ሌሎችን ለማስተማር ብቁና የታጠቁ መሆን
1 ሙሴ የይሖዋ ወኪል ሆኖ እንዲሠራ በተሾመ ጊዜ የአምላክን ቃል ለፈርዖን ለማወጅ ብቃት እንዳለው ሆኖ አልተሰማውም ነበር። (ዘጸ. 4:10፤ 6:12) ኤርምያስ የይሖዋ ነቢይ ሆኖ ለማገልገል እንዴት መናገር እንደሚችል እንደማያውቅ ለአምላክ በመናገር በራስ የመተማመን መንፈስ እንደሚጎድለው አሳይቷል። (ኤር. 1:6) እነዚህ ነቢያት መጀመሪያ ላይ በራሳቸው የመተማመን መንፈስ የጎደላቸው የነበሩ ቢሆኑም እንኳን ሁለቱም ደፋር የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸውን አስመስክረዋል። አምላክ ሁለቱንም በተሟላ መንገድ ብቁ እንዲሆኑ ረድቷቸዋል።
2 በዛሬው ጊዜም ቢሆን፣ ለይሖዋ ምስጋና ይግባውና አገልግሎታችንን በልበ ሙሉነት ለመፈጸም የሚያስችሉን ነገሮች ሁሉ አሉን። (2 ቆሮ. 3:4, 5፤ 2 ጢሞ. 3:17) እኛም የተሟላ መሣሪያ እንዳሉት የሰለጠነ መካኒክ የተሰጠንን አገልግሎት በጥሩ ችሎታ ለማከናወን እንድንችል ተገቢ በሆነ መንገድ የታጠቅን ነን። በጥር ከ1984 በፊት የታተሙ 192 ገጽ ያላቸውን መጽሐፎች እናበረክታለን። ከእነዚህ መጽሐፎች መካከል ታላቁን አስተማሪ ማዳመጥ፣ ጎድስ “ኢተርናል ፐርፐዝ ” ናው ትራያፊንግ ፎር ማንስ ጉድ ወይም ማንስ ሳልቬሽን አውት ኦቭ ዎርልድ ዲስትረስ አት ሃንድ! የተሰኙት መጽሐፎች በጉባኤያችሁ ይኖሩ ይሆናል። በተጨማሪም በሕይወት ተርፎ ወደ አዲስ ምድር መግባት የተሰኘውንም መጽሐፍ ማበርከት እንችላለን። ምንም እንኳን እነዚህ መንፈሳዊ መሣሪያዎች አዳዲስ ባይሆኑም በውስጣቸው የያዟቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ መልእክቶች አሁንም ቢሆን ወቅታዊ ናቸው። በተጨማሪም እነዚህ መጽሐፎች ሰዎች እውነቱን እንዲያውቁ ይረዷቸዋል። ከዚህ ቀጥሎ የቀረቡትን የመግቢያ ሐሳቦች ለምታበረክቷቸው ለየትኞቹም መጽሐፎች እንደ ሁኔታው በመለዋወጥ ልትጠቀሙባቸው ትችላላችሁ።
3 በአምላክ ቃል ላይ ፍላጎት ለማነሳሳት ትምህርትን የሚመለከት ርዕስ መጠቀም ይቻል ይሆናል። የሚከተለውን በመናገር ውይይቱን መጀመር ትችላለህ:-
◼ “በዛሬ ጊዜ ጥራት ያለው ትምህርት ማግኘት በጣም አሳሳቢ ነገር ሆኗል። በእርስዎ አመለካከት ታላቅ ደስታና የተሳካ ኑሮ የሚያስገኘው ከሁሉም የሚበልጠው ትምህርት የትኛው ነው ይላሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] አምላክ የሚሰጠውን እውቀት የሚያገኙ ሁሉ ዘላለማዊ ጥቅሞችን ሊያገኙ ይችላሉ። [ምሳሌ 9:10, 11ን አንብብ።] ይህ መጽሐፍ [ለማበርከት ያሰብከውን መጽሐፍ ርዕስ ተናገር] በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ነው። ወደ ዘላለም ሕይወት ሊመራ የሚችለው ብቸኛው የእውቀት ምንጭ ማን እንደሆነ ያመለክታል።” መጽሐፉ ከያዛቸው ምሳሌዎች መካከል (ለምሳሌ በሕይወት መትረፍ ከተሰኘው መጽሐፍ ገጽ 7 አንቀጽ 5ን) አንዱን አሳይ። መጽሐፉን አበርክትና ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ ዝግጅት አድርግ።
4 መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ትምህርት አስፈላጊ ስለመሆኑ ካወያየኸው ሰው ጋር ውይይት ለማድረግ ተመልሰህ በምትሄድበት ጊዜ እንዲህ ለማለት ትችላለህ:-
◼ “ባለፈው ጊዜ የተረጋገጠ የወደፊት ተስፋ ሊሰጠን የሚችለው የጥበብና የትምህርት ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሆነ ተወያይተን ነበር። እርግጥ ከቅዱሳን ጽሑፎች ማወቅ የሚገባንን ነገር ለመማር ጥረት ይጠይቃል። [ምሳሌ 2:1-5ን አንብብ።] ብዙ ሰዎች አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን መረዳት አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል። ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ትምህርቶች በይበልጥ እንዲያውቁ ለመርዳት በሰፊው የምንጠቀምበትን ዘዴ ባጭሩ ባሳይዎት ደስ ይለኛል።” በሕይወት መትረፍ የተሰኘውን ያበረከትከውን መጽሐፍ ገጽ 7 አንቀጽ 7ን የመሰለ ተስማሚ ቦታ ግለጥና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዴት እንደሚደረግ በአጭሩ አሳይ። የቤቱ ባለቤት ቋሚ ጥናት እንዲደረግለት የሚፈልግ ከሆነ ለማጥናት የምንገለገልበትን ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተሰኘ መጽሐፍ ይዘህ እንደገና እንደምትመለስ አብራራ።
5 “ኢተርናል ፐርፐዝ ” የተሰኘውን መጽሐፍ የምትጠቀም ከሆነ እንዲህ ብለህ በመናገር መጀመር ትችላለህ:-
◼ “[ሰላምታ።] ከአምላክ ቃል ውስጥ አንድ አበረታች ሐሳብ ልናካፍልዎት እንፈልጋለን። ኢየሱስ [ማቴዎስ 6:9, 10ን ጠቅሰህ] እንድንጸልይ ያስተማረን ለምንድን ነው ብለው ራስዎን ጠይቀው ያውቃሉ? ምንም እንኳን የአምላክ ስም በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ ቢገኝም አብዛኞቹ ያነጋገርናቸው ሰዎች የአምላክን ስም ሰምተው እንደማያውቁ ገልጸውልናል። አንድ አጭር አንቀጽ እንዳነብልዎት ይፍቀዱልኝ። [ገጽ 16 አንቀጽ 21ን አውጥተህ አንብብ።] የአምላክ ዘላለማዊ ዓላማ በቅርብ ጊዜ ፍጻሜውን ሲያገኝ የአምላክ ስም ይቀደሳል። ይህም ከአምላክ መንግሥት ጋር ተዛማጅነት ያለው ነው። ኢየሱስ በናሙና ጸሎቱ ውስጥ ያካተታቸውን ቃላት ትርጉም ከዚህ መጽሐፍ በይበልጥ ሊማሩ ይችላሉ።”
6 የሃይማኖት ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች የመጸለይ ልማድ ስላላቸው እንዲህ በማለት በዚህ ርዕስ ላይ ውይይት ለመጀመር ትችላለህ:-
◼ “ብዙዎቻችን በሕይወታችን ውስጥ አንድ ወቅት ላይ አምላክ እንዲረዳን ወደ እርሱ እንድንጸልይ የሚያስገድዱ ችግሮች ገጥመውናል። ሆኖም ብዙ ሰዎች ለጸሎቶቻቸው መልስ እንዳላገኙ ተሰምቷቸዋል። የሃይማኖት መሪዎችም እንኳን ሰላም እንዲሰፍን በአደባባይ የሚያቀርቡት ጸሎት ተሰሚነት ያላገኘ ይመስላል። እንዲህ የምንለው ጦርነትና ዓመፅ የሰውን ልጆች ማስጨነቃቸውን ስለቀጠሉ ነው። በእርግጥ አምላክ የሚቀርቡለትን ጸሎቶች ይሰማል? የሚሰማስ ከሆነ ብዙ ጸሎቶች መልስ የማያገኙት ለምንድን ነው? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ለምናቀርበው ጸሎት መልስ ማግኘት ከፈለግን ምን ነገሮች ሊሟሉ እንደሚገባቸው መዝሙር 145:18 ይናገራል። [ጥቅሱን አንብብ።] አንዱ ብቃት ለአምላክ የሚቀርቡ ጸሎቶች ከልብ የመነጩና የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሰፈሩት እውነቶች ጋር መስማማታቸው ነው።” የምታበረክተውን መጽሐፍ ካሳየኸው በኋላ ስለ ጸሎት ዋጋማነት መጽሐፉ የሚናገረው ምን እንደሆነ ጠቁመው። [ለምሳሌ ኢተርናል ፐርፐዝ ከተሰኘው መጽሐፍ ገጽ 190 አንቀጽ 7ን ወይም በሕይወት መትረፍ ከተሰኘው መጽሐፍ ገጽ 181 አንቀጽ 14ን ማሳየት ትችላለህ።]
7 ጸሎትን በሚመለከት ካለፈው የሚቀጥል ውይይት በምታደርግበት ጊዜ ይህን አቀራረብ መጠቀም ትችል ይሆናል:-
◼ “ጸሎትን አስመልክቶ ያደረግነው ውይይት አስደስቶኛል። ኢየሱስ ስለምን ነገሮች መጸለይ እንደሚቻል ከተናገረው ነገር ጠቃሚ መመሪያ እንዳገኙ ጥርጥር የለውም።” ማቴዎስ 6:9, 10ን አንብብና ኢየሱስ በናሙና ጸሎቱ ውስጥ የጠቀሳቸው ትልቅ ትኩረት የሚሰጥባቸው ቁም ነገሮች የትኞቹ እንደሆኑ ለይተህ ግለጽ። እውቀት ከተባለው መጽሐፍ “ከአምላክ ጋር መቀራረብ የምትችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ምዕራፍ 16ን አሳየውና ይህን ምዕራፍ እንዴት ማጥናት እንደሚቻል ማሳየት ትችል እንደሆነ ጠይቀው።
8 የአምላክን እውቀት ለሌሎች ለማስተላለፍ “ለዚህ ነገር የሚበቃ ማን ነው?” ብለን እንጠይቅ ይሆናል። ቅዱሳን ጽሑፎች ‘እኛ ነን’ የሚል መልስ ይሰጣሉ።— 2 ቆሮ. 2:16, 17