መጽሔት ለማበርከት ጊዜ መድብ
1 ይሖዋ መንገዶቹን የሚከተሉ ሁሉ ‘ሰላም፣ ሕይወትና ተስፋ ይኖራቸዋል’ ብሏል። (ኤር. 29:11) ስለዚህ ተስፋ የሚያብራሩ ትምህርቶች ወቅታዊ በሆነ መንገድ በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! መጽሔቶች ይቀርባሉ። እነዚህ መጽሔቶች በማንኛውም ሁኔታ ለሚገኙ ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ይጠቅማሉ። (1 ጢሞ. 2:4) አንተና ቤተሰብህ መጽሔት የምታበረክቱበት ቋሚ ጊዜ መድባችኋልን?
2 ይህ ሥራ በኢትዮጵያ ለምንገኘው አዲስ እንደመሆኑ መጠን በግለት እንደምንሳተፍ አያጠራጥርም። መጽሔቶቹ ለያዟቸው ትምህርቶች ያለህን አድናቆት ሕያው አድርገህ መጠበቅህ በጣም አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች አንዱ ነው። አንድ ሰው እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “መጽሔቶቻችሁን ማንበብ በእውነት አስደሳች ነገር ነው። መጽሔቶቹ መናኛና እንዲያው ተራ ‘አጽናኝ’ ሳይሆኑ ሕይወት ትርጉም ያለው እንዲሆን የሚረዱ መመሪያዎችን የያዙ ናቸው።” መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! ጥንቃቄ የተሞላበት ምርምር ውጤቶች ከመሆናቸውም በተጨማሪ በ“ልባምና ታማኝ ባሪያ” የሚዘጋጁ ምግቦች ናቸው። (ማቴ. 24:45) የሰዎችን ልብ ለመንካት የሚያገለግሉ ውጤታማ መሣሪያዎች ናቸው።
3 የምታበረክታቸው መጽሔቶች የያዟቸውን ትምህርቶች በሚገባ እወቃቸው። አሁን በአካባቢህ ላሉት ችግሮች የሚጠቅሙትን ነጥቦች ፈልግ። በበር ወይም በመንገድ የምታገኛቸውን ወንዶች፣ ሴቶችና ወጣቶች እንዴት እንደምታነጋግር መዘጋጀት ጥሩ ነው። መጽሔቶቹ ግለሰቦችንና ቤተሰቦችን በአጠቃላይ እንዴት እንደሚነኳቸው ለማሳየት ዝግጁ ሁን።
4 በመጽሔት ለመጠቀም ንቁ ሁን፦ በመጽሔት ተጠቅሞ ምስክርነት መስጠት በመስክ አገልግሎት ፕሮግራምህ ውስጥ ትልቅ ቦታ ሊይዝ ይገባል። መጽሔት ለማበርከት በጣም ተስማሚ ሆኖ ያገኘኸው ጊዜ የትኛው ነው? የጉባኤው የመጽሐፍ ጥናት ከመድረሱ በፊት ባለው ጊዜ ለአንድ ሰዓት ያህል ከበር ወደ በር ለመመስከር ሞክረህ ታውቃለህን? በአንዳንድ አካባቢዎች በምሽት ጊዜ የሚሰጠው ምስክርነት ውጤታማ ሆኖ ተገኝቷል። ቅዳሜ በተለያዩ መንገዶች መጽሔት ለማበርከት ተስማሚ የሆነ ጥሩ ቀን ነው። ይሁን እንጂ ሌሎች ቀኖችም ለዚህ ሥራ ተስማሚ ሊሆኑ ይችላሉ። ከቤት ወደ ቤትና ከሱቅ ወደ ሱቅ እየሄዱ ማገልገል የመጽሔት ማበርከቻው ቀን ቋሚ ክፍል ሊሆን ይገባል።
5 እያንዳንዱ አስፋፊ ከእያንዳንዱ የመጽሔት እትም የሚያበረክታቸውን በቂ ቅጂዎች ማዘዝ አለበት። በግል እንዲሁም በጉባኤ ደረጃ ትእዛዛችሁን አስታውቃችኋልን? ይሆናል የሚል አመለካከት ይኑርህ፤ እንዲሁም በመስክ ለምትጠቀምባቸው መጽሔቶች መግዣ የሚሆን ገንዘብ መድብ። አስፈላጊ ከሆነም ምን ያህል መጽሔቶች እንደሚያስፈልግህ እንደገና ገምግም። በዚያው መሠረት ትእዛዝህን አስተካክል። የቆዩ እትሞች ሲኖሩህ እቤታቸው ሄደህ ላጣሃቸው ሰዎች ልትተውላቸው ትችላለህ። ይህን ስታደርግ ግን በመንገድ የሚተላለፉ ሰዎች መጽሔቶቹን በማያዩበት ሁኔታና በቤቱ ውስጥ ሰው እንደሌለ በማያስመስል መንገድ በጥንቃቄና በማመዛዘን መሆን ይኖርበታል። የቆዩ ቅጂዎችን ጡረታ የወጡ ሰዎቸ በሚኖሩባቸው ቤቶችና በግል ክሊኒኮች እንዲሁም በሚፈቀድባቸው ሆስፒታሎች ትቶ መሄድ ይቻላል። እነዚህ መጽሔቶች ሁሉ እንደተበረከቱ ተደርገው ሊቆጠሩ ይችላሉ፤ በወሩ መጨረሻም በመስክ አገልግሎት ሪፖርት መመለሻ ቅጽ ላይ መመዝገብ አለባቸው።
6 ከላይ የቀረቡትን ሐሳቦች ከሠራህባቸው ልታበረክት የምትችለውን የመጽሔት ቁጥር ከፍ ልታደርግ እንደምትችል አያጠራጥርም። አሁን ባለው ክፉ ሥርዓት ኑሮ የከበደባቸው ልበ ቅን ሰዎች በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! እንደሚወጡት ያሉ አእምሮን የሚያድሱና መንፈስን የሚያነቃቁ ትምህርቶች ቢያገኙ ደስ ይላቸዋል። እነዚህ መጽሔቶች በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ከልብ ለሚፈልጉ ሁሉ አስፈላጊውን መንፈሳዊ ምግብ ያቀርባሉ። ስለዚህ በአገልግሎት ክልልህ እነዚህን መጽሔቶች ለማበርከት ንቁ ሁን፤ የበለጠ ለማሰራጨት የምትችልባቸውን ተጨማሪ መንገዶችም ፈልግ።