ለይሖዋ የአምልኮ ቦታ አክብሮት አሳዩ
1 ሰው ቤት በእንግድነት በምንሄድበት ጊዜ ለሰውዬው ንብረት አክብሮት በማሳየት ንብረቱን ላለማበላሸት እንጠነቀቃለን፤ ከዚህም በተጨማሪ የቤተሰቡን ሥርዓታማ ልማድ አናስተጓጉልም። የይሖዋ እንግዶች በምንሆንበት ጊዜ የበለጠ አክብሮት ማሳየታችን ምንኛ የተገባ ይሆናል! በቤቱ እንዴት መመላለስ እንደሚገባን ማወቅ ያስፈልገናል። (መዝ. 15:1፤ 1 ጢሞ. 3:15) ክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችንን የምናደርገው በመንግሥት አዳራሽም ሆነ በግል መኖሪያ ቤት ወይም በተከራየነው የሕዝብ አዳራሽ ቦታው፣ ‘ክብሩ ከምድርና ከሰማይ በላይ ከፍ ያለው’ የይሖዋ ቤት እንደሆነ በመቁጠር ለአምልኮ ቦታችን ሁልጊዜ አክብሮት እናሳያለን።—መዝ. 148:13 የ1980 ትርጉም
2 ለይሖዋ የአምልኮ ቦታ አክብሮት ማሳየት ሲባል ትልልቅ ስብሰባ የሚደረግበትን አዳራሽም ሆነ የመንግሥት አዳራሽ ወይም የግል መኖሪያ ቤት ለይሖዋ ክብር በሚያመጣ መንገድ በንጽህናና በጥሩ ሁኔታ መያዝን ያጠቃልላል። ስለዚህ ከመግባታችን በፊት ጫማችንን እናጸዳለን። በእጃችን ግድግዳውን እንዳናቆሽሽ እንጠነቀቃለን። መሬት ላይ የወደቁ ወረቀቶችን፣ ፕላስቲኮችንና ሌሎች ነገሮችን እናነሳለን። በጽዳት ፕሮግራሙ መሳተፍን እንደ መብት እንቆጥረዋለን። ይህ ደግሞ የመጸዳጃ ቤቱን በንጽህና መያዝን ይጨምራል። (ዘዳ. 23:14) የተሰበሩ ወንበሮችና የለቀቁ ሚስማሮች አደጋ ከማስከተላቸውም በላይ የሰዎችን ትኩረት ጠቃሚ ከሆነው መልእክታችን ስለሚሰርቁ አልፎ አልፎ ጥገና ማድረግ ያስፈልጋል። ከዚህም በተጨማሪ የመሰብሰቢያ ቦታችን በተወሰነ ጊዜ ቀለም መቀባት ያስፈልገዋል። መጽሐፍ ጥናት የሚደረግበት ቤት ቀለም መቀባት ካስፈለገው እዚያ የሚሰበሰቡ ወንድሞች በዚህ ረገድ በገንዘብም ሆነ በጉልበት ሊረዱ ይችላሉ። እነዚህ ለይሖዋ የአምልኮ ቦታ አክብሮትና ትኩረት እንደምንሰጥ የምናሳይባቸው መንገዶች ናቸው።—ነህ. 10:39
3 አክብሮት የጎደለን ሆነን ከመገኘት መጠበቅ የሚቻልበት መንገድ፦ አምልኮታችን ክብር የተሞላና ቅዱስ መሆኑን ከተገነዘብን በማንሾካሾክ፣ በመብላት፣ ማስቲካ በማላመጥ፣ ወረቀት በማንኮሻኮሽ፣ አሁንም አሁንም ወደ መጸዳጃ ቤት በመመላለስ ወይም አርፍዶ ወደ ስብሰባዎች መሄድን ልማድ በማድረግ ሌሎችን መረበሽ እንደማንፈልግ የታወቀ ነው። አክብሮትና አድናቆት ያላቸው ወላጆች ልጆቻቸው የመንግሥት አዳራሹንም ሆነ መጽሐፍ ጥናቱ የሚካሄድበትን ቤት ወለል፣ የሶፋ ልብስ ወይም ግድግዳ እንዲያቆሽሹ አይፈቅዱላቸውም። የስብሰባ ቦታችን የመጫወቻ ቦታ አለመሆኑን በመንገር ስብሰባው ካለቀ በኋላም ቢሆን ይቆጣጠሩዋቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ በስብሰባ ቦታ አሳፋሪ የሆነ ባሕርይ ማሳየት፣ የስንፍና ንግግር ወይም ጸያፍ ቀልድ ማውራት ፈጽሞ ተገቢ አለመሆኑን ሁላችንም እንደምንስማማበት ጥርጥር የለውም።—ኤፌ. 5:4
4 የክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችንን ዓላማ ሁልጊዜ ካስታወስን እኛም ሆንን ልጆቻችን ‘መኖር ለመረጥንበት’ የይሖዋ የአምልኮ ቦታ ተገቢውን አክብሮት ማሳየታችንን እናረጋግጣለን።—መዝ. 84:10