ጎረቤቶቻችን ምሥራቹን መስማት ያስፈልጋቸዋል
1 የአምላክ ፈቃድ ‘ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ’ ነው። (1 ጢሞ. 2:4) “ሰዎች ሁሉ” የሚለው አባባል ጎረቤቶቻችንን በሙሉ ያጠቃልላል። ምሥራቹን ለጎረቤቶቻችን ለማዳረስ አቀራረባችንን መቀያየርና የምናገኘውን የእያንዳንዱን ሰው ፍላጎት ሊቀሰቅስ የሚችለው ነገር ምን እንደሆነ ማሰብ ይኖርብናል። (1 ቆሮ. 9:19-23) የይሖዋ ድርጅት ‘ለዘላለም ሕይወት የተዘጋጁ’ ሰዎችን ልብ መንካት እንድንችል የሚረዱንን መሣሪያዎች አቅርቦልናል። (ሥራ 13:48) ጎረቤቶቻችን የሚያስፈልጓቸውን መንፈሳዊ ነገሮች ለማሟላት እንድንችል በሐምሌና በነሐሴ ወሮች የተለያዩ ብሮሹሮችን በቅናሽ ዋጋ ማለትም በአንድ ብር እንዴት ማበርከት እንደምንችል እስቲ እንመልከት።
2 የሚበረከቱ ብሮሹሮች፦ አንዳንድ ብሮሹሮችን ስታስተዋውቅ ሊጠቅሙህ የሚችሉ ሐሳቦች ከዚህ በታች በዝርዝር ቀርበዋል። እያንዳንዱ ሐሳብ የሚከተሉትን ነጥቦች ይዟል:- (1) ውይይት ለመጀመር የሚያስችል አንድ ስሜት ቀስቃሽ ጥያቄ፣ (2) ብሮሹሩ ውስጥ ያሉ ለውይይት የሚሆኑ ነጥቦች የሚገኙበትን ቦታ የሚጠቁም መግለጫ፣ በተጨማሪም (3) በውይይቱ መሃል ሊነበብ የሚችል ተስማሚ ጥቅስ። ሰውየው የሚሰጠውን ምላሽ መሠረት በማድረግ የተቀረውን የአቀራረቡን ክፍል በራስህ አባባል ማሟላት ትችላለህ።
በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ ኑር!
በአሁኑ ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ ምን በማድረግ ላይ እንዳለ አስበው ያውቃሉ?—ስዕል 41-2፤ ራእይ 11:15
የአምላክ መንግሥት ገነትን ታመጣለች
ኢየሱስ እንድንጸልይለት ስላስተማረን መንግሥት ማወቅ ይፈልጋሉ?—ገጽ 3፤ ማቴ. 6:9, 10
በሥላሴ ማመን ይገባሃልን?
ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት ማግኘታችን ለወደፊቱ ሕይወታችን ጠቃሚ ነውን?—ገጽ 3፣ አንቀጽ 3, 7-8፤ ዮሐ. 17:3
3 ብሮሹሮች በማበርከት የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለማቅረብ የሚያስችሉ ተጨማሪ ሐሳቦች ከዚህ በታች ቀርበዋል:-
◼ “ወደ እርሶ የመጣነው ጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ወስደን አንድ በጣም አስፈላጊ የሆነ ትንቢት ልንነግርዎት ነው። ትንቢቱን የጻፈው ሐዋርያው ዮሐንስ ሲሆን በራእይ ምዕራፍ 12 ከቁጥር 7 እስከ 12 ላይ ይገኛል። [ጥቅሱን አንብብ ወይም ቢያንስ ዋና ዋናዎቹን ነጥቦች ተናገር።] ይህ ለእኛ ምን ማለት እንደሆነ ያውቃሉ? [ጊዜ ስጠው።] ይህ ጦርነት በእርግጥ በሰማይ ተካሂዷል። በየዕለቱ የሰይጣን ታላቅ ቁጣ ያስከተላቸው መዘዞች በሕይወታችን ላይ ሲደርሱ እንመለከታለን። [አንዳንድ ምሳሌዎችን ጥቀስ። በተጨማሪም የአምላክ መንግሥት ከተባለው ብሮሹር በገጽ 22 ላይ ያለውን ስዕል ወይም በደስታ ኑር! ከተባለው ብሮሹር ስዕል 22 እና 23ን ማሳየት ትችላለህ።] በሕይወታችን ላይ የሚደርሱትን እነዚህን ችግሮች አስመልክቶ አምላክ የሚወስደውን እርምጃ ሌላ ጊዜ መጥቼ ብነግርዎ ደስ ይለኛል። እስከዚያው ድረስ ግን እነዚህን ሁለት ብሮሹሮች 2 ብር ብቻ ከፍለው በመውሰድ እንዲያነቧቸው አበረታታዎታለሁ።” [አንድ ብሮሹር ብቻ ማበርከትም ትችላለህ።] በዚህ አቀራረብ ላይ ጥቂት ማስተካከያዎች በማድረግና ገጽ 10 ላይ ባለው ነጥብ በመጠቀም የሙታን መናፍስት የተባለውንም ብሮሹር ማበርከት ይቻላል።
“የሙታን መናፍስት”
“ለሞት የሚዳርጉ አሳዛኝ አደጋዎች ስለሚከሰቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ ድንኳኖች ተተክለው እናያለን። ማጽናኛ የሚሰጥ አንድ ስዕል ላሳይዎ እፈልጋለሁ። [የሙታን መናፍስት የተባለውን ብሮሹር ገጽ 29 ላይ ገልጠህ በስዕሉ ላይ ሐሳብ ስጥ።] ይህ ስዕል በዮሐንስ ወንጌል ላይ በሚገኙት የኢየሱስ ቃላት ላይ የተመሠረተ ነው። [ዮሐንስ 11:11-14ን ወይም 5:28, 29ን አንብብ።] በዚያን ጊዜ ስለሚኖሩት ተጨማሪ በረከቶች በሚቀጥለው ጊዜ ልንወያይ እንችላለን። እስከዚያው ድረስ ለምን ብሮሹሩን አያነቡም? እስካሁን ከተነጋገርነው በተጨማሪ ብሮሹሩ ራሳችንን ከሰይጣን ጥቃቶች እንዴት መጠበቅ እንደምንችልና አምላክ ምድርን እንዴት ገነት እንደሚያደርግ ይገልጻል። [ብሮሹሩን አበርክት።]”
ለዘላለም ጸንቶ የሚኖረው መለኮታዊው ስም
“ወጣቶችም ሆኑ አረጋውያን ሁሉም ሰዎች ከአምላክ ጋር የጠበቀ ዝምድና እንዲኖራቸው እናበረታታቸዋለን። ሆኖም ብዙ ሰዎች ፈጣሪያችን ስም እንኳ እንዳለው እንደማያውቁ ተገንዝበናል። ኢየሱስ ‘በሰማይ የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ’ ብለን እንድንጸልይ ባስተማረበት ወቅት ስለ አምላክ ስም ተናግሯል። በዚህ ብሮሹር አማካኝነት ስሙን በተመለከተ ይበልጥ ለማወቅ ይችላሉ።” [በገጽ 31 ላይ “የአምላክን ስም ከማወቅ የሚገኙ በረከቶች” የሚለውን ንዑስ ርዕስ ካሳየኸው በኋላ መለኮታዊው ስም የተባለውን ብሮሹር አበርክትለት።]
4 መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዳ ብሮሹር፦ መጀመሪያ በሄድንበት ጊዜም ሆነ ተመላልሶ መጠየቆች ስናደርግ የአገልግሎታችን ዓላማ ምንጊዜም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር መሆን አለበት። በቀላሉ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመርና ለመምራት ቀጥሎ የቀረበው ብሮሹር ሊረዳን ይችላል:-
አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው?
በየሳምንቱ 30 ደቂቃ ወይም ከዚያ የሚያንስ ጊዜ በመመደብ በ16 ሳምንታት ውስጥ መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ማግኘት እንደሚችሉ ያውቃሉ?—ትምህርት 2 አንቀጽ 6፤ 2 ጢሞ. 3:16, 17
5 ኢየሱስ ስለ ደጉ ሳምራዊ በተናገረው ምሳሌ ላይ እውነተኛ ጎረቤት የሚባለው ችግር ላይ ለወደቀ ሰው ፍቅርና ደግነት የሚያሳይ ሰው መሆኑን በግልጽ ተናግሯል። (ሉቃስ 10:27-37) ባልንጀሮቻችን መንፈሳዊ ችግር አለባቸው። ምሥራቹን መስማት ያስፈልጋቸዋል። ምሥራቹን የማካፈል ኃላፊነታችንን ስንወጣ እውነተኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መሆናችንን እናሳያለን።—ማቴ. 24:14፤ ገላ. 5:14