በብሮሹሮች በመጠቀም የአምላክ ቃል አስተማሪዎች ሁኑ
1 እያንዳንዱ ውስን የይሖዋ አገልጋይ የአምላክን ቃል ለሌሎች በማስተማሩ ሥራ የመካፈል ኃላፊነት አለበት። “አሕዛብን . . . እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” የሚለውን ተልዕኮ የሰጠን በሰማይና በምድር ሁሉ ላይ ሥልጣን ያለው አካል መሆኑን ስንገነዘብ ይህ ኃላፊነት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ግልጽ ይሆናል። (ማቴ. 28:18–20) ስለዚህ ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ መካፈል አስተማሪዎች እንድንሆን ይጠይቅብናል!— 2 ጢሞ. 2:2
2 በነሐሴ ወር ብሮሹር ስናበረክት በማስተማር ችሎታችን መጠቀም እንችላለን። ትኩረት የሚስቡ ጥቂት ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦችን ከውስጣቸው ለመምረጥና ውይይት ለማስጀመር ሊረዱን የሚችሉ አንዳንድ ነጥቦችን ማዘጋጀት እንችላለን።
3 “አምላክ ስለ እኛ በእርግጥ ያስባልን?” የተባለውን ብሮሹር ስታበረክት እንዲህ ልትል ትችላለህ:-
◼ “አብዛኞቹን ጎረቤቶችዎን ስናነጋግር ወንጀል፣ ሽብር ፈጠራና ዓመፅ በፍጥነት መስፋፋቱ እንዳሳሰባቸው ተረድተናል። ይህ ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ችግር የሆነው ለምንድን ነው ብለው ያስባሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] መጽሐፍ ቅዱስ ይህ እንደሚሆን አስቀድሞ መናገሩ ለእኛ ልዩ ትርጉም አለው። [2 ጢሞቴዎስ 3:1–3ን አንብብ።] ይህ ‘በመጨረሻ ቀኖች’ እንደሚከናወን ልብ ይበሉ። ይህም አንድ ነገር ወደ መጨረሻ እየመጣ እንዳለ ያሳያል። ይህ ነገር ምን ይመስልዎታል?” መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት። ገጽ 22 አውጥተህ ሥዕሉን አሳየውና በዚህ ገጽ ላይ ከተጠቀሱት ጥቅሶች በአንዱ ወይም በሁለቱ ላይ ተወያዩ። እነዚህ በረከቶች በቅርቡ ይመጣሉ ብለን የምናምነው ለምን እንደሆነ ሌላ ጊዜ ተመልሰህ የምትነጋገሩበትን ቀን አመቻች።
4 “የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው? እንዴት ልታውቀው ትችላለህ?” የተባለውን ብሮሹር ስታበረክት የሚከተለውን አቀራረብ ለመጠቀም ትፈልግ ይሆናል።
◼ “ብዙ ሰዎች የሕይወትን እውነተኛ ዓላማ ለማግኘት ሲጥሩ አስቸጋሪ ሁኔታ ደርሶባቸዋል። ጥቂት ሰዎች የተወሰነ ደስታ አግኝተው ሲኖሩ ብዙዎች በሐዘንና በመከራ የተሞላ ሕይወት ይገፋሉ። አምላክ በዚህ ዓይነት ሁኔታ እንድንኖር ዓላማ የነበረው ይመስልዎታል? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] አምላክ ይህንን በመሰለ ዓለም ውስጥ እንድንኖር እንደሚፈልግ መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል።” ገጽ 21 ላይ ያለውን ሥዕል ካሳየኸው በኋላ ገጽ 25 እና 26 አንቀጽ 4–6 አውጣና አምላክ ቃል የገባው ምን እንደሆነ ግለጽለት። ተመልሰህ ስትሄድ ውይይት ለማድረግ እንዲያስችልህ “አምላክ የገባውን ቃል እንደሚፈጽም እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን?” ብለህ ጠይቅ።
5 በፊት ለፊቱና በጀርባው ላይ ያለውን ሥዕል ሙሉ በሙሉ በማሳየትና የሚከተለውን ጥያቄ በመጠየቅ “በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ ኑር!” የተባለውን ብሮሹር ማበርከት ትችላለህ:-
◼ “ደስተኛ ሰዎች በሞሉበት ይህንን በመሰለ ዓለም ውስጥ መኖር ይፈልጋሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ሰዎችን እንደሚወድና በዚህች ምድር ላይ ለዘላለም በደስታ እንዲኖሩ እንደሚፈልግ ይነግረናል።” ሥዕል ቁጥር 49 አውጣና ከተጠቀሱት ጥቅሶች መካካል አንዱን አንብብ። ከዚያም ሥዕል ቁጥር 50 አሳየውና በዚህ ገነት ውስጥ ለመኖር ከፈለግን ምን ማድረግ እንዳለብን ግለጽ። ሌላ ጊዜ ተመልሰህ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነ ከእርሱ ጋር ለመወያየት እንደምትፈልግ ንገረው።
6 ‘ለትምህርታችን ትኩረት በመስጠት ማደጋችን በግልጥ ሲታይ’ ይሖዋ ይደሰታል። (1 ጢሞ. 4:15, 16) ‘የመልካምን ወሬ የምሥራች’ ለመስማት የሚናፍቁ ሰዎችን ለመርዳት ጥረት ስናደርግ ብሮሹሮቻችን ከፍተኛ እገዛ ሊያበረክቱልን ይችላሉ።— ኢሳ. 52:7