የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • nwt ቲቶ 1:1-3:15
  • ቲቶ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ቲቶ
  • አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
ቲቶ

ለቲቶ የተጻፈ ደብዳቤ

1 የአምላክ ባሪያና የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስ። ይህ ሐዋርያ፣ አገልግሎቱ ከአምላክ ምርጦች እምነትና ከእውነት ትክክለኛ እውቀት ጋር የሚስማማ ሲሆን ይህ እውነት ለአምላክ ያደሩ ሆኖ ከመኖር ጋር የተቆራኘ ነው፤ 2 ደግሞም ሊዋሽ የማይችለው አምላክ+ ከረጅም ዘመናት በፊት በሰጠው የዘላለም ሕይወት+ ተስፋ ላይ የተመሠረተ ነው፤ 3 ይሁንና አዳኛችን በሆነው አምላክ ትእዛዝ በአደራ በተሰጠኝ+ የስብከቱ ሥራ አማካኝነት ራሱ በወሰነው ጊዜ ቃሉ እንዲታወቅ አደረገ፤ 4 የጋራችን በሆነው እምነት እውነተኛ ልጄ ለሆነው ለቲቶ፦

አባት ከሆነው አምላክና አዳኛችን ከሆነው ከክርስቶስ ኢየሱስ ጸጋና ሰላም ለአንተ ይሁን።

5 አንተን በቀርጤስ የተውኩህ ያልተስተካከሉትን* ነገሮች እንድታስተካክልና በሰጠሁህ መመሪያ መሠረት በየከተማው ሽማግሌዎችን እንድትሾም ነው፤ 6 ይኸውም ከክስ ነፃ የሆነ፣ የአንዲት ሚስት ባል እንዲሁም በስድነት* ወይም በዓመፀኝነት የማይከሰሱ አማኝ የሆኑ ልጆች ያሉት ማንም ሰው ካለ እንድትሾም ነው።+ 7 ምክንያቱም የበላይ ተመልካች በአምላክ የተሾመ መጋቢ እንደመሆኑ መጠን ከክስ ነፃ መሆን አለበት፤ በራሱ ሐሳብ የሚመራ፣+ ግልፍተኛ፣+ ሰካራም፣ ኃይለኛና* አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት የሚስገበገብ ሊሆን አይገባም፤ 8 ከዚህ ይልቅ እንግዳ ተቀባይ፣+ ጥሩ የሆነውን ነገር የሚወድ፣ ጤናማ አስተሳሰብ ያለው፣*+ ጻድቅ፣ ታማኝ፣+ ራሱን የሚገዛ፣+ 9 እንዲሁም ትክክለኛ* በሆነው ትምህርት+ ማበረታታትም* ሆነ ይህን ትምህርት የሚቃወሙትን መውቀስ+ ይችል ዘንድ የማስተማር ጥበቡን+ ሲጠቀም የታመነውን ቃል* በጥብቅ የሚከተል ሊሆን ይገባል።

10 ዓመፀኞች፣ በከንቱ የሚለፈልፉና አታላዮች የሆኑ በተለይም ግርዘትን በጥብቅ የሚከተሉ ብዙ ሰዎች አሉና።+ 11 እነዚህ ሰዎች አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ማስተማር የማይገባቸውን ትምህርት በማስተማር የመላውን ቤተሰብ እምነት እያፈረሱ ስለሆነ አፋቸውን ማዘጋት ያስፈልጋል። 12 ከእነሱ መካከል የሆነ የገዛ ራሳቸው ነቢይ “የቀርጤስ ሰዎች ምንጊዜም ውሸታሞች፣ አደገኛ አውሬዎችና ሥራ ፈት ሆዳሞች ናቸው” ብሏል።

13 ይህ የምሥክርነት ቃል እውነት ነው። ለዚህም ሲባል እነሱን አጥብቀህ መውቀስህን ቀጥል፤ ይኸውም በእምነት ጠንካሮች* እንዲሆኑ 14 እንዲሁም ለአይሁዳውያን ተረቶችና ከእውነት የራቁ ሰዎች ለሚሰጡት ትእዛዝ ትኩረት እንዳይሰጡ ነው። 15 ንጹሕ ለሆኑ ሰዎች ሁሉም ነገር ንጹሕ ነው፤+ ለረከሱና እምነት ለሌላቸው ሰዎች ግን ንጹሕ የሆነ ነገር የለም፤ አእምሯቸውም ሆነ ሕሊናቸው የረከሰ ነውና።+ 16 አምላክን እንደሚያውቁ በይፋ ይናገራሉ፤ ሆኖም በሥራቸው ይክዱታል፤+ ምክንያቱም አስጸያፊና የማይታዘዙ እንዲሁም ለማንኛውም ዓይነት መልካም ሥራ የማይበቁ ናቸው።

2 አንተ ግን ምንጊዜም ከትክክለኛ* ትምህርት ጋር የሚስማማ ነገር ተናገር።+ 2 አረጋውያን ወንዶች በልማዶቻቸው ረገድ ልከኞች፣ ቁም ነገረኞች፣ ጤናማ አስተሳሰብ ያላቸው እንዲሁም በእምነት፣ በፍቅርና በጽናት ጤናሞች ይሁኑ። 3 በተመሳሳይም አረጋውያን ሴቶች ለቅዱሳን ሰዎች የሚገባ ባሕርይ ያላቸው፣ ስም የማያጠፉ፣ ለብዙ ወይን ጠጅ የማይገዙ እንዲሁም ጥሩ የሆነውን ነገር የሚያስተምሩ ይሁኑ፤ 4 ይህም ወጣት ሴቶችን በመምከር* ባሎቻቸውን የሚወዱ፣ ልጆቻቸውን የሚወዱ፣ 5 ጤናማ አስተሳሰብ ያላቸው፣ ንጹሐን፣ በቤት ውስጥ የሚሠሩ፣* ጥሩዎችና ለባሎቻቸው የሚገዙ+ እንዲሆኑ ለማድረግ ያስችላቸዋል፤ ይህም የአምላክ ቃል እንዳይሰደብ ነው።

6 በተመሳሳይም ወጣት ወንዶች ጤናማ አስተሳሰብ እንዲኖራቸው አሳስባቸው፤+ 7 በማንኛውም ሁኔታ መልካም ሥራ በመሥራት አርዓያ መሆንህን አሳይ። ንጹሕ የሆነውን ነገር* በቁም ነገር አስተምር፤+ 8 ደግሞም ሊነቀፍ የማይችል ጤናማ* አነጋገር በመጠቀም አስተምር፤+ ይኸውም ተቃዋሚዎች ስለ እኛ የሚናገሩት መጥፎ ነገር አጥተው እንዲያፍሩ ነው።+ 9 ባሪያዎች ጌቶቻቸውን ለማስደሰት ጥረት በማድረግ በሁሉም ነገር ይገዙላቸው፤+ የአጸፋ ቃልም አይመልሱላቸው፤ 10 ደግሞም ሊሰርቋቸው አይገባም፤+ ከዚህ ይልቅ አዳኛችን የሆነው አምላክ ትምህርት በሁሉም መንገድ ውበት እንዲጎናጸፍ ያደርጉ ዘንድ ሙሉ በሙሉ እምነት የሚጣልባቸው ይሁኑ።+

11 የአምላክ ጸጋ ተገልጧልና፤ ጸጋው ለሁሉም ዓይነት ሰዎች መዳን ያስገኛል።+ 12 ይህም ጸጋ ፈሪሃ አምላክ በጎደለው መንገድ መኖርና ዓለማዊ ምኞቶችን+ መከተል ትተን አሁን ባለው በዚህ ሥርዓት* ውስጥ ጤናማ አስተሳሰብ በመያዝ፣ በጽድቅና ለአምላክ በማደር እንድንኖር ያሠለጥነናል፤+ 13 በዚህ ሁኔታ አስደሳች የሆነውን ተስፋ+ እንዲሁም የታላቁን አምላክና የአዳኛችንን የኢየሱስ ክርስቶስን በክብር መገለጥ እንጠባበቃለን፤ 14 ክርስቶስ ከማንኛውም ዓይነት የዓመፅ ሕይወት እኛን ነፃ ለማውጣትና*+ ለመልካም ሥራ የሚቀና+ ልዩ ንብረቱ የሆነ ሕዝብ ለራሱ ለማንጻት ሕይወቱን ለእኛ ሰጥቷል።+

15 እነዚህን ነገሮች፣ በሙሉ ሥልጣን መናገርህን፣ አጥብቀህ መምከርህንና* መውቀስህን ቀጥል።+ ማንም ሰው ፈጽሞ አይናቅህ።

3 ለመንግሥታትና ለባለሥልጣናት እንዲገዙና እንዲታዘዙ+ እንዲሁም ለመልካም ሥራ ሁሉ ዝግጁ እንዲሆኑ አሳስባቸው፤ 2 ደግሞም ስለ ማንም ክፉ ነገር እንዳይናገሩ፣ ጠበኞች እንዳይሆኑ ከዚህ ይልቅ ምክንያታዊ እንዲሆኑና+ ለሰው ሁሉ ገርነትን በተሟላ ሁኔታ እንዲያንጸባርቁ አሳስባቸው።+ 3 እኛም በአንድ ወቅት የማናመዛዝን፣ የማንታዘዝ፣ የምንስት፣ ለተለያየ ምኞትና ሥጋዊ ደስታ የምንገዛ፣ በክፋትና በቅናት የምንኖር፣ በሰዎች ዘንድ የምንጠላና እርስ በርስ የማንዋደድ ነበርን።

4 ይሁን እንጂ አዳኛችን የሆነው አምላክ ደግነትና+ ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር በተገለጠ ጊዜ 5 (እኛ በሠራነው የጽድቅ ሥራ ሳይሆን+ በምሕረቱ)+ እኛን አጥቦ ሕያው በማድረግና በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በማደስ+ አዳነን።+ 6 ይህን መንፈስ አዳኛችን በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት በእኛ ላይ አትረፍርፎ* አፈሰሰው፤+ 7 ይህን ያደረገው በእሱ ጸጋ አማካኝነት ከጸደቅን+ በኋላ ከተስፋችን ጋር በሚስማማ ሁኔታ የዘላለም ሕይወትን+ እንድንወርስ ነው።+

8 እነዚህ ቃላት እምነት የሚጣልባቸው ናቸው፤ ደግሞም በአምላክ ያመኑ ሁሉ መልካም ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንዲያተኩሩ እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ ዘወትር አስረግጠህ እንድትናገር እፈልጋለሁ። እነዚህ ነገሮች መልካምና ለሰዎች ጠቃሚ ናቸው።

9 ሆኖም ሞኝነት ከሚንጸባረቅበት ክርክር፣ ከትውልድ ሐረግ ቆጠራ፣ ከጭቅጭቅና ሕጉን በተመለከተ ከሚነሳ ጠብ ራቅ፤ እነዚህ ነገሮች ምንም የማይጠቅሙና ከንቱ ናቸው።+ 10 ኑፋቄ+ የሚያስፋፋን ሰው ከአንዴም ሁለቴ አጥብቀህ ምከረው።*+ ካልሰማህ ግን ከእሱ ራቅ፤+ 11 እንዲህ ዓይነቱ ሰው ከትክክለኛው መንገድ የወጣና ኃጢአት እየሠራ ያለ ከመሆኑም ሌላ በራሱ ላይ እንደፈረደ እወቅ።

12 አርጤማስን ወይም ቲኪቆስን+ ወደ አንተ ስልክ፣ እኔ ወዳለሁበት ወደ ኒቆጶሊስ ለመምጣት የተቻለህን ሁሉ አድርግ፤ ክረምቱን በዚያ ለማሳለፍ ወስኛለሁና። 13 ሕጉን ጠንቅቆ የሚያውቀው ዜናስም ሆነ አጵሎስ ለጉዟቸው የሚያስፈልጋቸው ነገር ሁሉ እንዲሟላላቸው የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ።+ 14 ይሁን እንጂ አሳሳቢ ችግር ሲፈጠር መርዳት እንዲችሉና+ ፍሬ ቢሶች እንዳይሆኑ የእኛም ሰዎች በመልካም ሥራ መጠመድን ይማሩ።+

15 አብረውኝ ያሉት ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡልሃል። ለሚወዱን የእምነት ባልንጀሮቻችን ሰላምታ አቅርብልኝ።

የአምላክ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን።

ወይም “የጎደሉትን።”

ወይም “በጋጠወጥነት።”

ወይም “የሚማታና።” የግሪክኛው ቃል ሌሎችን መስደብንም ሊያመለክት ይችላል።

ወይም “ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ ያለው፤ አስተዋይ።”

ወይም “ጤናማ፤ ጠቃሚ።”

ወይም “አጥብቆ መምከርም።”

ወይም “እምነት የሚጣልበትን መልእክት።”

ቃል በቃል “ጤናሞች።”

ወይም “ከጤናማ፤ ጠቃሚ ከሆነ።”

ወይም “ወደ ልቦናቸው እንዲመለሱ በመርዳት፤ በማሠልጠን።”

ወይም “ቤታቸውን የሚንከባከቡ።”

“በንጽሕና” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “የሚያንጽ።”

ወይም “በዚህ ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ቃል በቃል “ለመቤዠትና፤ ለመዋጀትና።”

ወይም “ማበረታታትህንና።”

ወይም “በልግስና።”

ወይም “አስጠንቅቀው።”

    የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ጽሑፎች (2011-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ