በአገልግሎት ረገድ ክህሎታችንን ማዳበር—ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን በማስታወሻ ላይ መመዝገብ
“ለራስህና ለምታስተምረው ትምህርት ምንጊዜም ትኩረት ስጥ።” (1 ጢሞ. 4:16) ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የጻፈው ይህ በመንፈስ መሪነት የተነገረ ምክር፣ አዲሶችም ሆንን ተሞክሮ ያለን እድገት ማድረጋችንን መቀጠል እንዳለብን ያሳያል። በዚህ ረገድ እኛን ለመርዳት ከዚህ እትም ጀምሮ “በአገልግሎት ረገድ ክህሎታችንን ማዳበር” የሚል አዲስ ተከታታይ ርዕስ በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ ይወጣል። እያንዳንዱ ርዕሰ ትምህርት፣ ከአገልግሎታችን ጋር በተያያዘ አንድ ጠቃሚ ክህሎት የሚያብራራ ሲሆን ይህን ክህሎት ማዳበር ስለሚቻልበት መንገድ የተወሰኑ ሐሳቦችንም ያቀርባል። እያንዳንዱ ርዕስ ሲወጣ ሁሉም በወሩ ውስጥ ያንን ክህሎት በአገልግሎት ላይ ተግባራዊ ለማድረግ ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ ይበረታታሉ። ወሩ ካበቃ በኋላ፣ በዚያ ክህሎት ላይ ትኩረት ማድረጋችን እንዴት እንደጠቀመን እንድንናገር የሚጋብዝ ክፍል በአገልግሎት ስብሰባ ላይ ይቀርባል። በዚህ ወር እንድንሠራበት የምንበረታታው ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን በማስታወሻ ላይ እንድንመዘግብ ነው።
አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? የተሰጠንን ተልዕኮ ለመፈጸም ከመስበክ ያለፈ ነገር ማድረግ ይጠይቅብናል። ፍላጎት ወዳሳዩ ሰዎች ተመልሰን መሄድና ማስተማር አለብን፤ በሌላ አባባል የዘራነውን የእውነት ዘር ውኃ ማጠጣት ይኖርብናል። (ማቴ. 28:19, 20፤ 1 ቆሮ. 3:6-9) ይህን ለማድረግ ደግሞ ያነጋገርነውን ግለሰብ እንደገና ፈልገን ማግኘት፣ ስለሚያሳስቡት ጉዳዮች አንስተን መነጋገር እንዲሁም ቀደም ሲል በተወያየንበት ርዕሰ ጉዳይ ላይ ተመሥርተን ውይይቱን መቀጠል ያስፈልገናል። በመሆኑም ፍላጎት ያለው ሰው ስናገኝ ማስታወሻ መያዛችን አስፈላጊ ነው።
ይህን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?
• ፍላጎት ያለውን ሰው መዝግባችሁ ለመያዝ እንድትችሉ በአገልግሎት ቦርሳችሁ ውስጥ ማስታወሻ ለመያዝ የሚያስፈልጉ መሣሪያዎችን መያዛችሁን አትርሱ። ማስታወሻችሁ ንጹሕና ያልተዝረከረከ እንዲሁም ወቅታዊ የሆኑ መረጃዎችን የያዘ እንዲሆን ጥረት አድርጉ። አንድ ሰው እንዳነጋገራችሁ ወዲያውኑ በማስታወሻችሁ ላይ መዝግቡት።
• ስላነጋገራችሁት ሰው የሚገልጽ መረጃ አስፍሩ። የግለሰቡን ስም እንዲሁም አድራሻውን ጻፉ፤ ለምሳሌ ያህል የቤቱን ምልክት፣ ስልክ ቁጥሩን ወይም የኢ-ሜይል አድራሻውን ጻፉ። ግለሰቡን ወይም ቤተሰቡን በመመልከት ያስተዋላችሁት ትኩረት ልትሰጡት የሚገባ ነገር አለ?
• ስለተወያያችሁበት ጉዳይ ዝርዝር ነገሮችን አስፍሩ። የትኞቹን ጥቅሶች አንብባችኋል? ስለሚያምንበት ነገር ምን የተናገረው ሐሳብ አለ? የትኛውን ጽሑፍ አበርክታችሁለታል? የተነጋገራችሁበትን ዕለትና ሰዓቱን መዝግቡ።
• በሚቀጥለው ጊዜ ስትመጡ ምን ለማድረግ እንዳሰባችሁ ጻፉ። ስለ ምን ጉዳይ ለመወያየት ቀጠሮ ይዛችኋል? ተመልሳችሁ እንደምትመጡ የተናገራችሁት ለመቼ ነው?
• ግለሰቡን ተመልሳችሁ ባነጋገራችሁት ቁጥር የምታገኟቸውን ሌሎች መረጃዎች አስፍሩ። ስለ ግለሰቡ ከሚያስፈልጋችሁ የበለጠ ሌሎች መረጃዎችን ማስፈራችሁ ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም።
በዚህ ወር እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦
• ማስታወሻችሁ ላይ በምትመዘግቡበት ወቅት ምን ምን ነገሮችን እየጻፋችሁ እንደሆነ አብረዋችሁ ለሚያገለግሉት ንገሯቸው።