-
ማቴዎስ 20:29-34አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
-
-
29 ከኢያሪኮ ወጥተው እየሄዱ ሳሉ እጅግ ብዙ ሕዝብ ተከተለው። 30 በዚህ ጊዜ መንገድ ዳር የተቀመጡ ሁለት ዓይነ ስውሮች ኢየሱስ በዚያ እያለፈ መሆኑን ሲሰሙ “ጌታ ሆይ፣ የዳዊት ልጅ፣ ምሕረት አድርግልን!” እያሉ ጮኹ።+ 31 ሆኖም ሕዝቡ ዝም እንዲሉ ገሠጿቸው፤ እነሱ ግን “ጌታ ሆይ፣ የዳዊት ልጅ፣ ምሕረት አድርግልን!” እያሉ ይበልጥ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ጮኹ። 32 ኢየሱስም ቆም ብሎ ጠራቸውና “ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። 33 እነሱም “ጌታ ሆይ፣ ዓይናችንን አብራልን” አሉት። 34 ኢየሱስም በጣም አዘነላቸውና ዓይኖቻቸውን ዳሰሰ፤+ ወዲያውኑም ማየት ቻሉ፤ ከዚያም ተከተሉት።
-
-
ሉቃስ 18:35-43አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
-
-
35 ኢየሱስ ወደ ኢያሪኮ እየተቃረበ ሳለ አንድ ዓይነ ስውር መንገድ ዳር ተቀምጦ ይለምን ነበር።+ 36 ዓይነ ስውሩም ብዙ ሕዝብ በዚያ ሲያልፍ ሰምቶ ስለ ሁኔታው ይጠይቅ ጀመር። 37 ሰዎቹም “የናዝሬቱ ኢየሱስ በዚህ እያለፈ ነው!” ብለው ነገሩት። 38 በዚህ ጊዜ “ኢየሱስ ሆይ፣ የዳዊት ልጅ፣ ምሕረት አድርግልኝ!” ሲል ጮኸ። 39 ከፊት ከፊት የሚሄዱትም ሰዎች ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እሱ ግን “የዳዊት ልጅ ሆይ፣ ምሕረት አድርግልኝ!” እያለ ይበልጥ መጮኹን ቀጠለ። 40 ኢየሱስም ቆመና ሰውየውን ወደ እሱ እንዲያመጡት አዘዘ። ሰውየው ወደ እሱ በቀረበ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ጠየቀው፦ 41 “ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?” እሱም “ጌታ ሆይ፣ የዓይኔን ብርሃን መልስልኝ” አለው። 42 ስለዚህ ኢየሱስ “የዓይንህ ብርሃን ይመለስልህ፤ እምነትህ አድኖሃል” አለው።+ 43 ወዲያውም የዓይኑ ብርሃን ተመለሰለት፤ አምላክን እያመሰገነም ይከተለው ጀመር።+ ሕዝቡም ሁሉ ይህን ሲያዩ አምላክን አወደሱ።+
-