ማደግህ ለሁሉም ግልጥ ሆኖ ይታይ
1 መሻሻልና እድገት የእውነተኛ ክርስትና አንዱ ምልክት ነው። የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንደመሆናችን የእርሱን አመራር እንከተላለን። ራሳችንን ለአምላክ ቅዱስ መንፈስ ስናስገዛ “ሙሉ ሰውም ወደ መሆን የክርሰቶስም ሙላት ወደሚሆን ወደሙላቱ ልክ” እንደርሳለን። (ኤፌ. 4:13) ከዚያም በ1 ጢሞቴዎስ 4:15 (አዓት) ላይ ጳውሎስ እንደጠቆመው ‘ማደጋችን ለሁሉም ሰው ግልጥ ሆኖ ይታያል።’ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተከሰቱት አዳዲስ ሁኔታዎችና ያገኘናቸው ተጨማሪ ድጋፎች ማደጋችን በተለያዩ መስኮች መገለጡን አስፈላጊና ቀላል አድርገውታል።
2 በይሖዋ ድርጅት በኩል ለምናገኘው የመንፈስ ቅዱስ አመራር ራሳችንን ካስገዛንና መሻሻል የምናደርግ ከሆነ እድገታችን ግልጥ ሆኖ የሚታይበት አንዱ ዘርፍ የመስክ አገልግሎታችን ነው። በግለሰብ ደረጃ ሁኔታህ እንዴት ነው? መሻሸላል የምታደርግ ነህን? እድገት አሳይተሃልን? ለምሳሌ ያህል ሕጋዊ እውቅና ከማግኘታችን በፊት ታደርግ ከነበረው በተለየ መንገድ ትሰብካለህን? ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ማገልገል የወርኃዊ አገልግሎትህ ቋሚ ክፍል ሆኗልን? እንዲሁም ብዙ ቁጥር ካላቸው እግረኞች ለይቶ የምሥራቹ አገልጋይ እንደሆንክ የሚያሳውቅህን የአገልግሎት ቦርሳ ትይዛለህን? በትልልቅ ስብሰባዎችና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የሚሰጡትን ሐሳቦች በመከተል የተለያዩ አቀራረቦችን፣ መግቢያዎችንና የመወያያ ርዕሶችን ትጠቀማለህን? ወይስ አሁንም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ወይም ስለ አምላክ መንግሥት መናገር እንደምትፈልግና አድማጭህ ስለጉዳዩ ለመወያየት ፍላጎት እንዳለውና እንደሌለው ትጠይቃለህ? በየወሩ የመንግሥት አገልግሎታችን ጥሩ ጥሩ ሐሳቦችን ያቀርባል። ይሖዋም እነዚህን ሐሳቦች በሥራ ላይ በማዋል መሻሻል የሚያሳዩትን ይባርካል።
3 መሻሻል የሚያደርጉ አስፋፊዎች በአገልግሎታቸው መጽሔቶችን ከመጠቀም የሚገኘውን ደስታ ቀምሰዋል። ሁልጊዜ መጽሔቶች አይለዩአቸውም፤ እንዲሁም አጭር አቀራረቦችን በመጠቀም መጽሔት የሚያበረክቱባቸውን ቀኖችም መድበዋል። በዓመት አራት ጊዜ የሚወጣው ባለ ሙሉ ቀለም ንቁ! መጽሔት ሲደርሰን ሁለት ዓይነት መጽሔቶችን በአንድ ላይ ማበርከት ስለምንችል በመጽሔት ተጠቅሞ ማገልገሉ ይበልጥ ማራኪ ይሆንልናል። በደብረ ብርሃን የሚገኝ አንድ አቅኚ በቅርብ ጊዜ በአንድ ወር ውስጥ 73 መጽሔቶችን ሲያበረክት በአዲስ አበባ አንዳንድ ረዳት አቅኚዎች እያንዳንዳቸው ከ100 የሚበልጡ መጽሔቶችን ሪፖርት አድርገዋል። አንድ ትልቅ ጉባኤ 746 መጽሔቶችን አበርክቷል። ብዙውን ጊዜ እነዚህን መጽሔቶች ከአንድ የሚበልጡ ሰዎች ያነቧቸዋል። በእነዚህ መጽሔቶች አማካኝነት የሚሰጠውን ሰፊ ምሥክርነት እስቲ አስቡ! በዚህ መጽሔቶችን በአገልግሎት በመጠቀም መስክ መሻሻል ልታሳይ ትችላለህን? የምታበረክተውን መጽሔት ብዛት በግልህ ለምን አታዝም?
4 አንድ ሰው እድገቱን በግልጥ ሊያሳይበት የሚችልበት ሌላው የአገልግሎታችን ዘርፍ በመንግሥት አገልግሎታችን መጽሔት ላይ በየወሩ ስለሚበረከቱ ጽሑፎች የሚወጣውን ማስታወቂያ ሥራ ላይ ማዋል ነው። ከይሖዋ ድርጅት ጋር እኩል መራመድና በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የሚወጡትን ሐሳቦች ተግባራዊ ማድረግ ትልቅ እርካታ ይሰጣል። ፍላጎት ያለው ሰው ስታገኙ ከቤት ወደ ቤት መመዝገቢያ ቅጽ ይዛችሁ በመሄድ ማስታወሻ ለመያዝ ትጠቀሙበታላችሁን? ይህም በዛ ያሉ ተመላልሶ ተመላልሶ መጠየቆችን ለማግኘትና በተሻለ መንገድ ለማነጋገር ይረዳል። ከዚያስ በኋላ እነዚህን ተመላልሶ መጠየቆች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ግብ አድርጋችሁ በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የሚወጡትን ሐሳቦች ተጠቅማችሁ ታነጋግራላችሁን? ሌላው ቀርቶ አነስተኛ የማንበብ ችሎታ ያላቸው አስፋፊዎች እንኳ በብሮሹሮቻችን በመጠቀም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መምራት ይችላሉ!
5 በስደቱ ወቅት ወንድሞቻችን ጠንካሮችና መሻሻል የሚያሳዩ ሆነው ለመገኘት ዘወትር መንፈሳዊ ምግብ መመገቡ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ተረድተው ነበር። ከእነዚህ ተጽዕኖዎች አንዳንዶቹ አሁን የሉብንም። ይሁንና ሰይጣን በመንገዳችን ላይ ሌሎች ወጥመዶችንና ማሰናከያዎችን ከማኖር አይቆጠብም። የዚያኑ ያህል ደግሞ ተጨማሪ መንፈሳዊ ምግብ አግኝተናል፤ ሳምንታዊ ስብሰባዎቻችንም የበለጠ ይዘት አላቸው። መንፈሳዊ ምግብ እንድናገኝ ለተደረጉልን ለእነዚህ ዝግጅቶች ከፍተኛ ግምት በመስጠት ሙሉ በሙሉ እየተጠቀምንባቸው ነውን? እድገት እያደረግን ለመቀጠል፣ ባለንበት ከመቆም ወይም ወደ ኋላ ከመንሸራተት ለመዳን ከፈለግን የግል ጥናት ማድረግ፣ ለስብሰባዎች መዘጋጀትና አዘውትሮ በስብሰባዎች ላይ መገኘታችን የግድ ነው። እድገታችሁ እንዲቀጥልና ለሁሉም ሰው ግልጥ ሆኖ እንዲታይ ለእነዚህ ነገሮች ትኩረት ስጧቸው። — 1 ጢሞ. 4:15
6 በአስተሳሰባችንና በግል ጠባያችን እድገት እያደረግን የምንቀጥልባቸው መስኮች ሁልጊዜም ይኖራሉ። ለምሳሌ ያህል በዓለም የዘረኝነትና የጎሣ ኩራት እየጠነከረ የሚሄድ በሚመስልበት በአሁኑ ወቅት እንደነዚህ ዓይነቶቹን የሥጋ ባሕርያት በልባችንና በአእምሮአችን ውስጥ ቦታ ነፍገናቸዋልን? አዲሱን ሰውነት በመልበስ፣ ከአሕዛብ ለተመረጡት ዕቃዎች ማለትም ለዓለም አቀፉ ወንድማማች ማኅበር ያለንን ፍቅር በማሳደግ እድገት እያደረግን ነውን? (1 ጴጥ. 2:17፤ ሐጌ 2:7) በዚህ አቅጣጫ ምንም ዓይነት ጉድለት ካለን መሪያችን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን በመከተል ረገድ ድካም እንዳለብን ያሳያል።
እድገታችን ለሁሉም ግልጥ ሆኖ ይታይ ዘንድ እነዚህን ማሳሰቢያዎችና ሐሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ አሁንም ጊዜው ገና አላለፈብንም።