አገልግሎታችሁን ለማስፋት አሁኑኑ እቅድ አውጡ
1. በመታሰቢያው በዓል ሰሞን ምን የማድረግ ልዩ አጋጣሚ አለን? ይህን ለማድረግ መዘጋጀት የምንችለውስ እንዴት ነው?
1 በየዓመቱ በመታሰቢያው በዓል ሰሞን ይሖዋን ‘በአንደበታችን እጅግ ለማመስገን’ የሚያስችል አጋጣሚ እናገኛለን። (መዝ. 109:30) ታዲያ ቤዛውን ላዘጋጀልን አምላክ ያላችሁን አድናቆት ለማሳየት በመጋቢት ወር አገልግሎታችሁን ማስፋት ትችላላችሁ? ይህን ማድረግ እንድትችሉ አሁኑኑ እቅድ ማውጣት መጀመር አለባችሁ።—ምሳሌ 21:5
2. ባለፈው ዓመት በሚያዝያ ወር ከረዳት አቅኚዎች ሰዓት ጋር በተያያዘ ለተደረገው ዝግጅት ምን ተሰምቷችሁ ነበር? ብዙዎችስ ምን ምላሽ ሰጥተዋል?
2 ረዳት አቅኚነት፦ ባለፈው ዓመት በሚያዝያ ወር ከረዳት አቅኚዎች ከሚጠበቀው ሰዓት ጋር በተያያዘ የተደረገው ማስተካከያ ጉባኤዎችን በጣም አስደስቷቸው ነበር። አንድ ወንድም እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ስለሆንኩ እስካሁን የዘወትር አቅኚ ሆኜ ማገልገል አልቻልኩም። ይሁንና በሚያዝያ ወር፣ 30 ሰዓት በማገልገል ረዳት አቅኚ ለመሆን አመለክትና 50 ሰዓት ለማገልገል ጥረት አደርጋለሁ።” የሙሉ ቀን ሥራ ያላት አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “ሠላሳ ሰዓት፣ ይህን ያህል ማገልገልማ በጣም ቀላል ነው!” በ80ዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ አቅኚ የነበሩ አንዲት እህት ዝግጅቱን አስመልክቶ ማስታወቂያ ሲነገር እንዲህ በማለት ተናግረዋል፦ “ይህ ለረጅም ጊዜ ስጠብቀው የነበረ አጋጣሚ ነው! ይሖዋ፣ አቅኚነት ምን ያህል ያስደስተኝ እንደነበር ያውቃል!” ረዳት አቅኚ ሆነው ማገልገል ያልቻሉ አስፋፊዎች ደግሞ በአገልግሎት የበለጠ ለመሳተፍ እቅድ አውጥተው ነበር።
3. በመጋቢት፣ በሚያዝያ እና በግንቦት ወሮች ረዳት አቅኚ ሆነን እንድናገለግል የሚገፋፉን ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
3 በዚህ ዓመትም ተመሳሳይ ዝግጅት ስለተደረገ በመጋቢት ወር 30 ወይም 50 ሰዓት በማገልገል ረዳት አቅኚ መሆን ይቻላል። ከዚህም በተጨማሪ ከቅዳሜ፣ መጋቢት 17 ጀምሮ ሰዎችን ሚያዝያ 5 ቀን በሚከበረው የመታሰቢያ በዓል ላይ እንዲገኙ ለመጋበዝ ልዩ ዘመቻ ስለሚደረግ በዚህ ዘመቻ መካፈል እንችላለን። ብዙዎች በመጋቢት ወር አገልግሎት ላይ ከፍ ያለ ተሳትፎ ማድረጋቸው ደስታ ስለሚያስገኝላቸው በሚያዝያ እና በግንቦትም 50 ሰዓት በማገልገል ረዳት አቅኚ ሆነው መቀጠላቸው የማይቀር ነው።
4. በአገልግሎት የምናደርገውን ተሳትፎ መጨመር የምንችለው እንዴት ነው? ይህስ ምን ጥቅም ያስገኝልናል?
4 በቀጣዩ ጊዜ በምታደርጉት የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችሁ ላይ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል በመታሰቢያው በዓል ሰሞን አገልግሎቱን ማስፋት ስለሚችልበት መንገድ ለምን አትወያዩም? (ምሳሌ 15:22) ይሖዋ ጥረታችሁን እንዲባርክላችሁ ጸልዩ። (1 ዮሐ. 3:22) በአገልግሎት የምታደርጉትን ተሳትፎ መጨመራችሁ፣ ይሖዋን የበለጠ ለማወደስ የሚረዳችሁ ከመሆኑም ሌላ ደስታችሁ እንዲጨምር ያደርጋል።—2 ቆሮ. 9:6