ወደ አምላክ ቅረብ
ለሚያገለግሉት ሁሉ ወሮታ ከፋይ የሆነ አምላክ
“አመሰግናለሁ።” አንድ መልካም ተግባር ካከናወነ ወይም ከልብ በመነጨ አሳቢነት ተነሳስቶ ለሌሎች ስጦታ ከሰጠ በኋላ እንደዚህ ያለውን የምስጋና ቃል መስማት የማያስደስተው ማን አለ? ሁላችንም፣ በተለይ የምንወዳቸው ሰዎች ጥረታችንን ሲያደንቁልን ደስ ይለናል። ከማንም በላይ የምንወደው ይሖዋ አምላካችንን እንደሆነ የታወቀ ነው። ታዲያ ይሖዋ እሱን ለማገልገል የምናደርገውን ጥረት በቁም ነገር ይመለከተዋል? ይሖዋ፣ የአምላክን ነቢይ ለማዳን ሲል ሕይወቱን አደጋ ላይ ለጣለው ለአቤሜሌክ ምን ዓይነት አመለካከት እንደነበረው እስቲ እንመርምር።—ኤርምያስ 38:7-13ን እና ኤር 39:16-18ን አንብብ።
አቤሜሌክ ማን ነበር? ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው አቤሜሌክ በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ ቤተ መንግሥት ውስጥ የነበረ ባለሥልጣን ነው።a አቤሜሌክ የኖረው በኤርምያስ ዘመን ነበር፤ ኤርምያስ፣ ከዳተኛዋ ይሁዳ ጥፋት እንደሚመጣባት እንዲያስጠነቅቅ አምላክ የላከው ነቢይ ነው። አቤሜሌክ፣ ፈሪሃ አምላክ በሌላቸው መኳንንት መካከል ቢኖርም አምላክን የሚፈራ እንዲሁም ለኤርምያስ ከፍተኛ አክብሮት ያለው ሰው ነበር። እነዚህ ክፉ መኳንንት፣ ኤርምያስን ሕዝቡን አሳምፀሃል ብለው በሐሰት ከወነጀሉት በኋላ፣ እንዲሞት ጭቃ ወደ ሞላበት የውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ ውስጥ ጣሉት፤ የአቤሜሌክ አምላካዊ ባሕርያት የተፈተኑት በዚህ ጊዜ ነበር። (ኤርምያስ 38:4-6) አቤሜሌክ ምን ያደርግ ይሆን?
አቤሜሌክ መኳንንቱ ይበቀሉኛል ብሎ ሳይፈራ በድፍረት እና በቆራጥነት እርምጃ ወስዷል። ወደ ሴዴቅያስ በግልጽ መጥቶ መኳንንቱ በኤርምያስ ላይ ያደረሱበትን በደል ተቃወመ። አቤሜሌክ ይህንን ደባ ወደፈጸሙት ሰዎች እየጠቆመ ሳይሆን አይቀርም “እነዚህ ሰዎች በነቢዩ በኤርምያስ ላይ . . . ክፋትን አድርገዋል” አለ። (ኤርምያስ 38:9) አቤሜሌክ ያደረገው ጥረት የተሳካለት ሲሆን በንጉሡ ትእዛዝ 30 ሰዎችን ይዞ ኤርምያስን ለማዳን ሄደ።
አቤሜሌክ በዚህ ወቅት ሌላ ግሩም ባሕርይ አሳይቷል፤ ይህ ባሕርይ ደግነት ነው። አቤሜሌክ “ያረጀ ጨርቅና ያለቀ ልብስ . . . ወደ ኤርምያስ ወደ ጕድጓዱ ውስጥ በገመድ አወረደለት።” ይህን ያደረገው ለምንድን ነው? ኤርምያስ ከጉድጓዱ ውስጥ ተጎትቶ በሚወጣበት ጊዜ ገመዱ ብብቱን እንዳይፈገፍገው ነው።—ኤርምያስ 38:11-13
ይሖዋ አቤሜሌክ ያደረገውን ተመልክቷል። ታዲያ አቤሜሌክ ላደረገው ነገር አድናቆቱን ገልጿል? አምላክ፣ ይሁዳ መጥፋቷ እንደማይቀር በኤርምያስ በኩል ለአቤሜሌክ ነገረው። ከዚያም አምላክ አምስት ነገሮችን እንደሚፈጽምለት ለአቤሜሌክ ቃል ገባለት። ይሖዋ እንዲህ ብሏል፦ “አድንሃለሁ . . . ለምትፈራቸው ሰዎች ዐልፈህ አትሰጥም። እታደግሃለሁ፤ . . . በሕይወት ታመልጣለህ . . . በሰይፍ አትወድቅም።” ይሖዋ፣ አቤሜሌክን እንደሚያድነው ቃል የገባው ለምንድን ነው? “በእኔ ታምነሃልና” ብሎታል። (ኤርምያስ 39:16-18) አቤሜሌክ እነዚህን እርምጃዎች የወሰደው የኤርምያስ ጉዳይ ስላሳሰበው ብቻ ሳይሆን በአምላክ ስለሚተማመንና በእሱ ላይ እምነት ስላለው እንደሆነ ይሖዋ ያውቅ ነበር።
ይህ ታሪክ የሚያስተላልፈው መልእክት ግልጽ ነው፦ ይሖዋ እሱን ለማገልገል የምናደርጋቸውን ጥረቶች ያደንቃል። ይሖዋ በእምነት እሱን ለማምለክ የምናደርገውን በጣም ትንሹን ነገር እንኳ እንደሚያስታውስ መጽሐፍ ቅዱስ ዋስትና ይሰጠናል። (ማርቆስ 12:41-44) ታዲያ ይህ፣ አድናቂ ወደሆነው ወደዚህ አምላክ ይበልጥ ለመቅረብ አያነሳሳህም? ወደ እሱ ከቀረብክ በቃሉ ውስጥ እንደተጻፈው ‘ከልብ ለሚፈልጉት ወሮታ ከፋይ’ እንደሆነ ራስህ ማረጋገጥ ትችላለህ።—ዕብራውያን 11:6
በግንቦት ወር የሚነበብ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል፦
◼ ከኤርምያስ 32 እስከ 50
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አቤሜሌክ “ጃንደረባ” ተብሎ ተጠርቷል። (ኤርምያስ 38:7) ይህ ቃል፣ በቀጥታ ሲወሰድ ስልብ የሆነ ወንድን የሚያመለክት ቢሆንም በቤተ መንግሥት ውስጥ ኃላፊነት ያለውን ማንኛውንም ሰው ለማመልከትም ተሠርቶበታል።