ከአምላክ ድርጅት ጋር ተቀራርቦ መኖር
በሮይ ኤ ሪያን እንደተነገረው
ሳንድሂል ሚዞሪ ተብሎ መጠራቱ ተገቢ ነው። ምክንያቱም ለጥ ባለው የገጠር አካባቢ ከአሸዋ ጉብታ የበለጠ ሆኖ አይታይም። ይህች የብዙ መንገዶች መገናኛ የሆነች መንደር ከሩትሌጅ ወደ ምዕራብ አምስት ኪሎሜትር ብቻ ርቃ የምትገኝ ስትሆን ስምንት ወይም ዘጠኝ ቤቶች፣ አንድ የሜቶዲስት ቤተክርስቲያንና አንዲት ትንሽ የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቅ ብቻ ይገኙበታል። ጥቅምት 25 1900 የተወለድኩት በዚህች መንደር ነበር።
አባቴ የመንደር ቀጥቃጭ ነበር። ወላጆቼ ወደ ቤተክርስቲያን የሚሄዱት አልፎ አልፎ ቢሆንም እናቴ በሜቶዲስት ቤተ ክርስቲያን ወዳለው የእሁድ ትምህርት ቤት ትልከኝ ጀመር። አንድ ሰው ክርስቲያን መባል አለበት ብዬ አምን ስለነበር ሜቶዲስት የሚለውን ስም አልወደውም ነበር። ሆኖም ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነትና ለዘላለም ሕይወት ፍላጎትና ጥማት አደረብኝ።
ዕድሜዬ 16 ዓመት በሆነ ጊዜ በሳንታ ፌ የባቡር ሐዲድ ለመቀጠር ሄድኩ። ስሙ ጂም የተባለ ከዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች (የይሖዋ ምሥክሮች በዚያን ጊዜ የሚጠሩበት ስም ነው) አንዱ የሆነ ሰው ከእኛ የባቡር ሐዲድ ጓድ ጋር ለመሥራት መጣ። እኔና እሱም ዘወትር አብረን እንሠራ ነበር። ጂም ሲነግረኝ እኔም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን አዳመጥኩ። ጥሩ እንደሆነ ስለተሰማኝ ከመጻሕፍቱ አንዱን እንዲያውሰኝ ጠየቅሁት።
ጂም በዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ማህበሩ ሲ.ቲ ራስል የታተመውን እስተዲስ ኢን ዘ እስክሪፕቸርስ (የቅዱሳን ጽሑሮች ጥናት) የመጀመሪያውን ጥራዝ አዋሰኝ። ስመልስለት ሌሎቹንም ጥራዞች እንዲያውሰኝ አደረግሁ። ከዚያ በኋላ ጥቂት ቆይቶ ጂም የባቡር ሐዲድ መሥሪያ ቤት ለቆ ሄደ። ከዚያ በኋላ በድጋሚ ያየሁት በሩትሌጅ ጎዳና ላይ ጥሩ ጥሩ ሥዕሎች ያሉበትን የፍጥረት ታሪክ ፎቶ ትርኢት የተሰኘውን መጽሐፍ የሚፈልጉ ሰዎች ሲጠይቁት ነበር። በኋላ በራሱ ቤት በሚካሄደው የቡድን ስብሰባ እንድገኝ ጋበዘኝ። በየሳምንቱ እሁድ በስብሰባው ላይ ለመገኘት አምስቱን ኪሎሜትር በእግሬ እሄድ ነበር።
ወርቃማው ዘመን (ዛሬ ንቁ! የተሰኘው) መጽሔት በ1919 መታተም ሲጀምር የመስክ አገልግሎት ለመጀመር ፈለግሁ። ሌላ አንድ አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪና እኔ ይህን አዲስ መጽሔት ከቤት ወደ ቤት ለማደል ወሰንን። በተወለድንበት ከተማ የሰዎችን ቤት ማንኳኳት ትንሽ ፍርሃት ስለተሰማን በባቡር ተሳፍረን በአቅራቢያው ወደሚገኝ ሌላ ከተማ ሄድን። በዚህ ሥራ ልምምድ ያልነበረን ቢሆንም ሁለታችንም በየፊናችን ሄድንና እስከ ቀትር ድረስ በሮችን አንኳኳን። ሁለት የኮንትራት ጥያቄዎችን ተቀበልኩ። ከእነዚህም አንዱ በባቡር ሐዲድ አብሮኝ ከሚሠራ ሰው የቀረበ ነበር።
ጥቅምት 1920 በሩትሌጅ አቅራቢያ በሚገኝ አንድ ኩሬ ውስጥ ተጠመቅሁ። ወላጆቼ ከዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጋር መገናኘቴን ተቃወሙ። ይህም የሆነው ከ1914-18 በነበሩት የጦርነት ዓመታት በቀሳውስት አነሳሽነት በመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ላይ የደረሰውን ተቃውሞ ያውቁ ስለነበር ነበር። ይሁን እንጂ በኋላ አባቴ በመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ አንዳንድ ስብሰባዎች ላይ መገኘትና ወርቃማው ዘመን የተባለውን መጽሔት ማንበብ ጀምሮ ነበር። እናቴ ከመሞቷ በፊት ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ እምነታችንን ወደ መቀበል አዘንብላ ነበር። ሆኖም ከቤተሰቦቼ ይህን እውነት የተቀበለ አልነበረም።
የፈተና ጊዜ
በእነዚያ የቀድሞ ጊዜያት በሩትሌጅ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስብሰባዎች ላይ አዘውትረን የምንገኘው ከእኔ ጋር አራት ብቻ ነበርን። ከእኔ ሌላ እነዚያ ሦስቱ የይሖዋን ድርጅት ተው። አንዱ በዚያ አካባቢ የመጽሐፍ ቅዱስ የሕዝብ ንግግር የሚሰጥ በጣም ግሩም ተናጋሪ ነበር። ይሁን እንጂ በችሎታው ኮራና የጥንት ክርስቲያኖች እንደሚያደርጉት ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው ስብከት መካፈል ክብሩን ዝቅ የሚያደርግበት ሆኖ ተሰማው።—ሥራ 5:42፤ 20:20
እነዚህ ሦስት ሰዎች ከዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጋር መተባበራቸውን ሲያቆሙ ኢየሱስ ለሰዎች “የእሱን ሥጋ ስለመብላትና ደሙን ስለመጠጣት” በተናገረ ጊዜ ሐዋርያው ጴጥሮስ የተሰማው ዓይነት ስሜት ተሰማኝ። በዚያ ወቀት በትምህርቱ ተሰናክለው ብዙዎቹ ጥለውት ሄዱ። ኢየሱስ ሐዋርያቱን “እናንተ ደግሞ ልትሄዱ ትወዳላችሁን?” ብሎ ጠየቃቸው። ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ” ብሎ መለሰ።—ዮሐንስ 6:67, 68
ጴጥሮስ “የእሱን ሥጋ ስለመብላትና ደሙን ስለመጠጣት” ሲናገር ምን ማለቱ እንደሆነ ሙሉ በሙሉ ባይረዳም ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ቃል እንዳለው ተገንዝቦ ነበር። እኔም ስለ ድርጅቱ የተሰማኝ እንደዚህ ነበር። በጽሑፎች ላይ የማነበው ነገር ሁሉ ባይገባኝም እውነቱን አግኝቼ ነበር። ሆኖም የማይገባኝ ነገር በሚነገርበት ጊዜ ተከራክሬ አላውቅም። ቆይቶ ጉዳዩ ይብራራል፣ ወይም አመለካከቶች ይስተካከላሉ። ማብራሪያው እስኪሰጥ ድረስ በትዕግሥት በመጠበቄ ሁልጊዜ ደስተኛ ሆኛለሁ።—ምሳሌ 4:18
ከአቅኚነት ሥራ ጋር መለማመድ
ሐምሌ 1924 በኮሎምቦስ ኦሀዮ በተደረገው ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ተገኘሁ። ይህን ስብሰባ ወርቃማው ዘመን “ባለፉት ዓመታት ከተደረጉት ስብሰባዎች ሁሉ የበለጠ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ስብሰባ” በማለት ገልጾታል። በዚያ ስብሰባ ላይ “ክስ” የተሰኘ ቀስቃሽ ውሳኔ ተላልፎ ነበር። በዚያ ስብሰባ ላይ ያገኘሁት ዕውቀትና ያየሁት መንፈስ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ወይም አቅኚ እንድሆን አበረታታኝ።
ከስብሰባው ስመለስ የባቡር ሐዲድ ሥራዬን ተውኩና ከአንድ ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ጋር አቅኚ ሆነን አንድ ላይ ማገልገል ጀመርን። ሆኖም ከዓመት በኋላ የወላጆቼ የጤና ይዞታ ስለተበላሸ የእኔ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሆኑ። አቅኚነቴን ትቼ በቧንቧ መሥመር ኩባንያ ተቀጠርኩ። ነገር ግን እዚያ የሚሠሩት ሰዎች ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑ ባለመሆናቸው ያንንም ሥራ ተውኩና ንብ ማርባትና ማር የመሸጥ ሥራ ጀመርኩ።
እስከ 1933 መጨረሻ ድረስ ሁለቱም ወላጆቼ ስለሞቱ ከግዴታ ነፃ ሆንኩ። ስለዚህ በ1934 ጸደይ ወራት ላይ የንብ እርባታ ሥራዬን ለሌላ ሰው አደራ ሰጠሁና የምኖርበት አንድ ትንሽ ተጎታች ቤት ሠርቼ አቅኚ በመሆን የሙሉ ጊዜ አገልግሎቴን እንደገና ጀመርኩ። መጀመሪያ ላይ በኩዊንስ ኢሊኖይስ ከአንድ በዕድሜ የገፉ ምሥክር ጋር ሠራሁ። በኋላ ወደ ሚዞሪ ተመልሼ በመሄድ ከአቅኚዎች ቡድን ጋር ማገልገል ጀመርኩ።
በ1935 በማዕከላዊው ምዕራብ ከባድ ድርቅ ነበርና እኛም የምንሠራው ሙሉ በሙሉ በእርሻ በሚተዳደር አካባቢ ስለነበር ኑሮ ከባድ ሆነብን። ስለዚህ ማንም ሰው ገንዘብ ስላልነበር ጽሑፎች ስንሰጣቸው ብዙውን ጊዜ የሚሰጡን የምግብ እህልና አንዳንድ ቁሳቁሶችን ነበር።
የአቅኚነት አገልግሎት በደቡብ
በዚያ የክረምት ወራት ቅዝቃዜውን ለመሸሽ ብለን ወደ አርካንስስ ሄድን። በዚያም አካባቢ ብዙ ጽሑፎችን ለማደልና በቆርቆሮ የታሸጉ ብዙ ሸቀጦችን ለማግኘት ችለን ነበር። ብዙ ጊዜም የአሉሚኒየም ዕቃዎችን፣ ያረጁ የነሐስ ወይም የመዳብ ዕቃዎችን፣ ያረጁ መኪናዎች ራዲያተሮችንና ባትሪዎችን እንዲሁም ልንሸጣቸው የምንችል ሌሎች ነገሮችን እንቀበል ነበር። ይህም በአገልግሎት ለምንጠቀምበት የ ኤ ሞዴል ፎርድ መኪናዬ ነዳጅ መግዣ ገንዘብ አስገኘልን።
በተራራማው የኦዝራክ አምባ በሚገኙት የኒውተን፣ ሰርሲና ካሮል አካባቢዎች አገልግለናል። በአርካንሳስ ተራራ ለሚኖሩ ሰዎች ስንሰብክ ያጋጠመን ተሞክሮ አንድ መጽሐፍ ይሞላል። በእነዚያ ጊዜያት የመኪና መንገዶች ያልሠለጠኑ ስለነበሩ ወይም ደግሞ ጭራሹኑ ስላልነበሩ አብዛኛውን ሥራችንን የምንሠራው በእግር በመጓዝ ነበር። በቡድናችን ውስጥ ከነበሩት ውስጥ አንዳንድ አቅኚዎች በተራራው ጫፍ ላይ የሚገኙ ሰዎችን ለማግኘት ሲሉ በፈረስ ይሄዱ ነበር።
አንድ ጊዜ ሳም ስለሚባል ፍላጎት ያሳየ ሰው ሰማንና በመጨረሻ የሚኖረው በተራራው ጫፍ ላይ መሆኑን ሰማን። እጁን ዘርግቶ ተቀበለንና እንድናድር ያቀረበልንን ግብዣ ተቀብለን ስናድር በጣም ደስ አለው። የሳም ሚስት ለመልእክታችን ባታሳይም ሬክስ የሚባል የ16 ዓመት ልጁ ግን ፍላጎት ነበረው። ስንመለስ ሳም እንደገና ተመልሰን እንድንጠይቀው ጋበዘንና ከሁለት ሳምንት በኋላ ተመልሰን እንደገና ከእነሱ ጋር አደርን።
ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሥፍራችን ልንመለስ ስንነሣ እንደገና እንድንመጣ የጋበዘችን የሳም ሚስት ነበረች። ለሬክስ ጥሩ ምሳሌዎች እንደሆንንለት ነገረችን። “መጥፎና ተሳዳቢ የሆነ ልጅ ነው። እናንተ ልጆች እዚህ መጥታችሁ ከሄዳችሁ ወዲህ ግን ብዙም የተሳደበ አይመስለኝም” አለችን። ዓመታት ካለፉ በኋላ ሬክስን በደቡብ ላንሲንግ ኒውዮርክ ጊልያድ ትምህርት ቤት ሲከታተል አገኘሁት። እንደዚህ የመሰሉ ተሞክሮዎች በዓመታቱ ሁሉ ከፍተኛ እርካታ አምጥተውልኛል።
የቤቴል አገልግሎት
አቅኚ ለመሆን ሳመለክት ቤቴል ተብሎ በሚጠራው በኒውዮርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ለማገልገልም አመልክቼ ነበር። በ1935 የጸደይ ወራት ማመልከቻዬ ተቀባይነት እንዳገኘና የቤቴል አገልግሎቴን ለመጀመር በኒውዮርክ ደቡብ ላንሲንግ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የመንግሥት እርሻ ድረስ በመሄድ ሪፖርት እንዳደርግ ተነገረኝ። ወዲያውኑ አንድ ምሥክር ወንድም ተሳቢ ቤቴን እንዲረከበኝ ዝግጅት አደረግሁ።
ሞዴል ኤ ፎርዴን እየነዳሁ ወደ ኒውዮርክ ሄድኩና ግንቦት 3, 1935 ከጧቱ 4:30 ላይ ደረስኩ። ያን ዕለት ከሰዓት በኋል በሰባት ሰዓት ላይ እንጨት የመፍለጥ ሥራ እንድሠራ ተመደብኩ። በሚቀጥለው ቀን ወደ ከብት ማርቢያ ጣቢያ ሄጄ ላሞችን በማለብ ለመርዳት ሪፖርት እንዳደርግ ተነገረኝ። በከብት እርባታ ጣቢያው አንዳንዴ ጧት ጧትና ምሽት ላይ ወተት በማለብና ቀን ቀን ደግሞ በእርሻና በአትክልት ቦታ ላይ ከሚሠሩት ሠራተኞች ጋር በመሥራት አያሌ ዓመታት አሳልፌአለሁ። ንቦችን በመንከባከብም ለቤቴል ቤተሰብ ማር እየቆረጥኩ በማቅረብ ሠርቼአለሁ። በ1953 ወደ አይብ ማውጫ ክፍል ተዛወርኩ።
ለይሖዋ ባለው የትሕትና፣ የታማኝነትና የታዛዥነት አስደናቂ ጠባዩ ሕይወቴን ከነኩት መሃል ዋልተር ጆን “ፓፒ” ቶርን አንዱ ነበር። በ1894 የመጀመሪያዎቹ ፒሊግሪሞች እንዲሆኑ ከተሾሙት 21 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ አንዱ ነበር። ይህም ሥራ በርካታ ጉባኤዎችን ለማበረታታት ከሚጎበኙት የዛሬዎቹ የክልል የበላይ ተመልካቾች ሥራ ጋር ተመሳሳይ ነው። ወንድም ቶርን በተጓዥነት ሥራው ረዥም ዓመታት ካሳለፈ በኋላ ወደ መንግሥት እርሻው በመምጣት በዶሮ ቤት ይሠራ ነበር። በተለያዩ ወቅቶች “ስለራሴ ከፍተኛ ግምት ሰጥቼ በማስብበት ጊዜ ከራሴ ለየት ብዬ በመቆም ራሴን ‘አንተ ትንሽ የአቧራ ብናኝ ለመሆኑ የምትመካበት ምን አለህ’ እለዋለሁ” ብሎ ሲናገር እሰማው ነበር።
ሌላው ለእኔ ምሳሌ የሆነው ትሑት ሰው ዛሬ የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ጆን ቡዝ ነው። በዓመታቱ ሁሉ “ወሳኙ ነገር የምታገለግሉበት ቦታና ደረጃ ሳይሆን በጣም አስፈላጊው ማንን የምታገለግሉ መሆናችሁ ነው” እንዳለ ይጠቅሳል። በጣም ቀላል አነጋገር ሆኖ ግን ትልቅ እውነት ያዘለ ነው! ይሖዋን ማገልገል ከመብቶች ሁሉ የበለጠ መብት ነው!
በቤቴል አገልግሎቴ ከተፈጸሙት ጎላ ያሉ ነገሮች አንዱ በ1943 በመንግሥት እርሻው የጊልያድ የሚስዮናውያን ትምህርት ቤት መከፈት ነው። ከብዙ የዓለም ክፍሎች ከመጡ አቅኚዎች ጋር መገናኘት በእርግጥ አስደሳች ነበር። በዚያ ጊዜ በእያንዳንዱ ኮርስ የሚካፈሉት ተማሪዎች ቁጥር መቶ ያህል ነበር። ስለዚህ በየስድስት ወሩ መቶ አዳዲስ ተማሪዎች ወደ መንግሥት እርሻው ይመጡ ነበር። የምረቃ በዓሎቹ በላይኛው የኒውዮርክ ግዛት ባሉት ገጠርማ እርሻ ቦታዎች ወደሚገኘው የሥልጠና ማዕከል በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ይስባሉ።
የሥራ ለውጥ
የጊልያድ ትምህርት ቤት ወደ ብሩክሊን በተዛወረ ጊዜና በደቡብ ላንሲንግ የነበረው ዋናው የመኝታና የመማሪያ ክፍሎችን የያዘ ሕንፃ ሲሸጥ የከብት እርባታው በዎልክሂል ኒውዮርክ ወደሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ እርሻ ተዛወረ። ስለዚህ በ1969 መጨረሻ ላይ በዎልክሂል ወዳለው እርሻ ተዛወርኩና እስከ 1983 ድረስ አይብ መሥራቴን ቀጠልኩ። ከዚያም የሥራ ለውጥ ተሰጠኝና የአትክልተኝነትና ግቢ የማስዋብ ሥራ ጀመርኩ።
ከጥቂት ጊዜ በፊት ቃለ መጠይቅ በተደረገልኝ ጊዜ ለ30 ዓመታት የአይብ ማውጣት ሥራ ስሠራ ከቆየሁ በኋላ የሥራ ለውጥ ሲሰጠኝ ምን እንደተሰማኝ ስጠየቅ “ምንም አልተሰማኝም” በማለት በግልጽ ተናገርኩ። “ምክንያቱም አይብ የማውጣቱን ሥራ አልወደውም ነበር።” ዋናው ቁም ነገር እኛ ትክክለኛ አስተያየት ካለንና ለአምላካዊ አመራር በትሕትና የምንገዛ ከሆነ በማንኛውም ምድብ ሥራ ይሖዋን ለማገልገል ደስተኞች ልንሆን የምንችል መሆኑ ነው። ስለዚህ ምንም እንኳ አይብ የማውጣትን ሥራ ባልወደውም የቤቴል ቤተሰብን የሚጠቅም ስለሆነ በሥራዬ ደስ ይለኝ ነበር። ታላቁን አምላካችንን ይሖዋን በታማኝነትና ባለማጉረምረም ካገለገልን ምድብ ሥራችን ምንም ይሁን ምን ደስተኞች ልንሆን እንችላለን።
እየደከምኩ በሄድኩባቸው ዓመታት በቤቴል ከማገልገል የተሻለ ነገር ላገኝ እችል ነበር ብዬ አላስብም። ጥሩ እንክብክቤ ይደረግልኛል። ዕድሜዬ 90 ዓመት ቢሆንም ምድብ ሥራዬን በማከናወን ለመቀጠል ችያለሁ። እስከ አሁን ብዙ ዓመታት በዚህ በመጠበቂያ ግንብ እርሻ ላሉ የቤቴል ቤተሰብ አባሎች የጧቱን አምልኮ በሊቀመንበርነት ለመምራት ተረኛ የመሆን መብት አግኝቻለሁ። አጋጣሚ ሳገኝ ወደ ቤቴል የሚመጡ አዳዲሶች የተሰጣቸውን ማንኛውንም ዓይነት የአገልግሎት መብት እንዲጠቀሙበትና በአገልግሎት መብቶቻቸውም እንዲረኩና ደስተኞች እንዲሆን አበረታታቸዋለሁ።
ባለፉት ዓመታት ብዙ ጊዜ የውጭ አገሮችን ለመጎብኘት ችያለሁ። ለምሳሌ ሕንድን፣ ኔፓልን፣ ሩቅ ምሥራቅንና አውሮፓን ጎብኝቻለሁ። የሚከተለው ምክር በዓለም ዙሪያ በየጉባኤዎቻቸው ውስጥ ላሉ የይሖዋ ሕዝቦች ይረዳቸው ይሆናል። እሱም አሁን ባላችሁ ሁኔታ እርኩ በተተከላችሁበትም አፈር ላይ በመንፈሳዊ አብቡ የሚል ነው።
አምላክን ሳልባክን በማገልገል እንድቀጥል ስላስቻለኝ ነጠላ ሆኜ መኖርን መርጫለሁ። ታላቁ አምላካችን ለታማኝነት ሽልማት ይሆን ዘንድ የዘላለም ሕይወት ተስፋ ሰጥቷል። ይህም የዘላለም ሕይወት ለብዙዎች በዚህችው ምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ነው። ለሌሎቻችን ደግሞ ይህ የዘላለም ሕይወት የሚሰጠንን ማንኛውንም ዓይነት ሥራ እንድንሠራ በሰማይ ፍጻሜ የሌለውን ሕይወት በጉጉት መጠባበቅ ነው።
አንዳንዶች የእኔ 90 ዓመት ረዥምና የበለጸገ ሕይወት እንደሆን ይሰማቸው ይሆናል። ሕይወቴ የበለጸገ ይሁን እንጂ ረዥም የሚባል ግን አይደለም። ከአምላክ ድርጅትና ከእውነት ቃሉ ጋር ተቆራኝተን በመኖር ሕይወታችንን ለዘላለም ልናረዝመው እንችላለን።a
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ሮይ ሪያን የሕይወት ተሞክሮውን በሚጽፍበት ጊዜ ጤንነቱ በድንገት አክል ገጠመውና በጧቱ አምልኮ ሊቀመንበር የመሆን ተራውን ከፈጸመ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ሐምሌ 5, 1991 ምድራዊ ሕይወቱን ጨርሷል።
[የገጽ 26 ስዕል]
ወንድም ሪያን በወጣትነት ዘመኑ ከሞዴል ቲ ፎርድ መኪና አጠገብ ቆሞ