ክርስቲያናዊ ሕይወት
ትራክቶችን ተጠቅሞ ውይይት መጀመር
ከጥር 2018 አንስቶ በክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ ሽፋን ላይ የውይይት ናሙናዎች መውጣት ጀምረዋል። ለሰዎች እንዲሁ ጽሑፍ ከመስጠት ይልቅ ከእነሱ ጋር በመወያየት ላይ እንድናተኩር ተበረታተናል። አስፋፊዎች አቀራረባቸውን እንደ ሁኔታው እንዲያስተካክሉ ለመርዳት ሲባል መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ ተጠቅሞ ውይይት መጀመር የሚቻለው እንዴት እንደሆነ የሚያሳዩ የውይይት ናሙና ቪዲዮዎች ቀርበዋል። እንዲህ ሲባል ግን ከቤት ወደ ቤት ስንሰብክ ጽሑፎችን መጠቀም አይኖርብንም ማለት ነው? በፍጹም! ለምሳሌ ትራክቶች ውይይት ለመጀመር የሚያስችሉ ውጤታማ መሣሪያዎች ናቸው። የሚከተለውን ዘዴ የትኛውንም ትራክት ለማበርከት ልትጠቀምበት ትችላለህ፦
በፊተኛው ገጽ ላይ ያለውን ጥያቄ የቤቱን ባለቤት ጠይቀውና አማራጮቹን አንብብለት።
በሁለተኛው ገጽ አናት ላይ የሚገኘውን ጥቅስ(ሶች) ተጠቅመህ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን መልስ አሳየው። ጊዜ የሚፈቅድልህ ከሆነ በትራክቱ ውስጥ የሚገኙትን ሌሎች ነጥቦች አንብበህ ተወያዩበት።
ትራክቱን ለቤቱ ባለቤት ስጠው፤ ከዚያም የቀሩትን ነጥቦች ሲመቸው እንዲያነባቸው አበረታታው።
ከመሄድህ በፊት “ምን ይመስልሃል?” በሚለው ሥር ያለውን ጥያቄ አሳየውና መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን መልስ በሚቀጥለው ጊዜ ለመወያየት ቀጠሮ ያዝ።
ተመልሰህ ስትሄድ ባለፈው ባነሳኸው ጥያቄ መልስ ላይ ተወያይ፤ ከዚያም በቀጣዩ ጊዜ የምትወያዩበት ሌላ ጥያቄ አንሳ። ጥያቄውን ከድረ ገጻችን ወይም በትራክቱ የጀርባ ገጽ ከተጠቀሰው ጽሑፍ ላይ መምረጥ ትችላለህ። ተገቢ እንደሆነ በተሰማህ ጊዜ ላይ፣ ከአምላክ የተላከ ምሥራች! የተባለውን ጽሑፍ ወይም በማስተማሪያ መሣሪያዎቻችን ውስጥ የሚገኝ ሌላ ማጥኛ ጽሑፍ አስተዋውቅ።