ብሮሹሮችን በማበርከት ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ፈልጎ ማግኘት
1 ብሮሹሮች ኃይለኛ መሣሪያዎች ናቸው። 32 ገጾች ብቻ ያለው አንድ ብሮሹር ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነቶችን በሚገባ ሊያስጨብጥ እንዲሁም ከአምላክ እውቀት ጋር የሚጋጩ ሐሳቦችንና ትምህርቶችን ሊያፈርስ ይችላል። — 2 ቆሮንቶስ 10:5
2 እንደ አንድ አካል ሆነው በዓለም ዙሪያ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርጉት የይሖዋ ምሥክሮች የተባለውን ብሮሹር ካነበበ በኋላ አንድ ሰው እንዲህ ብሎ ለመጻፍ ተገፋፍቷል:- “እንዲህ ዓይነት ድርጅት በፍጹም አይቼ አላውቅም። . . . ሃይማኖታዊ ግብዝነት በበዛበት በዚህ ዘመን ውስጥ የአምላክን ፈቃድ በቁምነገር የሚይዙ ሰዎች ማግኘት በጣም የሚያስገርም ነው።” አንድ በአፍሪካ ውስጥ የሚገኝ ጠንቋይ በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን ብሮሹር አጠና። ይህ ብሮሹር በዚህ ሰው ላይ ምን ውጤት አስከተለ? የጥንቆላ ተግባሩን ተወ፤ እንዲሁም ከመጀመሪያ ሚስቱ በስተቀር አብረውት የሚኖሩትን ሌሎች ሴቶች አሰናበታቸው። ከዚያም የመጀመሪያ ሚስቱን በሕግ አገባት።
3 በሥላሴ ማመን ይኖርብሃልን? የተባለው ብሮሹር በማስረጃ የተደገፈ፣ ምክንያታዊና ውጤታማ የሆነ ለእውነት የቆመ መሣሪያ ነው። በጃማይካ ዌስት ኢንዲስ ለሚታተመው ዘ ሰንዴይ ግሊነር ለተባለው ጋዜጣ ሃይማኖት ነክ ጉዳዮችን የሚጽፉ አንድ ሰው ስለዚህ ብሮሹር አስተያየታቸውን ሲሰጡ እንዲህ ብለዋል:- “ጽሑፉ የምሥክሮቹ ድንቅ ሥራ ነው። አሁን የሥላሴም ሆነ የሁለት አምላክ አማኝ አደጋ ላይ ወድቋል። ቡክሌቱ የሥላሴ ትምህርት ከመጽሐፍ ቅዱስ የተገኘ አለመሆኑን ለማሳየት ከታሪካዊና ከቲኦሎጂያዊ ምንጮች በመጥቀስ ብዙ ማስረጃዎችን ያቀርባል። . . . ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው የሚለውን አመለካከት በመቃወም በምሥክሮቹ የተዘጋጁትን አሳማኝና ከበድ ያሉ የመከራከሪያ ነጥቦች መጠነኛ የቤተ ክርስቲያን እውቀት ያላቸው ቀርቶ ጥሩ እውቀት አለን የሚሉትም እንኳን ይቋቋሙታል ብሎ ማሰቡ ለዚህ የሃይማኖት ነክ ጉዳዮች ጸሐፊ አስቸጋሪ ነው።”
4 በሚገባ ተጠቀሙባቸው፦ ውጤታማ ለመሆን ከተፈለገ እነዚህ ማራኪና እውቀት ሰጪ የሆኑ መሣሪያዎች ለሚያነቧቸው ሰዎች መበርከት አለባቸው። የተለያዩ ሐሳቦችን የያዙ ልዩ ልዩ ብሮሹሮች ስላሉን ለምንመሰክርለት ግለሰብ ተስማሚ ነው ብለን የምናስበውን ብሮሹር ለማበርከት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። የብሮሹሮቻችንን ይዘት ጥሩ አድርጎ ማወቅና የተለያዩ ብሮሹሮችን በቅርብ መያዝ በመስክ አገልግሎት፣ በቤት ወይም በማንኛውም ቦታ በሚገባ እንድንጠቀምባቸው ያስችለናል።
5 ለምሳሌ ያህል በሕዝበ ክርስትና የሥላሴ ትምህርት ግራ የተጋባ ወይም ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው ብሎ የሚያስብ ሰው ስታነጋግሩ በየትኛው ብሮሹር ትጠቀማላችሁ? አፍቃሪ የሆነ አምላክ ይህን ሁሉ መከራ ለምን ይፈቅዳል ብሎ ለሚጠይቅ ሰው የሚያስፈልገው የትኛው ብሮሹር ነው? ሰዎችን የሚጠቅም መንግሥት ማስፈለጉ እንደሚያሳስበው ለሚገልጽልህ ሰው ተስማሚ ሊሆን የሚችለው ብሮሹር የትኛው ነው?
6 የትኛውን ብሮሹር እንደምንጠቀም ከማወቅ በተጨማሪ ብሮሹሩ ስለያዛቸው ሐሳቦች በመጥቀስ የሰውየውን ፍላጎት ለመቀስቀስ መጣር አለብን። ሁኔታዎቹ ከፈቀዱልህ ትምህርቱን እንዲያነበው የሰውየውን ፍላጎት ሊቀሰቅስ የሚችል ሐሳብ ወይም ሥዕላዊ መግለጫ አሳየው አለዚያም አንድ ወይም ሁለት አንቀጾችን አብረኸው አንብበህ የተጠቀሱትን ጥቅሶች አውጣና ተወያይበት። በዚህ መንገድ ግሩም የሆኑ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ተጀምረዋል።
7 ብሮሹሮቻችን ቅዱስ ጽሑፋዊ የሆኑ መልሶችን ይሰጣሉ፤ እንዲሁም በዓለም ውስጥ በሚሠሩት አስጸያፊ ነገሮች ለሚያዝኑና ለሚተክዙ ሰዎች ተስፋ ያዘሉ ናቸው። (ከሕዝቅኤል 9:4 ጋር አወዳድር) በግ መሰል የሆኑት ሰዎች እነዚህ ጽሑፎች የያዟቸውን መልዕክቶች ይቀበላሉ። ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ስንፈልግ በሁሉም ዓይነት የአገልግሎታችን ዘርፎች በብሮሹሮች በጥሩ ሁኔታ እንጠቀም።