የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • nwt ያዕቆብ 1:1-5:20
  • ያዕቆብ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ያዕቆብ
  • አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
ያዕቆብ

የያዕቆብ ደብዳቤ

1 የአምላክና የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ የሆነው ያዕቆብ፣+ በየቦታው ለተበተኑት ለ12ቱ ነገዶች፦

ሰላምታ ይድረሳችሁ!

2 ወንድሞቼ ሆይ፣ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቁጠሩት፤+ 3 ይህን ስታደርጉ ተፈትኖ የተረጋገጠው እምነታችሁ ጽናት እንደሚያስገኝ ታውቃላችሁ።+ 4 ይሁንና በሁሉም ረገድ ምንም የማይጎድላችሁ ፍጹማንና* እንከን የለሽ እንድትሆኑ ጽናት ሥራውን ሙሉ በሙሉ ይፈጽም።+

5 እንግዲህ ከእናንተ መካከል ጥበብ የጎደለው ሰው ካለ አምላክን ያለማሰለስ ይለምን፤+ አምላክ ማንንም ሳይነቅፍ* ለሁሉም በልግስና ይሰጣልና፤+ ይህም ሰው ይሰጠዋል።+ 6 ሆኖም ምንም ሳይጠራጠር በእምነት መለመኑን ይቀጥል፤+ የሚጠራጠር ሰው በነፋስ እንደሚገፋና እንደሚናወጥ የባሕር ማዕበል ነውና። 7 እንዲያውም እንዲህ ዓይነቱ ሰው ከይሖዋ* አንዳች ነገር አገኛለሁ ብሎ መጠበቅ የለበትም፤ 8 ይህ ሰው በሁለት ሐሳብ የሚዋልልና በመንገዱ ሁሉ የሚወላውል ነው።+

9 ይሁንና ዝቅ ያለው ወንድም ከፍ በመደረጉ ደስ ይበለው፤*+ 10 እንዲሁም ባለጸጋ የሆነው ዝቅ በመደረጉ+ ደስ ይበለው፤ ምክንያቱም ባለጸጋ ሰው እንደ ሜዳ አበባ ይረግፋል። 11 ፀሐይ ወጥታ በኃይለኛ ሙቀቷ ተክሉን ታጠወልጋለች፤ አበባውም ይረግፋል፤ ውበቱም ይጠፋል፤ ባለጸጋ ሰውም ልክ እንደዚሁ በዕለት ተዕለት ተግባሩ ሲዋትት ከስሞ ይጠፋል።+

12 ፈተናን በጽናት ተቋቁሞ የሚኖር ሰው ደስተኛ ነው፤+ ምክንያቱም ይህ ሰው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት በሚያገኝበት ጊዜ፣ ይሖዋ* እሱን ለሚወዱት ቃል የገባውን የሕይወት አክሊል ይቀበላል።+ 13 ማንም ሰው ፈተና ሲደርስበት “አምላክ እየፈተነኝ ነው” አይበል። አምላክ በክፉ ነገር ሊፈተን አይችልምና፤ እሱ ራሱም ማንንም በክፉ ነገር አይፈትንም። 14 ሆኖም እያንዳንዱ ሰው በራሱ ምኞት ሲማረክና ሲታለል* ይፈተናል።+ 15 ከዚያም ምኞት ከፀነሰች በኋላ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአት ሲፈጸም ደግሞ ሞት ያስከትላል።+

16 የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ አትታለሉ። 17 መልካም ስጦታ ሁሉና ፍጹም ገጸ በረከት ሁሉ ከላይ ነው፤+ ይህ የሚወርደው ከሰማይ ብርሃናት አባት+ ሲሆን እሱ ደግሞ ቦታውን እንደሚቀያይር ጥላ አይለዋወጥም።+ 18 ፈቃዱ ስለሆነም ከፍጥረታቱ መካከል እኛ እንደ በኩራት እንድንሆን+ በእውነት ቃል አማካኝነት ወለደን።+

19 የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ ይህን እወቁ፦ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየና+ ለቁጣ የዘገየ መሆን አለበት፤+ 20 የሰው ቁጣ የአምላክ ጽድቅ እንዲፈጸም አያደርግምና።+ 21 ስለዚህ ጸያፍ የሆነውን ነገር ሁሉና ክፋትን ሁሉ* አስወግዳችሁ+ እናንተን* ሊያድን የሚችለውን በውስጣችሁ የሚተከለውን ቃል በገርነት ተቀበሉ።

22 ሆኖም ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ+ እንጂ የውሸት ምክንያት እያቀረባችሁ ራሳችሁን በማታለል ሰሚዎች ብቻ አትሁኑ። 23 ማንም ሰው ቃሉን የሚሰማ እንጂ የማያደርገው ከሆነ+ የገዛ ፊቱን በመስተዋት እያየ ካለ ሰው ጋር ይመሳሰላል። 24 ይህ ሰው ራሱን ካየ በኋላ ይሄዳል፤ ወዲያውም ምን እንደሚመስል ይረሳል። 25 ሆኖም ነፃ የሚያወጣውን ፍጹም ሕግ+ በትኩረት የሚመለከትና በዚያ የሚጸና ሰው ሰምቶ የሚረሳ ሳይሆን በሥራ ላይ የሚያውል ሰው ነው፤ በሚያደርገውም ነገር ደስተኛ ይሆናል።+

26 አንድ ሰው አምላክን እያመለከ እንዳለ* ቢያስብም እንኳ አንደበቱን የማይገታ* ከሆነ+ ይህ ሰው የገዛ ልቡን ያታልላል፤ አምልኮውም ከንቱ ነው። 27 በአምላካችንና በአባታችን ዓይን ንጹሕና ያልረከሰ አምልኮ* ‘ወላጅ አልባ የሆኑ ልጆችንና+ መበለቶችን+ በመከራቸው መርዳት+ እንዲሁም ከዓለም እድፍ ራስን መጠበቅ’ ነው።+

2 ወንድሞቼ ሆይ፣ በአንድ በኩል ክብር በተጎናጸፈው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የምታምኑ ሆናችሁ በሌላ በኩል ደግሞ አድልዎ ታደርጋላችሁ?+ 2 በጣቶቹ ላይ የወርቅ ቀለበቶች ያደረገና ያማረ ልብስ የለበሰ ሰው ወደ ስብሰባችሁ ቢመጣና ያደፈ ልብስ የለበሰ ድሃ ሰውም እንደዚሁ ወደ ስብሰባው ቢገባ 3 ያማረ ልብስ ለለበሰው ሰው አክብሮት በማሳየት “እዚህ የተሻለው ቦታ ላይ ተቀመጥ” ድሃውን ደግሞ “አንተ እዚያ ቁም” ወይም “እዚህ ከእግሬ ማሳረፊያ በታች ተቀመጥ” ትሉታላችሁ?+ 4 እንዲህ የምትሉ ከሆነ በመካከላችሁ የመደብ ልዩነት እንዲኖር ማድረጋችሁ አይደለም?+ ደግሞስ ክፉ ፍርድ የምትፈርዱ ፈራጆች መሆናችሁ አይደለም?+

5 የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ ስሙ። አምላክ በእምነት ባለጸጋ እንዲሆኑና+ እሱን ለሚወዱ ቃል የገባውን መንግሥት እንዲወርሱ ከዓለም አመለካከት አንጻር ድሆች የሆኑትን አልመረጠም?+ 6 እናንተ ግን ድሃውን ሰው አዋረዳችሁ። እናንተን የሚጨቁኗችሁና+ ጎትተው ፍርድ ቤት የሚያቀርቧችሁ ሀብታሞች አይደሉም? 7 እናንተ የተጠራችሁበትን መልካም ስም የሚሳደቡት እነሱ አይደሉም? 8 እንግዲያው በቅዱስ መጽሐፉ መሠረት “ባልንጀራህን* እንደ ራስህ ውደድ”+ የሚለውን ንጉሣዊ ሕግ ተግባራዊ የምታደርጉ ከሆነ መልካም እያደረጋችሁ ነው። 9 ማዳላታችሁን የማትተዉ ከሆነ+ ግን ኃጢአት እየሠራችሁ ነው፤ ሕጉም ሕግ ተላላፊዎች ናችሁ ብሎ ይፈርድባችኋል።*+

10 አንድ ሰው ሕጉን ሁሉ የሚጠብቅ ሆኖ ሳለ አንዱን ትእዛዝ ሳይጠብቅ ቢቀር ሁሉንም እንደጣሰ ይቆጠራል።+ 11 “አታመንዝር”+ ያለው እሱ “አትግደል”+ የሚል ትእዛዝም ሰጥቷልና። እንግዲህ ምንዝር ባትፈጽምም እንኳ ከገደልክ ሕግ ተላላፊ ሆነሃል። 12 ነፃ በሆኑ ግለሰቦች ሕግ* የሚዳኙ ሰዎች በሚናገሩበት መንገድ መናገራችሁንና እነሱ እንደሚያደርጉት ማድረጋችሁን ቀጥሉ።+ 13 ምሕረት የማያደርግ ሰው ያለምሕረት ይፈረድበታልና።+ ምሕረት በፍርድ ላይ ድል ይቀዳጃል።

14 ወንድሞቼ ሆይ፣ አንድ ሰው እምነት አለኝ ቢል ነገር ግን እምነቱ በሥራ የተደገፈ ባይሆን ምን ጥቅም ይኖረዋል?+ እምነቱ ሊያድነው ይችላል?+ 15 አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት የሚለብሱት ቢያጡና* ለዕለት የሚያስፈልጋቸውን በቂ ምግብ ባያገኙ 16 ሆኖም ከመካከላችሁ አንዱ “በሰላም ሂዱ፤ ይሙቃችሁ፤ ጥገቡም” ቢላቸው ለሰውነታቸው የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ግን ባይሰጣቸው ምን ይጠቅማቸዋል?+ 17 ስለዚህ በሥራ ያልተደገፈ እምነትም በራሱ የሞተ ነው።+

18 ይሁን እንጂ አንድ ሰው እንዲህ ይላል፦ “አንተ እምነት አለህ፤ እኔ ደግሞ ሥራ አለኝ። እምነትህን ከሥራ ለይተህ አሳየኝ፤ እኔ ደግሞ እምነቴን በሥራ አሳይሃለሁ።” 19 አንድ አምላክ እንዳለ ታምናለህ አይደል? ማመንህ መልካም ነው። ይሁንና አጋንንትም ያምናሉ፤ በፍርሃትም ይንቀጠቀጣሉ።+ 20 አንተ ከንቱ ሰው፣ እምነት ያለሥራ እንደማይጠቅም ማረጋገጥ ትፈልጋለህ? 21 አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያ ላይ ካቀረበ በኋላ የጸደቀው በሥራ አይደለም?+ 22 እምነቱ ከሥራው ጋር አብሮ ይሠራ እንደነበረና ሥራው እምነቱን ፍጹም እንዳደረገው ትገነዘባለህ፤+ 23 ደግሞም “አብርሃም በይሖዋ* አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት”+ የሚለው የቅዱስ መጽሐፍ ቃል ተፈጸመ፤ እሱም የይሖዋ* ወዳጅ ለመባል በቃ።+

24 እንግዲህ ሰው የሚጸድቀው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራም ጭምር እንደሆነ ትገነዘባላችሁ። 25 ዝሙት አዳሪዋ ረዓብም መልእክተኞቹን በጥሩ ሁኔታ ተቀብላ ካስተናገደቻቸውና በሌላ መንገድ ከላከቻቸው በኋላ በሥራ አልጸደቀችም?+ 26 በእርግጥም አካል ያለመንፈስ* የሞተ እንደሆነ ሁሉ+ እምነትም ያለሥራ የሞተ ነው።+

3 ወንድሞቼ ሆይ፣ ከእናንተ መካከል ብዙዎች አስተማሪዎች አይሁኑ፤ ምክንያቱም እኛ የባሰ ፍርድ እንደምንቀበል* ታውቃላችሁ።+ 2 ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንሰናከላለንና።*+ በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር ይህ ሰው መላ ሰውነቱንም መቆጣጠር* የሚችል ፍጹም ሰው ነው። 3 ፈረሶች እንዲታዘዙልን አፋቸው ውስጥ ልጓም ካስገባን መላ ሰውነታቸውንም መምራት እንችላለን። 4 መርከቦችንም ተመልከቱ፦ በጣም ትልቅና በኃይለኛ ነፋስ የሚነዱ ቢሆኑም የመርከቡ ነጂ በትንሽ መሪ ወደሚፈልገው አቅጣጫ ሁሉ ይመራቸዋል።

5 ልክ እንደዚሁም ምላስ ትንሽ የአካል ክፍል ሆና ሳለ ጉራዋን ትነዛለች። በጣም ሰፊ የሆነን ጫካ በእሳት ለማያያዝ ትንሽ እሳት ብቻ ይበቃል! 6 ምላስም እሳት ናት።+ ምላስ በአካል ክፍሎቻችን መካከል የክፋትን ዓለም ትወክላለች፤ መላ ሰውነትን ታረክሳለችና፤+ እንዲሁም መላውን የሕይወት ጎዳና* ታቃጥላለች፤ እሷም በገሃነም* ትቃጠላለች። 7 ማንኛውም ዓይነት የዱር እንስሳ፣ ወፍ፣ በምድር ላይ የሚሳብ ፍጥረትና በባሕር ውስጥ የሚኖር ፍጥረት በሰዎች ሊገራ ይችላል፤ ደግሞም ተገርቷል። 8 ምላስን ግን ሊገራ የሚችል አንድም ሰው የለም። ምላስ ገዳይ መርዝ የሞላባት፣ ለመቆጣጠር የምታስቸግር ጎጂ ነገር ናት።+ 9 በምላሳችን አባት የሆነውን ይሖዋን* እናወድሳለን፤ ይሁንና በዚህችው ምላሳችን “በአምላክ አምሳል” የተፈጠሩትን ሰዎች+ እንረግማለን። 10 ከአንድ አፍ በረከትና እርግማን ይወጣሉ።

ወንድሞቼ፣ ይህ መሆኑ ተገቢ አይደለም።+ 11 አንድ ምንጭ ከዚያው ጉድጓድ ጣፋጭና መራራ ውኃ ያፈልቃል? 12 ወንድሞቼ፣ የበለስ ዛፍ ወይራን ወይም ደግሞ የወይን ተክል በለስን ሊያፈራ ይችላል?+ ከጨዋማ ውኃም ጣፋጭ ውኃ ሊገኝ አይችልም።

13 ከእናንተ መካከል ጥበበኛና አስተዋይ ሰው ማን ነው? ሥራውን የሚያከናውነው ከጥበብ በመነጨ ገርነት* መሆኑን በመልካም ምግባሩ ያሳይ። 14 ሆኖም በልባችሁ ውስጥ መራራ ቅናትና+ ጠበኝነት*+ ካለ አትኩራሩ፤+ እንዲሁም በእውነት ላይ አትዋሹ። 15 ይህ ከሰማይ የሚመጣ ጥበብ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ምድራዊ፣+ እንስሳዊና አጋንንታዊ ነው። 16 ቅናትና ጠበኝነት* ባለበት ሁሉ ብጥብጥና መጥፎ ነገሮችም ይኖራሉ።+

17 ከሰማይ የሆነው ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጹሕ+ ነው፤ ከዚያም ሰላማዊ፣+ ምክንያታዊ፣+ ለመታዘዝ ዝግጁ የሆነ፣ ምሕረትና መልካም ፍሬዎች የሞሉበት+ እንዲሁም አድልዎና+ ግብዝነት የሌለበት+ ነው። 18 ከዚህም በላይ የጽድቅ ፍሬ ሰላም ፈጣሪ ለሆኑ ሰዎች*+ ሰላማዊ በሆኑ ሁኔታዎች+ ይዘራል።

4 በእናንተ መካከል ያለው ጦርነትና ጠብ ከየት የመጣ ነው? በውስጣችሁ* ከሚዋጉት ሥጋዊ ፍላጎቶቻችሁ የመነጨ አይደለም?+ 2 ትመኛላችሁ ሆኖም አታገኙም። ትገድላላችሁ እንዲሁም ትጎመጃላችሁ፤* ይሁንና ማግኘት አትችሉም። ትጣላላችሁ እንዲሁም ትዋጋላችሁ።+ ስለማትጠይቁም አታገኙም። 3 በምትጠይቁበት ጊዜም አታገኙም፤ ምክንያቱም የምትጠይቁት ለተሳሳተ ዓላማ ይኸውም ሥጋዊ ፍላጎታችሁን ለማርካት ነው።

4 አመንዝሮች ሆይ፣* ከዓለም ጋር መወዳጀት ከአምላክ ጋር ጠላትነት መፍጠር እንደሆነ አታውቁም? ስለዚህ የዓለም ወዳጅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ ራሱን የአምላክ ጠላት ያደርጋል።+ 5 ወይስ ቅዱስ መጽሐፉ “በውስጣችን ያደረው መንፈስ በቅናት ሁልጊዜ ይመኛል” ያለው ያለምክንያት ይመስላችኋል?+ 6 ይሁን እንጂ አምላክ የሚሰጠው ጸጋ እንዲህ ካለው መንፈስ የላቀ ነው። በመሆኑም ቅዱስ መጽሐፉ “አምላክ ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤+ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” ይላል።+

7 ስለዚህ ራሳችሁን ለአምላክ አስገዙ፤+ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙት፤+ እሱም ከእናንተ ይሸሻል።+ 8 ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል።+ እናንተ ኃጢአተኞች እጆቻችሁን አንጹ፤+ እናንተ ወላዋዮች ልባችሁን አጥሩ።+ 9 ተጨነቁ፣ እዘኑ፣ አልቅሱ።+ ሳቃችሁ ወደ ሐዘን፣ ደስታችሁም ወደ ተስፋ መቁረጥ ይለወጥ። 10 በይሖዋ* ፊት ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤+ እሱም ከፍ ከፍ ያደርጋችኋል።+

11 ወንድሞች፣ አንዳችሁ ሌላውን መንቀፋችሁን ተዉ።+ ወንድሙን የሚነቅፍ ወይም በወንድሙ ላይ የሚፈርድ ሁሉ ሕግን ይነቅፋል እንዲሁም በሕግ ላይ ይፈርዳል። በሕግ ላይ የምትፈርድ ከሆነ ደግሞ ፈራጅ ነህ እንጂ ሕግን ፈጻሚ አይደለህም። 12 ሕግ የሚሰጥና የሚፈርድ አንድ ብቻ ነው፤+ እሱ ማዳንም ሆነ ማጥፋት ይችላል።+ ታዲያ በባልንጀራህ* ላይ የምትፈርድ አንተ ማን ነህ?+

13 እንግዲህ እናንተ “ዛሬ ወይም ነገ ወደዚህች ከተማ እንሄዳለን፤ እዚያም ዓመት እንቆያለን፤ እንነግዳለን እንዲሁም እናተርፋለን” የምትሉ ስሙ፤+ 14 ሕይወታችሁ ነገ ምን እንደሚሆን እንኳ አታውቁም።+ ለጥቂት ጊዜ ታይቶ እንደሚጠፋ እንፋሎት ናችሁና።+ 15 ከዚህ ይልቅ “ይሖዋ* ከፈቀደ+ በሕይወት እንኖራለን፤ ደግሞም ይህን ወይም ያን እናደርጋለን” ማለት ይገባችኋል። 16 አሁን ግን እናንተ ከልክ በላይ ጉራ በመንዛት ትኩራራላችሁ። እንዲህ ያለው ጉራ ሁሉ ክፉ ነው። 17 ስለዚህ አንድ ሰው ትክክል የሆነውን ነገር እንዴት ማድረግ እንዳለበት እያወቀ ሳያደርገው ቢቀር ኃጢአት ይሆንበታል።+

5 እናንተ ሀብታሞች እንግዲህ ስሙ፤ እየመጣባችሁ ባለው መከራ አልቅሱ እንዲሁም ዋይ ዋይ በሉ።+ 2 ሀብታችሁ በስብሷል፤ ልብሳችሁንም ብል በልቶታል።+ 3 ወርቃችሁና ብራችሁ ሙሉ በሙሉ ዝጓል፤ ዝገቱም በእናንተ ላይ ይመሠክራል፤ ሥጋችሁንም ይበላል። ያከማቻችሁት ነገር በመጨረሻዎቹ ቀናት እንደ እሳት ይሆናል።*+ 4 እነሆ፣ በእርሻችሁ ላይ ያለውን ሰብል ለሰበሰቡት ሠራተኞች ሳትከፍሏቸው የቀራችሁት ደሞዝ ይጮኻል፤ አጫጆቹም ለእርዳታ የሚያሰሙት ጥሪ ወደ ሠራዊት ጌታ ወደ ይሖዋ* ጆሮ ደርሷል።+ 5 በምድር ላይ በቅንጦት ኖራችኋል፤ የራሳችሁንም ፍላጎት ለማርካት ትጥሩ ነበር። በእርድ ቀን ልባችሁን አወፍራችኋል።+ 6 ጻድቁን ኮነናችሁት፤ ደግሞም ገደላችሁት። እሱ እየተቃወማችሁ አይደለም?*

7 እንግዲህ ወንድሞች፣ ጌታ እስከሚገኝበት ጊዜ+ ድረስ በትዕግሥት ጠብቁ። እነሆ፣ ገበሬ የመጀመሪያውና የኋለኛው ዝናብ እስኪመጣ ድረስ በመታገሥ የምድርን መልካም ፍሬ ይጠባበቃል።+ 8 እናንተም በትዕግሥት ጠብቁ፤+ ጌታ የሚገኝበት ጊዜ ስለተቃረበ ልባችሁን አጽኑ።+

9 ወንድሞች፣ እንዳይፈረድባችሁ አንዳችሁ በሌላው ላይ አታጉረምርሙ።*+ እነሆ፣ ፈራጁ ደጃፍ ላይ ቆሟል። 10 ወንድሞች፣ በይሖዋ* ስም የተናገሩትን ነቢያት+ መከራ በመቀበልና ትዕግሥት በማሳየት+ ረገድ አርዓያ አድርጋችሁ ተመልከቷቸው።+ 11 እነሆ፣ የጸኑትን ደስተኞች* እንደሆኑ አድርገን እንቆጥራቸዋለን።+ ስለ ኢዮብ ጽናት ሰምታችኋል፤+ በውጤቱም ይሖዋ* ያደረገለትን አይታችኋል፤+ በዚህም ይሖዋ* እጅግ አፍቃሪና* መሐሪ እንደሆነ ተመልክታችኋል።+

12 ከሁሉም በላይ ወንድሞቼ፣ በሰማይም ሆነ በምድር ወይም በሌላ መሐላ መማላችሁን ተዉ። ከዚህ ይልቅ “አዎ” ካላችሁ አዎ ይሁን፤ “አይደለም” ካላችሁ አይደለም ይሁን፤+ አለዚያ ለፍርድ ትዳረጋላችሁ።

13 ከእናንተ መካከል መከራ እየደረሰበት ያለ ሰው አለ? መጸለዩን ይቀጥል።+ ደስ የተሰኘ አለ? የምስጋና መዝሙር ይዘምር።+ 14 ከእናንተ መካከል የታመመ ሰው አለ? የጉባኤ ሽማግሌዎችን ወደ እሱ ይጥራ፤+ እነሱም በይሖዋ* ስም ዘይት ቀብተው+ ይጸልዩለት። 15 በእምነት የቀረበ ጸሎት የታመመውን* ሰው ይፈውሰዋል፤ ይሖዋም* ያስነሳዋል። በተጨማሪም ኃጢአት ሠርቶ ከሆነ ይቅር ይባላል።

16 ስለዚህ ፈውስ ማግኘት እንድትችሉ አንዳችሁ ለሌላው ኃጢአታችሁን በግልጽ ተናዘዙ፤+ እንዲሁም አንዳችሁ ለሌላው ጸልዩ። ጻድቅ ሰው የሚያቀርበው ምልጃ ታላቅ ኃይል አለው።+ 17 ኤልያስ እንደ እኛው ዓይነት ስሜት ያለው ሰው ነበር፤ ያም ሆኖ ዝናብ እንዳይዘንብ አጥብቆ በጸለየ ጊዜ በምድሩ ላይ ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር ዝናብ አልዘነበም።+ 18 ከዚያም እንደገና ጸለየ፤ ሰማዩም ዝናብ ሰጠ፤ ምድሩም ፍሬ አፈራ።+

19 ወንድሞቼ፣ ከእናንተ መካከል አንድ ሰው ከእውነት መንገድ ስቶ ቢወጣና ሌላ ሰው ቢመልሰው፣ 20 ኃጢአተኛን ከስህተት ጎዳናው የሚመልስ ማንኛውም ሰው+ ኃጢአተኛውን* ከሞት እንደሚያድንና ብዙ ኃጢአትን እንደሚሸፍን እወቁ።+

ወይም “ምሉዓንና።”

ወይም “ስህተት ሳይፈላልግ።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ቃል በቃል “ይኩራራ።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “ሲማረክና በወጥመድ ሲያዝ።”

“እጅግ ተስፋፍቶ የሚገኘውን ክፋት” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ነፍሳችሁን።”

ወይም “ሃይማኖተኛ እንደሆነ።”

ወይም “አንደበቱ ላይ ልጓም የማያስገባ።”

ወይም “ሃይማኖት።”

“ባልንጀራ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል የአንድን ሰው የቅርብ ጓደኛ ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ሰው ሊያመለክት ይችላል።

ወይም “ይወቅሳችኋል።”

ቃል በቃል “በነፃነት ሕግ።”

ቃል በቃል “ቢራቆቱና።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “እስትንፋስ።”

ወይም “ፍርዱ እኛ ላይ እንደሚጠብቅ።”

ወይም “እንሳሳታለንና።”

ወይም “ለመላ ሰውነቱ ልጓም ማስገባት።”

ወይም “ተፈጥሯዊውን የሕይወት እሽክርክሪት።” ቃል በቃል “የመወለድን እሽክርክሪት።”

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

“ልዝብ፤ ለስላሳ፤ ሸካራ ያልሆነ” የሚል ትርጉም አለው።

“የራስ ወዳድነት ምኞት” ማለትም ሊሆን ይችላል።

“የራስ ወዳድነት ምኞት” ማለትም ሊሆን ይችላል።

“ሰላም ፈጣሪ በሆኑ ሰዎች” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “በአካል ክፍሎቻችሁ ውስጥ።”

ወይም “ትቀናላችሁ።”

ወይም “እናንተ ከዳተኞች።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

“ባልንጀራ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል የአንድን ሰው የቅርብ ጓደኛ ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ሰው ሊያመለክት ይችላል።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “ሥጋችሁን እንደ እሳት ይበላዋል። በመጨረሻዎቹ ቀናት ሀብት አከማችታችኋል።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “እሱ እየተቃወማችሁ አይደለም።”

ወይም “አታማሩ።” ቃል በቃል “አታቃስቱ።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “የተባረኩ።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “ከአንጀት የሚራራና።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

“የደከመውን” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “የኃጢአተኛውን ነፍስ።”

    የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ጽሑፎች (2011-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ