላክን ቃል የመስማትን ያህል አስፈላጊ የሆነው ሌላው ነገር ምንድን ነው? አምላክ ለእኛ ያለው ፈቃድ ምን እንደሆነ ማስተዋል የምንችለው እንዴት ነው? ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ለመስበክ ፈቃደኛ መሆን ያለብን ለምንድን ነው? አርኪና አስደሳች የሆነ ሕይወት መምራት የምትችሉት እንዴት ነው? ወጣቶች፣ ለይሖዋ በተግባር ልታሳዩት የሚገባው ነገር ምንድን ነው? የአምላክን ፈቃድ ማድረጋችን ምን ወሮታ ያስገኝልናል? ሌሎችን ማነጻችንና ማበረታታታችን አጣዳፊ የሆነው ለምንድን ነው?
3. ከልዩ ስብሰባው ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
3 በስብሰባው ላይ ለመገኘት ጥረት አድርጉ እንዲሁም ፕሮግራሙን በጥሞና ተከታተሉ። በስብሰባው ላይ አንድ የቤቴል ተወካይ ወይም ተጓዥ የበላይ ተመልካች፣ ጎብኚ ተናጋሪ ሆኖ ሊገኝ ይችላል። ከስብሰባው በፊትና በኋላ ከእሱም ሆነ ከሚስቱ (ያገባ ከሆነ) ጋር ለመጫወት ነፃነት ይሰማችሁ። ወደ ቤት ስትመለሱ ደግሞ በስብሰባው ላይ የሰማችሁትን ትምህርት እንዳትረሱ ትምህርቱን በቤተሰብም ሆነ በግለሰብ ደረጃ በመከለስ ከአምላክ ፈቃድ ጋር ይበልጥ ተስማምታችሁ መኖር ስለምትችሉበት መንገድ ለማሰብ ጥረት አድርጉ።—ያዕ. 1:25
4. በሕይወታችን ውስጥ ከሁሉ አስቀድመን የአምላክን ፈቃድ ማድረግ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
4 የራሳቸውን ፍላጎት የሚያሳድዱና ለይሖዋ ፈቃድ ለመገዛት እምቢተኛ የሆኑ ሰዎች ሁሉ በቅርቡ ይጠፋሉ። (1 ዮሐ. 2:17) ይሖዋ በሕይወታችን ውስጥ ከሁሉ አስቀድመን የእሱን ፈቃድ እንድናደርግ እኛን ለመርዳት ሲል ይህን ወቅታዊ ትምህርት ስላዘጋጀልን ምንኛ አመስጋኞች ነን!