የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w12 3/15 ገጽ 7-9
  • ምክር የምትሰጠው እንዴት ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ምክር የምትሰጠው እንዴት ነው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ምክር መጠየቅ ያለብን ለምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ምክር መስጠት የምንችለው እንዴት ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ምርምር ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • አዲስ የምርምር መሣሪያ
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2014
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
w12 3/15 ገጽ 7-9

ምክር የምትሰጠው እንዴት ነው?

ሰዎች ምክር እንድትሰጣቸው ጠይቀውህ ያውቃሉ? ለምሳሌ እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎች ቀርበውልህ ያውቃሉ፦ ‘ምን ባደርግ ይሻላል? ወደዚህ ግብዣ ልሂድ? ይህን ሥራ ልያዝ? ከዚህ ሰው ጋር መጠናናት ልጀምር?’

ሰዎች በቅንነት ተነሳስተው ከወዳጃቸው፣ ከቤተሰባቸው አልፎ ተርፎም ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ዝምድና ሊነካ የሚችል ውሳኔ ማድረግ ሲፈልጉ እርዳታ ይጠይቁህ ይሆናል። ታዲያ የምትሰጣቸው ምክር በምን ላይ የተመሠረተ ነው? ብዙ ጊዜ ምክር የምትሰጠው እንዴት ነው? ግለሰቡ የጠየቀህ ነገር ከባድም ይሁን ቀላል፣ ምሳሌ 15:28 “የጻድቅ ሰው ልብ የሚሰጠውን መልስ ያመዛዝናል” እንደሚል ልብ በል። ቀጥሎ የቀረቡት አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ምክር በመስጠት ረገድ እንዴት ሊረዱህ እንደሚችሉ እስቲ እንመልከት።

1 ስለ ጉዳዩ ትክክለኛ ግንዛቤ ይኑርህ።

“ከማዳመጡ አስቀድሞ የሚመልስ፣ ቂልነትና ዕፍረት ይሆንበታል።”​—ምሳሌ 18:13

ጥሩ ምክር ለመስጠት፣ ምክር የጠየቀህን ግለሰብ ሁኔታና ስለ ጉዳዩ ያለውን አመለካከት መረዳት ይኖርብሃል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው ወደ ቤትህ ለመምጣት የተሻለው መንገድ የትኛው እንደሆነ ስልክ ደውሎ ጠየቀህ እንበል፤ ለግለሰቡ አቅጣጫውን ለመጠቆም ምን ነገር ማወቅ ይኖርብሃል? ግለሰቡ ያለበትን ቦታ ሳታውቅ ሰውየው በየትኛው መንገድ ቢመጣ የተሻለ እንደሆነ መጠቆም ትችላለህ? እንደማትችል የተረጋገጠ ነው። በተመሳሳይም ትክክለኛ ምክር ለመስጠት ግለሰቡ ያለበትን “ቦታ” ማወቅ ማለትም የዚያን ሰው ሁኔታና ስለ ጉዳዩ ያለውን አመለካከት መረዳት ይኖርብሃል። በምንሰጠው ምክር ላይ ተጽዕኖ ሊያደርጉ የሚችሉ ያላወቅናቸው ነገሮች ይኖሩ ይሆን? ሁኔታውን በሚገባ ሳንገነዘብ ምክር የምንሰጥ ከሆነ ግለሰቡ ይበልጥ ግራ ሊጋባ ይችላል።​—ሉቃስ 6:39

ምን ያህል ምርምር እንዳደረገ እወቅ። በተጨማሪም ምክር ለፈለገው ግለሰብ እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን መጠየቅ የጥበብ እርምጃ ሊሆን ይችላል፦ “ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ሊረዱህ የሚችሉ ይመስልሃል?” “ያሉህ አማራጮች ምን ጥቅምና ጉዳት ሊኖራቸው ይችላል ብለህ ታስባለህ?” “በጉዳዩ ላይ ምን ያህል ምርምር አድርገሃል?” “የጉባኤ ሽማግሌዎች፣ ወላጆችህ፣ አስጠኚህ ወይም ሌሎች ሰዎች ምን ምክር ሰጥተውሃል?”

ግለሰቡ የሚሰጠው ምላሽ ስለ ጉዳዩ ለማወቅ ምን ያህል ጥረት እንዳደረገ እንድናስተውል ይረዳናል። በተጨማሪም ሌሎች የሰጡትን ሐሳብ ግምት ውስጥ ያስገባ ምክር ለመለገስ ያስችለናል። ምክር ጠያቂው ግለሰብ፣ እሱ መስማት የሚፈልገውን ብቻ በመናገር ‘ጆሮውን የሚኮረኩርለት’ ሰው እየፈለገ እንደሆነና እንዳልሆነ ለመለየትም ይረዳናል።​—2 ጢሞ. 4:3

2 ያልታሰበበት መልስ አትስጥ።

“ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየና ለቁጣ የዘገየ መሆን አለበት።”​—ያዕ. 1:19

በጉዳዩ ላይ በጥሞና ሳናስብ በቅን ልቦና ተነሳስተን መልስ እንሰጥ ይሆናል። ይሁን እንጂ ምንጊዜም ቢሆን እንዲህ ማድረግ የጥበብ አካሄድ አይደለም፤ በተለይ ደግሞ በምንነጋገርበት ጉዳይ ላይ ጥልቀት ያለው ምርምር አድርገን የማናውቅ ከሆነ በችኮላ መልስ መስጠት ተገቢ አይሆንም። ምሳሌ 29:20 “በችኰላ የሚናገርን ሰው ታያለህን? ከእርሱ ይልቅ ተላላ ተስፋ አለው” ይላል።

የምትሰጠው ምክር ከአምላክ ቃል ጋር ሙሉ በሙሉ የሚስማማ መሆኑን ለማረጋገጥ ጊዜ ወስደህ አሰላስል። ‘“የዓለም መንፈስ” እና አስተሳሰብ በአመለካከቴ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። (1 ቆሮ. 2:12, 13) ምክር ለመስጠት በቅን ልቦና መነሳሳት ብቻውን በቂ የማይሆንበት ጊዜ እንዳለ አስታውስ። ኢየሱስ ከፊቱ ስለሚጠብቀው ከባድ ተልእኮ ሲናገር ሐዋርያው ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ፣ በራስህ ላይ እንዲህ አትጨክን፤ በምንም ዓይነት እንዲህ ያለ ነገር አይደርስብህም” በማለት ኢየሱስን መክሮት ነበር። ጴጥሮስ ካደረገው ነገር ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን? ቅን ልብ ያለው ሰው እንኳ ካልተጠነቀቀ ‘የአምላክን ሳይሆን የሰውን ሐሳብ’ ሊያራምድ ይችላል። (ማቴ. 16:21-23) በእርግጥም ከመናገራችን በፊት ማሰባችን በጣም አስፈላጊ ነው! ደግሞስ እኛ ያለን ተሞክሮ አምላክ ካለው ጥበብ ጋር ሲነጻጸር እጅግ በጣም አነስተኛ አይደለም?​—ኢዮብ 38:1-4፤ ምሳሌ 11:2

3 ትሑት በመሆን የአምላክን ቃል ተጠቀም።

“በራሴ ተነሳስቼ አንዳች ነገር እንደማላደርግ ከዚህ ይልቅ እነዚህን ነገሮች የምናገረው ልክ አብ እንዳስተማረኝ መሆኑን ታውቃላችሁ።”​—ዮሐ. 8:28

“እኔ አንተን ብሆን ኖሮ እንዲህ አደርግ ነበር” ትላለህ? ግለሰቡ ላቀረበው ጥያቄ መልስ መስጠት ያን ያህል ከባድ በማይሆንበት ጊዜም እንኳ ኢየሱስ በትሕትናና ልክን በማወቅ ረገድ የተወውን ምሳሌ መከተል የተሻለ ነው። ኢየሱስ ያለው ጥበብና ተሞክሮ ከማንኛውም ሰው እጅግ የላቀ ቢሆንም እንዲህ ብሏል፦ “እኔ የተናገርኩት በራሴ ተነሳስቼ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ምን እንደምልና ምን እንደምናገር ያዘዘኝ . . . አብ ራሱ ነው።” (ዮሐ. 12:49, 50) ኢየሱስ፣ ያስተማራቸው ትምህርቶችም ሆኑ የሰጣቸው ምክሮች ምንጊዜም ከአባቱ ፈቃድ ጋር የሚስማሙ ነበሩ።

ለምሳሌ፣ ወታደሮች ኢየሱስን ሊይዙት ሲመጡ ደቀ መዛሙርቱ መዋጋት ይኖርባቸው እንደሆነና እንዳልሆነ ኢየሱስን እንደጠየቁት የሚናገር ዘገባ በ⁠ሉቃስ 22:49 ላይ እናገኛለን። እንዲያውም አንደኛው ደቀ መዝሙር ሰይፍ በመምዘዝ እርምጃ ወስዶ ነበር። ኢየሱስ እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ እንኳ ጊዜ ወስዶ የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ ለደቀ መዛሙርቱ እንዳስረዳቸው በ⁠ማቴዎስ 26:52-54 ላይ የሚገኘው ዘገባ እንደሚናገር ልብ በል። ኢየሱስ በ⁠ዘፍጥረት 9:6 ላይ በሚገኘው መሠረታዊ ሥርዓት እንዲሁም በ⁠መዝሙር 22 እና በ⁠ኢሳይያስ 53 ላይ በሚገኙት ትንቢቶች ላይ ተመሥርቶ ጥበብ ያዘለ ምክር ሊሰጥ ችሏል፤ ይህም የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ የረዳ ከመሆኑም በላይ ይሖዋን ደስ እንዳሰኘ ጥርጥር የለውም።

4 በቲኦክራሲያዊ ቤተ መጻሕፍትህ ተጠቀም።

“በተገቢው ጊዜ ምግባቸውን እንዲሰጣቸው ጌታው በአገልጋዮቹ ላይ የሾመው ታማኝና ልባም ባሪያ በእርግጥ ማን ነው?”​—ማቴ. 24:45

ኢየሱስ አስፈላጊ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ የሚያቀርብ ታማኝ ባሪያ ሾሟል። ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ምክር ወይም መረጃ ስትሰጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ለመመርመር በቂ ጊዜ ትመድባለህ?

የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ማውጫ (እንግሊዝኛ) እና ዎችታወር ላይብረሪa በመጠቀም ግልጽ የሆኑ በርካታ መረጃዎችን በቀላሉ ማግኘት እንችላለን። ተዝቆ የማያልቅ መረጃ የምናገኝባቸውን እነዚህን መሣሪያዎች ችላ ማለት እንዴት ያለ ሞኝነት ነው! ምክር የሚፈልጉ ሰዎችን ሊጠቅሙ የሚችሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ርዕሰ ጉዳዮችና በርካታ ጽሑፎች ይገኛሉ። ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዲመረምሩና በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ውሳኔ እንዲያደርጉ በመርዳት ረገድ ምን ያህል የተዋጣልህ ነህ? አንድ ሰው ጂፒኤስ (ግሎባል ፖዚሽኒንግ ሲስተም) በተባለው አቅጣጫ ጠቋሚ መሣሪያ አማካኝነት ያለበትን ስፍራና ሊደርስበት የሚፈልግበትን ቦታ ማወቅ እንደሚችል ሁሉ ምርምር የምናደርግባቸው መሣሪያዎችም አንድ ግለሰብ እየተጓዘ ያለበትን መንገድ እንዲገነዘብና ከዚህ የሕይወት መንገድ እንዳይወጣ ማድረግ ያለበትን ነገር እንዲያስተውል ይረዱታል።

ብዙ ሽማግሌዎች በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ማውጫ እና በዎችታወር ላይብረሪ ተጠቅመው የሚፈልጓቸውን ጽሑፎች እንዴት ማግኘት እንደሚችሉ አስፋፊዎችን አሠልጥነዋል፤ ይህም ወንድሞችና እህቶች በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ ምርምር አድርገው ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ ረድቷቸዋል። ሽማግሌዎች የሚሰጡት እንዲህ ያለው እርዳታ አስፋፊዎች በወቅቱ ለገጠማቸው ችግር መፍትሔ እንዲያገኙ ከማስቻሉም በላይ ምርምር የማድረግ ልማድ እንዲኖራቸውና በይሖዋ መንፈሳዊ ዝግጅቶች የመተማመን መንፈስ እንዲያዳብሩ ያደርጋል። በዚህ መንገድ ወንድሞች “ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንዲችሉ የማስተዋል ችሎታቸውን በማሠራት” ማሠልጠን ችለዋል።​—ዕብ. 5:14

5 ለሌሎች ውሳኔ ላለማድረግ ተጠንቀቅ።

“እያንዳንዱ የራሱን የኃላፊነት ሸክም ይሸከማል።”​—ገላ. 6:5

ዞሮ ዞሮ እያንዳንዱ ግለሰብ የትኛውን ምክር መከተል እንዳለበት ራሱ መወሰን ይኖርበታል። ይሖዋ እሱ ባወጣቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች ለመመራት ወይም ላለመመራት የመወሰን መብት ሰጥቶናል። (ዘዳ. 30:19, 20) አንድ ግለሰብ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንዲመረምርና በዚያ ላይ ተመሥርቶ የራሱን ውሳኔ እንዲያደርግ የሚያስገድዱ አንዳንድ ሁኔታዎች አሉ። የጉዳዩን ክብደት ወይም ምክር የጠየቀንን ሰው ዕድሜ ግምት ውስጥ በማስገባት ‘በዚህ ጉዳይ ላይ ምክር የመስጠት መብት አለኝ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብን ይሆናል። አንዳንድ ጉዳዮች በጉባኤ ሽማግሌዎች ቢያዙ ወይም ምክር ጠያቂው ዕድሜው አነስተኛ ከሆነ ጉዳዩን ለወላጆቹ መተው የተሻለ ይሆናል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በሲዲ የተዘጋጀው ዎችታወር ላይብረሪ በአሁኑ ጊዜ በ39 ቋንቋዎች ይገኛል። የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ማውጫ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ ከ45 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይገኛል።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

በቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራም ወቅት የሚደረግ ምርምር

በቅርቡ ለቀረቡልህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ፕሮግራም አውጥተህ ለምን ምርምር አታደርግም? አንድ ሰው ከታች እንዳሉት ዓይነት ጥያቄዎች ቢያቀርብልህ ጥያቄውን ለመመለስ የሚረዱትን ጽሑፎችና የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው? ለምሳሌ አንድ ሰው ‘ከእገሌ ጋር መጠናናት ብጀምር ምን ይመስልሃል?’ ብሎ ጠየቀህ እንበል። በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ማውጫ ወይም በዎችታወር ላይብረሪ ተጠቅመህ ምርምር ስታደርግ በመጀመሪያ ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ዝምድና ያለውን ርዕስ ተመልከት። ለምሳሌ ማውጫው ላይ “ዴቲንግ” ወይም “ሜሬጅ” የሚሉትን ርዕሶች መመልከት ትችላለህ። ከዚያም ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጽሑፎች ለማግኘት ንዑስ ርዕሶችን ተመልከት። እንዲሁም ከዋናው ርዕስ በታች “ሲ ኦልሶ” የሚል መኖር አለመኖሩን ተመልከት፤ እንዲህ የሚል ካለ ከጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ተዛማጅነት ያላቸውን ሌሎች ርዕሶች ይጠቁምሃል።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ይሖዋ በድርጅቱ በኩል ላደረገው ዝግጅት ምስጋና ይግባውና እኛ ክርስቲያኖች ከሁሉ የተሻለ ምክር መስጠትም ሆነ መቀበል ችለናል። መክብብ 12:11 “የጠቢባን ቃላት እንደ ሹል የከብት መንጃ ናቸው፤ የተሰበሰቡ አባባሎቹም እጅግ ተቀብቅበው እንደ ገቡ ችንካሮች ሲሆኑ፣ ከአንድ እረኛ የተሰጡ ናቸው” ይላል። በፍቅር የተሰጠ ጠቃሚ ምክር ልክ እንደ “ከብት መንጃ” ማለትም ገበሬዎች ከብቶችን ለመምራት እንደሚጠቀሙበት ሹል በትር ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ ይመራል። ‘ተቀብቅበው የገቡ ችንካሮች’ ወይም ሚስማሮች አንድ ነገር ተያይዞ እንዲቆይ ያደርጋሉ። በተመሳሳይም ጥሩ ምክር መስጠት ዘላቂ የሆነ ውጤት ያስገኛል። ጠቢባን ‘የእረኛቸውን’ ማለትም የይሖዋን ጥበብ የሚያንጸባርቁ ‘የተሰበሰቡ አባባሎችን’ በመመርመር ታላቅ ደስታ ያገኛሉ።

ምክር በምትሰጥበት ጊዜ የዚህን እረኛ ምሳሌ ተከተል። ምክር ስንጠየቅ ጥሩ አድማጭ መሆናችን ከተቻለ ደግሞ ጠቃሚ ምክር መስጠታችን እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! የምንሰጠው ምክር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ከሆነ ምክሩ ግለሰቡን የሚጠቅም ከመሆኑም በላይ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኝ ሊረዳው ይችላል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ