ዓርብ፣ ሐምሌ 18
ነገሥታት እንዲሁም ለአምላኩና ለአባቱ ካህናት [አደረገን]።—ራእይ 1:6
የተወሰነ ቁጥር ያላቸው የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት በመንፈስ ቅዱስ ተቀብተዋል፤ እነዚህ ሰዎች ከይሖዋ ጋር ልዩ ዝምድና አላቸው። እነዚህ 144,000 ሰዎች በሰማይ ከኢየሱስ ጋር ካህናት ሆነው ያገለግላሉ። (ራእይ 14:1) ቅድስት የተባለው የማደሪያ ድንኳኑ ክፍል ቅቡዓን ክርስቲያኖች ገና ምድር ላይ ሳሉ ያሉበትን ሁኔታ ማለትም በመንፈስ የተወለዱ የአምላክ ልጆች መሆናቸውን ያመለክታል። (ሮም 8:15-17) ቅድስተ ቅዱሳን የተባለው የማደሪያ ድንኳኑ ክፍል ደግሞ ይሖዋ የሚኖርበትን ሰማይን ያመለክታል። ቅድስቱንና ቅድስተ ቅዱሳኑን የሚለየው “መጋረጃ” ኢየሱስ የመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ታላቅ ሊቀ ካህናት ሆኖ ወደ ሰማይ እንዳይገባ ያገደውን ሥጋዊ አካሉን ያመለክታል። ኢየሱስ ሰብዓዊ አካሉን ለሰው ልጆች መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ ሁሉም ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሰማያዊ ሕይወት ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ ከፍቷል። እነሱም ቢሆኑ ሰማያዊ ሽልማታቸውን ለመቀበል ሥጋዊ አካላቸውን መተው ይጠበቅባቸዋል።—ዕብ. 10:19, 20፤ 1 ቆሮ. 15:50፤ w23.10 28 አን. 13
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 19
ስለ ጌድዮን . . . እንዳልተርክ ጊዜ ያጥረኛል።—ዕብ. 11:32
ጌድዮን ኤፍሬማውያን ትችት በሰነዘሩበት ወቅት በገርነት ምላሽ ሰጥቷል። (መሳ. 8:1-3) መልስ የሰጠው በቁጣ አልነበረም። ስሜታቸውን ሲገልጹ በማዳመጥ ትሕትና አሳይቷል፤ እንዲሁም ውጥረት የሰፈነበትን ሁኔታ በዘዴ አርግቧል። ጥበበኛ የሆኑ ሽማግሌዎችም ትችት ሲሰነዘርባቸው በጥሞና በማዳመጥ እንዲሁም በገርነት ምላሽ በመስጠት የጌድዮንን ምሳሌ መከተል ይችላሉ። (ያዕ. 3:13) በዚህ መንገድ ለጉባኤው ሰላም አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። ጌድዮን ምድያማውያንን ድል በማድረጉ የተነሳ ክብር ሲሰጠው የሰዎቹ ትኩረት ወደ ይሖዋ እንዲዞር አድርጓል። (መሳ. 8:22, 23) ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች የጌድዮንን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው? ላከናወኑት ሥራ ይሖዋ እንዲመሰገን ማድረግ ይችላሉ። (1 ቆሮ. 4:6, 7) ለምሳሌ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ የማስተማር ችሎታውን በተመለከተ ቢመሰገን የሰዎቹን ትኩረት የትምህርቱ ምንጭ ወደሆነው ወደ አምላክ ቃል ወይም ከይሖዋ ድርጅት ወደምናገኘው ሥልጠና ማዞር ይችላል። ሽማግሌዎች ‘ወደ ራሴ አላስፈላጊ ትኩረት እየሳብኩ ነው?’ ብለው አልፎ አልፎ ራሳቸውን መመርመራቸው ጠቃሚ ነው። w23.06 4 አን. 7-8
እሁድ፣ ሐምሌ 20
ሐሳቤ እንደ ሐሳባችሁ . . . አይደለም።—ኢሳ. 55:8
በጸሎት የጠየቅነውን ነገር ካላገኘን ‘ጥያቄዬ ተገቢ ነው?’ ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ እንችላለን። ብዙውን ጊዜ፣ የሚበጀንን ነገር እንደምናውቅ ይሰማናል። ሆኖም የጠየቅናቸው ነገሮች ላይጠቅሙን ይችላሉ። የምንጸልየው ስለ አንድ ችግር ከሆነ ለዚያ ችግር እኛ ከጠየቅነው የተሻለ መፍትሔ ሊኖር ይችላል። የምንጠይቃቸው አንዳንድ ነገሮች ደግሞ ከይሖዋ ፈቃድ ጋር ላይስማሙ ይችላሉ። (1 ዮሐ. 5:14) ልጃቸው እውነት ውስጥ እንዲቆይ ይሖዋን በጸሎት የጠየቁ ወላጆችን እንደ ምሳሌ እንመልከት። ጥያቄያቸው ተገቢ ይመስላል። ይሁንና ይሖዋ ማናችንንም እንድናገለግለው አያስገድደንም። ልጆቻችንን ጨምሮ ሁላችንም እሱን ለማገልገል እንድንመርጥ ይፈልጋል። (ዘዳ. 10:12, 13፤ 30:19, 20) በመሆኑም እነዚህ ወላጆች የልጃቸውን ልብ ለመንካት እንዲረዳቸው ይሖዋን ቢጠይቁ የተሻለ ነው፤ ይህም ልጃቸው ይሖዋን እንዲወደውና የእሱ ወዳጅ እንዲሆን ሊያነሳሳው ይችላል።—ምሳሌ 22:6፤ ኤፌ. 6:4፤ w23.11 21 አን. 5፤ 23 አን. 12