“ለሁሉም ዓይነት ሰዎች” ስበኩ
1. ውጤታማ ወንጌላውያን ከእጅ ባለሙያዎች ጋር የሚመሳሰሉት እንዴት ነው?
1 አንድ የተዋጣለት የእጅ ባለሙያ የተለያዩ መሣሪያዎች የሚኖሩት ከመሆኑም ሌላ እያንዳንዱን መሣሪያ መቼ እና እንዴት መጠቀም እንዳለበት ያውቃል። በተመሳሳይ እኛም የወንጌላዊነት ሥራችንን እንድንወጣ የሚያግዙን በርካታ መሣሪያዎች አሉን። ለምሳሌ ያህል፣ “ለሁሉም ዓይነት ሰዎች” መስበክ እንድንችል የሚረዱን የተለያዩ ብሮሹሮች ተዘጋጅተውልናል። (1 ቆሮ. 9:22) የዚህ ወር የመንግሥት አገልግሎታችን አንደኛው አባሪ ከእነዚህ ብሮሹሮች መካከል አንዳንዶቹን የያዘ ሲሆን እያንዳንዱ ብሮሹር ለማን ታስቦ እንደተዘጋጀና ብሮሹሩን እንዴት ማበርከት እንደሚቻል ይገልጻል።
2. በአገልግሎታችን ላይ ብሮሹሮችን መጠቀም የምንችለው መቼ ነው?
2 ብሮሹሮቹን የምንጠቀመው መቼ ነው?፦ የእጅ ባለሙያው አንድን መሣሪያ አስፈላጊ በሆነበት ጊዜ ሁሉ ይጠቀምበታል። በተመሳሳይ እኛም አንድ ብሮሹር በሚበረከትበት ወር ብቻ ሳይሆን ለአንድ ሰው ሊጠቅመው ይችላል ብለን በምናስብበት ጊዜ ሁሉ ልናበረክትለት እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ የምናገለግለው የክርስትና እምነት ባልተስፋፋበት ብሎም ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ ያላቸው ፍላጎት አነስተኛ በሆነበት አካባቢ ከሆነ የሚበረከተው ጽሑፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለው መጽሐፍ ቢሆንም እንኳን ተስማሚ የሆነ ብሮሹር ማበርከታችን ጠቃሚ ነው፤ የግለሰቡን የማወቅ ፍላጎት ካነሳሳን በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ ልናስተዋውቀው እንችላለን።
3. ለምሥክርነቱ ሥራ የሚረዱንን መሣሪያዎች በጥበብ መጠቀም ያለብን ለምንድን ነው?
3 መጽሐፍ ቅዱስ በሙያቸው ሥልጡን ስለሆኑ ሰዎች በአድናቆት ይናገራል። (ምሳሌ 22:29) በዛሬው ጊዜ “ቅዱስ” ከሆነው ‘ምሥራቹን የማወጅ ሥራ’ የበለጠ አስፈላጊ ሥራ እንደሌለ የተረጋገጠ ነው። (ሮም 15:16) “ምንም የሚያፍርበት ነገር እንደሌለው ሠራተኛ” ለመሆን ያሉንን መሣሪያዎች በጥበብ ለመጠቀም ጥረት እናደርጋለን።—2 ጢሞ. 2:15