“የግለሰቡን ትኩረት ሊስቡ የሚችሉ የቆዩ መጽሔቶችን ወይም ብሮሹሮችን አበርክቱ”
የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ በማበርከት በመጀመሪያው ቀን ጥናት ለማስጀመር በምንሞክርባቸው ወሮች ላይ የቤቱ ባለቤት ቀደም ሲል መጽሐፉን አግኝቶ ከነበረና ጥናት እንዲጀምር የቀረበለትን ግብዣ ካልተቀበለ “የግለሰቡን ትኩረት ሊስቡ የሚችሉ የቆዩ መጽሔቶችን ወይም ብሮሹሮችን አበርክቱ” የሚል ማበረታቻ ተሰጥቶናል። እንዲህ ያለ ማበረታቻ የተሰጠን ለምንድን ነው?
ብሮሹሮችና የቆዩ መጽሔቶች የተለያዩ ወቅታዊ ርዕሰ ጉዳዮችን ያነሳሉ። ምናልባት በእነዚህ ጽሑፎች ውስጥ ከሚገኙት ሐሳቦች መካከል አንዱ የቤቱን ባለቤት ልብ ሊነካ ይችላል። ስለዚህ ወደ አገልግሎት ስትወጣ የተለያዩ ብሮሹሮችንና የቆዩ መጽሔቶችን ለመያዝ ሞክር። የቆዩ መጽሔቶች ከሌሉህ ደግሞ ምናልባት ከጉባኤህ የመጽሔት ክፍል ማግኘት ትችል ይሆናል። ከዚያም የምታነጋግረው ሰው ቀደም ሲል የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ አግኝቶ ከሆነ እንዲሁም ጥናት ለመጀመር ፈቃደኛ ካልሆነ የያዝካቸውን መጽሔቶች ወይም ብሮሹሮች አውጥተህ በማሳየት የሚፈልገውን እንዲወስድ ልትጋብዘው ትችላለህ። ከዚያ በኋላ ፍላጎቱን ማሳደግ እንድትችል ተመልሰህ ለመሄድ ቀጠሮ ያዝ። ምናልባትም ውሎ አድሮ ግለሰቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ይጀምር ይሆናል።