ተከታዮቹ እንዲሆኑ አበረታቷቸው
1 ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 3:6 ላይ “እኔ ተከልሁ አጵሎስም አጠጣ ነገር ግን እግዚአብሔር ያሳድግ ነበር” ሲል ጽፏል። ጳውሎስ ይህን ሐሳብ የተጠቀመው በክርስቶስ ራስነት ሥር በአንድነት የመሥራትን አስፈላጊነት እንዲያስተውሉ ወንድሞቹን ለመርዳት ነበር። በዚህ መንገድ በጣም አስፈላጊ በሆነው የመትከልና የማጠጣት ሥራ የሚጫወቱትን ወሳኝ ሚና እንዲገነዘቡም ረድቷቸዋል።
2 ያ ሕይወት አድን ሥራ ወደ ፍጻሜ የሚደርሰው በዚህ ዘመን ነው። ራሳችንን የወሰንን ክርስቲያኖች እንደመሆናቸን መጠን ሌሎች የክርስቶስ ተከታዮች እንዲሆኑ የመርዳት ከባድ ኃላፊነት ተጥሎብናል። (ሥራ 13:48) ቀደም ሲል የቀሰቀስከውን የሰዎችን ፍላጎት ተከታትለህ ማሳደግ የምትችለው እንዴት ነው? ከዚህ ቀጥሎ አንዳንድ ሐሳቦች ቀርበዋል:-
3 ሰዎች ያሳዩትን ፍላጎት መኮትኮት:- “ባለፈው ጊዜ ሥራ ቢበዛብዎትም ባደረግነው አጭር ውይይት የወደፊቱ ጊዜ እንደሚያሳስቦት ገልጸውልኝ ነበር። በራእይ 1:3 ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ዘመኑ እንደቀረበ’ እንደሚናገር አንብበን እንደ ነበር ያስታውሳሉ። ይህም በሁላችንም የወደፊት ሕይወት ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ አለው። ይህ መጽሐፍ ስለ ጥቅሱ ምን እንደሚል ልብ ይበሉ። [ራእይ መደምደሚያው ከተባለው መጽሐፍ በገጽ 17 አንቀጽ 11 ላይ ያለውን ሐሳብ አንብብ።] ይህ ጽሑፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ያሉትን ትንቢቶች በሙሉ በአጭሩ የሚያብራራ ከመሆኑም በላይ እኛ በግል እንዴት መጠቀም እንደምንችል ይጠቁማል። የበለጠ ለማወቅ ይፈልጋሉ?”
4 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ራእይ መደምደሚያው በተባለው መጽሐፍ መጠቀም:- “እርስዎን እንደገና በማግኘቴ ተደስቻለሁ። ባለፈው ጊዜ በተውኩልዎት መጽሐፍ ውስጥ የሚገኝ አንድ በጣም የሚያበረታታ ተጨማሪ ሐሳብ ላካፍልዎት እሻለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ ለዘላለም ከሚኖሩ ሰዎች ጋር በተያያዘ መንገድ ስለ አንድ ‘የሕይወት መጽሐፍ’ ይናገራል። በዚያ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት የእነማን ስሞች እንደሆኑ ማወቅ ይፈልጋሉ?” ራእይ መደምደሚያው የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 298 ግለጥ። አንቀጽ 11 ካነበብክ በኋላ በአንቀጹ ውስጥ ያሉትን ጥያቄዎች ጠይቅ። አንድ ሁለት አንቀጾችን ከተወያያችሁ በኋላ ተመልሰህ መጥተህ ውይይቱን መቀጠል እንደምትፈልግ ግለጽ።
5 ፍላጎት ለመቀስቀስ በሥዕላዊ መግለጫዎች ተጠቀም:- ራእይ መደምደሚያው የተባለው መጽሐፍ ብዙ ሕያው የሆኑ ሥዕላዊ መግለጫዎች ይዟል። እነዚህን ሥዕሎች በማጉላት ፍላጎት መቀስቀስ ይቻላል። ለምሳሌ ተመላልሶ መጠየቅ ስናደርግ ገጽ 7ን መግለጥ እንችላለን። ዮሐንስ በፍጥሞ ደሴት ውስጥ ሳለ የሚያሳየውን ሥዕል ጠቁም። ራእይ 1:3 ለዮሐንስ የተሰጠው ራእይ አስደሳች መልእክት እንዳለው ያጎላል። ራእይ ስለ አስፈሪ አውሬዎችና ስለ ጥፋት እየተናገረ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? በመጽሐፉ ውስጥ በገጽ 6 ላይ የሚገኙትን አንቀጽ 1 እና 2 አወያየው። በሽፋኑ ውስጠኛ ክፍል ያሉት ሥዕላዊ መግለጫዎችም ሆነ በገጽ 302፣ 308 እና 309 ላይ የሚገኙት ስለ ምድራዊ ገነት የሚጠቁሙ ትዕይንቶች ሊጠቀሱ ይቸላሉ።
6 ጳውሎስ በመከሩ ሥራ ስለሚሳተፍ ሠራተኛ ሲናገር “እንደ ራሱ ድካም መጠን የራሱን ደመወዝ ይቀበላል” ብሏል። (1 ቆሮ. 3:8) ሌሎች የኢየሱስ ተከታዮች እንዲሆኑ ለመርዳት ከፍተኛ ጥረት የምናደርግ ከሆነ ታላቅ ሽልማት እንደምናገኝ የተረጋገጠ ነው።